የቀበሌ ጥሩምባ በአሜሪካ

የሃበሻው ህይወት በጭቃ የተለወሰ ነው። ያለፈውን መከራ ተውኩትና ተወኝ ሲል የሙጥኝ እያለው እንሆ በባህር ማዶም የስደት ኑሮውን እንዳይገፋበት እንቅፋት ሆኖበታል። አንድ የማውቀው ኤርትራዊ ነኝ ባይ (ተወልዶ ያደገው ደሴ ነው) ወያኔ  እናቱንና አባቱን ኤርትራዊ ናቹህ በሚል የተጣመመ ፓለቲካ ከደሴ አባሮ አስመራ ስለአስገባቸው እነሱን ለመጠየቅ ቪዛ የኤርትራን ኤምባሲ ይጠይቃል። እነሱም ከምትኖርበት ስቴት ይህን ሰው ደውለህ በማናገር ወረቀት ይጽፍልሃል እሱ የሚሰጥህን ወረቀትና ማመልከቻህን ለእኛ አቅርብ ይሉታል። ሰልክ ደውሎ የተባለውን ሰው ያገኘዋል። በቀጠሮአቸው መስረት ይገናኙና ወረቀት እንዲጽፍለት ይጠይቀዋል። እሱም እሺ እስቲ መዝግብ ላይ ስምህን ልመልከት ይለዋል። በርግጥም ስሙ መዝገብ ላይ አለ ግን መዋጮ አልከፈለም (፪%)፤ የኤርትራ ስብሰባ ላይ አልተገኘምና ሌሎች ነገሮችንም በማጣቀስ ወረቀት ሊሰጠው እንደማይችል ይነግረዋል። እሱም በጣም በማዘንና በመበሳጨት ያሰናዳውን ማመልከቻ ቀዳዶ በመጣል አስመራ ለቤተሰብ ደውሎ መምጣት እንደማይችል ያስረዳቸዋል። ቤተሰቡም ሰው እንደሞተ ተላቅሰው ነገሩ በዚሁ ይዘጋል።

ይህን ሁሉ በስልክ ለእኔ ሲያጫውተኝ እያለቀሰ ነበር። እኔም አብሬው አለቀስኩ። ትንሽ ሳይቆይ ሌላ የስልክ ጥሪ መጣና አንስቼ አደፍርስ አልኩ። ሰላም ጤና ይስጥልኝ አለ። ማን ለበል። ጎይቶም ነኝ። ምነው ድምፅህ ቀየር አለብኝ አለኝ። እኔም ሳላመነታ ሰው ሳላቅስ ስለነብር ነው አልኩት። እርሱም ትንሽ ግራ ገባውና ማን ሞቶ ነው በማለት ጠየቀኝ። እኔም ማንም አልኩትና ከላይ ያለውን ታሪክ ነገርኩት። እርሱም እንባ ሲተናነቀው ተሰማኝ። በል ስለደወልክበት ጉዳይ እናውራ የእኛ ችግር ማለቂያ የለውም አልኩት። ወይ አንተ እኔስ የደወልኩት የገጠመኝን ላጫውትህ አይደል አለ። ቀጥል አልኩት። “የሰላይ ተሰላይ” የሚለውን መጽሃፍ ሃገርቤት እያለህ አንበሃል አለኝ። አዎን አቶ ማሞ ውድነህ የተረጎሙትን አንብቤአለሁ አልኩት። የማጫውትህ ገጠመኝ ከዛ መጽሃፍ ጋር ይገናኛል። መልካም አልኩት።

