ምህረትና የደርግ ባለስልጣኖች

ያላደፈ ትዝታዬ እንደሚነግረኝ ከሆነ ግፍ በኢትዪጵያ ምድር ላይ በቃኝ እንደማይል የሃምሌ ዝናብ መውረድ ከጀመረ ዘመናት ቆጥረናል። ትሻልን እናመጣለን በልን ለውጥ ስንሻም የጨነቀው እርጉዝ ያገባል እንዲሉ የአሁኑ ካለፈው እየባሰ ጊዜ የሻረውን እንድናመሰግን ያድርገናል። ከሰሞኑ ከወደ አዲስ አበባ የሚናፈሰው ወሬ እንደሚጠቁመን ከሆነ የቀድሞ የደርግ ባለስልጣኖች በምህረት ወያኔ ከከተታቸው ዘብጥያ ይፈታሉ የሚል ነው። ወሬው ማለፊያ ነው። የአፍሪካ ትልቁ ችግር ያዘው ጥለፈው እያለን ለመኖር ማስር መግደላችን በወንድምና እህት ደም ላይ ጮቤ መርገጣችን ነው። ምህረትን አናውቅም። ብቀላን የተሞላ አእምሮም ጤናማ እይታ የለውም። ከራሱ የቁመና ጥላ ጋር የተጣላ ነውና። አሁን ወያኔ የምህረት ወሬ ሲያወራልንም እሰየው ያሰኛል።  ይሁን እንጂ ምህረት የሚለው ቃል ምን ማለት ነው? ያን ያህል አስከፊ በደል በኢትዪጵያ ህዝብ ላይ ያደረሱት ለምህረት ሲታጩ በእነርሱ ቀጥተኛ ትእዛዝ አብረዋቸው ሲገርፉና ሲገድሉ የነበሩ ዛሬ በየክልሉ ለዘመናት ታስረው የሚገላቱትን ይጨምራል? ወይስ ለምዕራቡ የወሬ ፍጆታ ከመቃብር በራፍ ላይ የቆሙ አዛውንት የደርግ ባለስልጣናትን በመልቀቅ እዪልን ለማለት በፊታችን ላይ ወያኔ ያንጠለጠለው ሜታ ከረሜላ ነው? ምህረት ሁሉን ያካታል። ያለፈን ይረሳል። ምህረት በሃገር ውስጥና በውጭ ሃገር በየምክንያቱ የተወንጀሉትንና በደልም ሰርተው የውን ምህረት የሚያሻቸውን ሁሉ ያጠቃላል። ብሄራዊ እርቅ ዘር፤ጎሳንና ሃይማኖትን ሳይለይ ሁሉን በምህረቱ መሽፈን አለበት። ለምሳሌ ከወያኔ ጋር ከጎን ቆመው ለአያሌ ዘመናት ታግለው ዛሬ በባእድ ሃገር የሚንከራተቱ የቀድሞ የህወሃት ታጋዬችን ሁሉ መጨመር አለበት። እውነተኛ በሄራዊ እርቅ ሁሉን ያካታል። ያጠፋን፤ ሳያጠፉ በሃሰት የተወንጀሉን ሁሉ ያካትታል። ዛሬ በወያኔ ድብቅና ይፋ እስርቤቶች ፍዳ የሚቆጥሩትን አእላፍ ወገኖቻችን ያጠቃልላል። ያለበለዛ አንድ እንጭትን እንደማሰር ይቆጥራል። ባጭሩ ዝም ብሎ መልፋት ነው።

ሰለደርግ በዙ ውንጀላዎች ተወስተዋል። ከተከስሱበት አንድ ክስ ግን በጭራሽ ከእውነት ጋር አይዛመድም። ደርግ በምሥራቃዊው የርዕዮተ – ዓለም እይታ አይኑ ታውሮ በደንበር ገተር የረገጠውን ሁሉ እሳት ከመለኮሱ ውጭ የዘር አድሎ አልነበረበትም። የዘር ማጥፋት ውንጀላው ሰንካላ ነው። ደርግ በዘር አያምንም አምኖም አያውቅም። ሲመራበት ከነበረው ሶሻሊስት መርህ ጋርም የዘር ማጥፋት ዘመቻው አብሮ አይሄድም። ደርግ ዘረኛ አልነበረም። ግራም ነፈሰ ቀኝ የአሁኖቹ አለቆቻችን አንድ ሊገነዘቡት የሚገባ ነገር አለ። ይቅር መባባል ባህላችን ነው። ይህ ባህል እንዲስፋፋና ሁላችንም በሰላም በደስታ እንድንኖር ፍትህ በሃገሪቱ እንዲሰፍን ከተፈለገ ሁለገብ መንግስታዊ (ላዕላይና ታህታይ) መዋቅራት በሁሉም የሃገሪቱ ዜጎች እንዲጣመርና እንዲመራ  መደረግ አለበት። ወያኔ ብቻ ከጠራው ምንጭ ተጎንጭቶ ከደፈረሰ በህዋላ ህዝባችንን ኑና ጠጡ ማለት መቀለድ ይሆናል። ሰው በችሎታውና በእውቀቱ ዘሩ ከተመን ሳይገባ የሚኖርባት የእኩል የሆነች ሃገር ማዋቀር እስካልተቻለ ድረስ የምናደርገው የኢኮኖሚ ግንባታና የምህረት ግርግር የሮም አወዳደቅ ነው የሚሆነው።

ቆይተን እንይ

አደፍርስ ተሰማ