የሱዳን የመገንጠል ጥያቄና መጭው መከራ
የሱዳን የመገንጠል ጥያቄና መጭው መከራ
አሁን ሽር ጉድ የሚባልለት የደቡብ ሱዳን የመገንጠል ዘመቻ የሚያመጣውን የወደፊት ሰቆቃና ጠኔ አይናቸው ያለቅጥ የታወረው ፓለቲከኞች አሁን አይታያቸውም። ቢስሚላሂ ብሎ የሰው አንገት መቁረጥ ከጀመረ ወዲህ አክራሪው የእስልምና እምነት ሰው የማይጨብጠው እሳት ሆነዋል። በዚህም የተነሳ አብረው በሰላምና በፍቅር ለዘመናት ይኖሩ የነበሩ የአንዲት ሃገር ዜጎች መንታ መንገድ ለመከተል ተገደዋል። አሁን በውጭ እጅ ገፋፊነት ከሱዳን እንዲገነጠሉ ሹክ የሚባልላቸው የደቡብ ሱዳን ዜጎች አስከፊ ችግር ወደፊት እንደሚገጥማቸው ለመተንበይ እጣት መቁጠር አያስፈልግም።
አፍሪቃ በዚህ ሳቢያ ያላት ታሪክ አያኮራም። ሲያድ ባሬን አውርደን የተሻለ መንግስት እናመጣለን ያሉት የሶማሊያ አማጽያን አሁን ሶማሊያ ያለችበትን ሁኔታ ሲመለከቱ ፍጻሜው ካለፈው የከፋ እንደሆነ ይረዳሉ። የእርስ በእርስ ግድያውም ይቀጥላል። ህብረት ጉልበት ነው። መታገስ የተሻለ ሃሳብን ለማመዛዘን ጊዜ ይሰጣል። የአፍሪቃዊው አህጉር እደል – ፈንታ ግን የሚለካው በታጠቀ ሃይል ብቻ ነው። ለውጥ ብለን የምናውራውም የቀደመውን ግፈኛ ሌላው የተራበ ገፍትሮ በመጣል አለቅነቱን ሲያረጋግጥ ነው። ከእናት ሃገር መገንጠልና ብቻ መሆንም የህዝብን ሰቆቃ ለማራዘም እንጂ እዚህ ግባ የሚባል ፋይዳ የለውም። በአውሮፓም ሆነ በሌላ አህጉር ተገንጥሎ የተሳካለት ሃገር ካለ አመላክቱኝ። አሁን በአፍሪቃ ቀንድ ላይ ሃገር ነኝ የምትለው አድሲቱ ኤርትራ የስንቱን ሰው ደምና እንባ እንዳስፈሰሰችውና በማፍሰስም ላይ እንደሆነች ምስክር አያሻም። ወያኔ በአዲስ አበባ ሻበያ በአስመራ በህዝባችን ላይ የፈጸሙትና በመፈጸም ላይ ያሉት በደል በአሃዝ ለማስቀመጥ ይከብዳል። ደቡብ ሰዳንና ሰሜን ሱዳንም በዚህ ይመሰላሉ። አዎ አሁንም ደቡብ ሰዳንና ከቁራሽ የተረፈው ሱዳን መላተማቸው አይቀርም። በዛ ሳቢያ የሚፈጠረው ችግር ከቁራሽ ለተረፈችው ኢትዮጵያና ለተጎራባች ሃገሮች እንቅልፍ የሚነሳ የቤት ስራ ነው የሚሆነው።
ነጩ ዓለም ለራሱ ጎተራ ብቻ ነው የሚያስበው። የጥቁር ሰው ደም አይገደውም። ይህ እጃቸውን በከተቱበት የዓለም ከፍል ሁሉ አይተነዋል። አሁን ደቡብ ሱዳንን የሚገፋፉትም ለነዳጅ ጥቅምና ሰሜኑን ሱዳን በዓይነ ቁራኛ ለመመልከት ስፍራ ፍለጋ ብቻ ነው። ጊዜው መሽና ተረሳኝ እንጂ አንድ የህብረት ትምህርት መጽሃፍ አርእስቱ “አብሮ መኖር በዓለም ዙሪያ” ይባል ነበር። ዛሬ አብሮ መኖር እየቀረ የሃገራችን ተረት እንዳለው “በየወገንህ ቢሉት የመቶ አመት ቆዳ ገቢያ ወጥቶ ቆመ” እንዲሉ እየሆነ ነው። አብሮ መኖር ቀርቶ በስፍራው ዘረኝነትና ጠባብ ብሄርተኝነት ተካ የመገንጠል በሽታ በዛ። ቋንቋችን ተሰባጠረ፤ በክልል ተከፈልን። ሲያሞኙንም ፌዲራሊዚም ይሉናል። አፈናው፤ ግድያው፤ የዘር ማጥፋት ዘመቻው በይፋና በህቡዕ ቀጥሏል። የደቡብ ሱዳንም መከራ በመገንጠልዋ ይበዛል እንጂ ስክነት አያገኝም።
ቆይተን እንይ
አደፍርስ ተሰማ