ለእራት ሰው ቤት ተጠርቼ ሄድኩ። ወደ ሃያ የምንሆን ሃበሾች (ኤርትራዊያን፤ኢትዮጵያዊያንና )አራት ነጮች ተሰባስበናል። ራቱ የተለያየ የሃበሻ ምግብ እንደ ብፌ አይነት ዝግጅት የተቀናበረ ነበር። ድለቱ፤ ክትፎው፤ ቀይና አልጫ ወጡ በያይነቱ። የሚበቃንን ያህል ምግብ ከወሰድን በህዋላ ስፍራ ስፍራ ይዘን መብላት ጀመርን። ከዚያም ውስኪ፤ ቢራ፤ ብራንዲና የተለያዩ መጠጦችን መጋት ጀመርን። ከመካከላችን አንድ ያልቅጥ ውስኪውን ይጋተው ጀመር። እኔም ቡና ያዝኩና ወደጎን ቅጭ አለኩ። ያለልክ ውስኪውን የሚጠጣው ሰው ከጎኔ በመቀመጥ ወሬ በመጀመር ያለልቡ ማን እንደሆነና ምን እንደሚሰራ ይነግረኝ ነበር። እየሞቀው ሲሄድም የአድዋ ተወላጅ መሆኑንና በአለንበት ከተማ የወያኔን የስለላ ቅርንጫፍ ተጠሪ መሆኑን ሲነግረኝ አጋጣሚውን በመጠቀም አንዳንድ ጥያቄ እጠይቀው ጀመር የሰጠኝ ምላሽ አሳዛኝና አሰቃቂ ነው። ወያኔ በስልጣን ላይ ለመቆየት የሚጠቀምባቸውን ብልሃቶች አስረዳኝ (ወደፊት በሌላ ስፍራ ዝርዝር አቅርባለሁ) የዚህ ሰው መለፍለፍ ደስ ያላለው ሌላው የወያኔ አባል ከእኔ ጎትቶ ወስደውና ጫዎታችን በዛው ተገታ። ብዙም ሳይቆይ ሌላ ሰው አጠገቤ ቁጭ አለ። እሱም እንደበፊቱ ሰው ሞቅ ብሎታል። ያው የፈረደበትን ውስኪ እንደ ውሃ ይጠጣል። ታዲያስ ኑሮ እንዴት ይዞሃል አልኩት። ኑሮ አይከፋም ፓለቲካ ግን ሰለቸኝ አለ። እኔም ከፈገግታ ጋር አሁንማ ነጻ ሃገር ሆናቹሃል ምን ችግር አለ አልኩት። ሳላስበው ምርር አለና አንተ በእኔ ቦታ ሆነህ ብታየው ነጻነቱ ባርነት ነው አለኝ። አንተ የምትኖረው አሜሪካ ምን ባርነት አለ አልኩት ያልገባኝ በማስመሰል። አንተ ታሾፋለህ አለኝ እንደ መቆጣት ብሎ። እኔ የማወራህ ስለ ኤርትራ ነው አለ። እሺ ቀጥል። እኔ ዛሬ ለዚህ ራት ጥሪ መምጣት አልፈለኩም ነበር አለ። ታዲያ ማን አስገደደህ ሰለው እንደመተክዝ አለና ሳያስበው ሻቢያ አለ። አሁን አንተ በተራህ መቀለድ ጀመርክ ስለው አይደለም። እውነቴን ነው አለኝ። ለስለላ ነው የመጣሁት አለና ቆመ። እኔም አብሬው በመቆም ያለልቡ ሚስጢር እንደሚያውጣ ገባኝና ምን ወሬ ይገኛል በለህ ነው አልኩት። እሱም የወያኔ ሰላይ አለ ስለተባለ በራት ስም ምን ሊያደራጅ ነው በማለት ነው አለኝና እርፍ። አያሳዝንም አደፍርስ? ሰው ከሃገሩ ተሰዶ በሰላም እንጀራ አለመቁረሱ? እረዳሃለሁ እመነኝ። ሰው ነፍሱን ሽጥዋል። አይዞህ ዛሬን በነገ አይን አትይ። የተሻለ ቀን ይመጣል አልኩትና ስልኩን ዘጋሁት።

እንጥብጣቢ ወሬ ፍለጋ በህዝባችትን ውስጥ ተሰግስገው የሻብያና የወያኔ የወሬ ጆኒያ በመሆን ወገናችን ኑሮን እንዳይገፋ እንቅፋት የሚሆኑትን ግለሰቦች ለይተን ማወቅ አለብን። አንድ የህግ ባለሙያ እንደነገረኝ እነዚህ ግለሰቦች ለሌላ መንግስት በስለላ ሥራ መሰማራታችውን በመረጃ ከቀረበ የመታሰርና ብሎም ማባረር ይቻላል። ትላንት የረሳነውን የቀበሌ ጥሩንምባ ቃናውን በዘርና በጎሳ አጣፍጠው በውጭው ዓለም ለስብሰባ ውጡ፧ መዋጮ ክፈሉ እያሉ ለመኖር ከኑሮ ጋር የሚታገለውን ህዝባችንን ባያዋክቡት ይሻላል።

አደፍርስ ተስማ