ከጋብቻ በፊት ውል (Prenup)
ያለንበት ዘመን ሰው ካላነደደው እሳት የሚሞቅበት፤ ካልማሰበት የውሃ ምንጭ የሚጠጣበት ጊዜ ነው። ልባቸው በፍቅር የተለከፉ ፍቅረኞችም የቅርብና የሩቁን አጣርተው ማየት ስለማይችሉ በልባቸው በተቀጣጠለው የጋራ እሳት የተነሳ ነገርን ሳያመዛዝኑ ተጣምረው ትላንት ያስተቃቀፋቸው የፍቅር እሳት ዛሬ የሚያቃጥላቸው አእላፍ ናቸው።
በቅርብ ቀን አንድ የፈረንጅ የስራ ባልደረባዬ አንዲት መልከ-መልካም የሆነችና የተማረች ሃበሻ ለትዳር ይጠይቃል፡፡ ትውውቃቸው የቆዬ በመሆኑ እሺ እንድምትለው ልቡ ነግሮታል። የመጠየቂያው ቀን ደረሰና በሃገሩ ባህል መሰረት ቀለበት ገዝቶ ወደ አስራ-አምስት በምንሆን ሰዎች ፊት በአንድ ጉልበቱ በመበርከክ ለጋብቻ ይጠይቃታል። በደስታ ልብዋ የፈነጠዘው ሃበሻም እሺ ካለች በህዋላ እናቱ ለረጅም ጊዜ እንደተለይችው ህፃን አንገቱ ላይ ተጠመጠመችበት። እኔም በልቤ የምችለው ስጠኝ ፈጣርዬ አሁን አይኔ የሚያየውን ትርኢት በእኔ ላይ ቢደርስ ወገቤ ተሰብሮ በምርኩዝ እንደምሄድ እርግጠኛ ነኝ። የተጠረበ የቤት ምሰሶ አጠና የሚመስለው ነጩ የስራ ባልደረባዬ ያለምንም ችግር በአየር ላይ ተሸክሞአት መሳሳም ጀመሩ እኛም ጭብጨባውን አቀለጥነው።
ወደ ማታ ላይ ሰልኬ ሰለጠራ አንስቼ ሃሎ አልኩ። አንተ አደፍርስ አለ የሴት ድምፅ – አቤት ማን ልበል? አንተ ደግሞ የዞረብህ ጥዋት ሰውን አይተህ ማታ የምትረሳ በማለት በነገር ጎሽም አረገቺኝና ሄለን ነኝ ቁመሃል ወይስ ምን እየሰራህ ነው አለች። እኔም አዎ ቆሜ ነው የማውራሽ ልሩጥ እንዴ ስላት የስላቅ ሳቅ በመሳቅ በትእዛዝ መልክ ቁጭ በል ከአንተ ምክር እፈልጋለሁ አለች። እኔም መልካም አልኩና ከጎኔ ካለው ሶፋ ላይ ሰው ገፍትሮ እንደጣለኝ ዘው አልኩበት።
ሰማ አደፍርስ ከጋብቻ በፊት ውል (ፕሪናፕ) ጉዳይ ታውቃለህ? ብዙም ባይሆን አዎን አልኩ። ባጭሩ አንቺም ሆነ እርሱ ከጋብቻ በፊት ያጠራቀማቹህትን ሃብት እንዲሁም የዕዳ ክምር ለራስ የሚያደርግ ነው አልኳት። እንደፈላስፎች ቃላት ታበዛለህ። በሚገባኝ መልክ አስረዳኝ እንደገና አለችኝ። እኔም አማርኛ ነበር እኮ የምናገረው በማለት እንደገና ላብራራላት ሞከርኩ። እሱም ሆነ አንቺ ከጋብቻ በፊት ያላቹህ ንብረትና ዕዳ የየግል የሚያደርግ ውል ነው። እንደ ውሉ አይነት ጥብቀቱና መላላቱ ይለያያል። አሃ አሁን ገባኝ። ፕሪናፕ እናርግ አለኝ እኮ። ታዲያ ምን ችግር አለው ጠበቃ ፈልጉና ከአምስት መቶ እስከ ሁለት ሺ ዶላር ሊፈጅ ይችላል መፍጸም ነው ስላት። ከሁለቱም በኩል እንደተለኮሰ ሻማ በፍጥነት መቀጣጠል ጀመረች። አንተ እኮ እነርሱን ሆነሃል። አቅፎኝ እያደረ እንዴት ሃብቱን ንብረቱን ከእኔ ይደብቃል። መደብቅ እኮ አይደለም። ያማ ቢሆን ፕሪናፕ እናርግ አይልሽም ነበር። ያለኝና የሚኖርኝ (ውርስንም ይጨምራል) ሃብት ይህ ነው። እዳዬንም እወቂው ማለቱ መደበቅን አያመለክትም። ይህ የፕሪናፕ ውልም በሃውልት ላይ የተጻፊ አይደለም ሊቀየር ይችላል አልኳት።
እንደምታውቂው ጊዜ ወዳጅም ጠላትም ነውና ልጅ ሲመጣ ፍቅር ሲደረጅ ዛሬ እንደምታስቡት አንቺም ሆነ እርሱ አታስቡም ሲላት ነገሬ ያልተዋጠላት ሄለን እንደዚህ አይነት ትዳርና ህይወት አልፈልግም በፕሪናፕም አላምንም አለች። ልጅን ሲወድ ከእነንፍጡ ነው አለች። አንቺ ደግሞ እርሱ ቀርቶ ሌላ ዘፈን መጥቶ ይልቅስ ጊዜ ወስደሽ ረጋ ብለሽ አስቢበት በእኔም አመለካከት መልካም ጅመራ ነው አልኳት። ምክሬ ያልጣፈጣት ሄለንም አመሰግናለሁ እኔ ግን አላረገውም በማለት ስልኩን ዘጋችው።
ስልኩን ከዘጋችው በህዋላ ብቻዬን ስለጉዳዬ ማሰብ ጀመርኩ። ዘመናችን ቁሳዊው ዓለም የሰውን ዓይን ያወረበት፤ የሰው ልጅ የማንነቱ መለኪያና መታውቂያ የሚነዳው መኪና እንጂ ስሙ ያልሆነበት ጊዜ ደርሰናል። አብለጭላጩ አለምም ረሱን እያሳየ የድብብቆሽ ጫዋታ ስለሚጫወትብን እንደምንሻው መስተናገድ አልቻልንም። ትርፍ ፍለጋ ስንባዝን በእጃችን የያዝነውን ጥለን ዛሬ ስንቶች ነን ያለፈው ህይወታችን የሚቆጨን? ይሆናል ብለን የጀመርነው ፈራርሶ ራቁታችን ያስቀረን? ሰው ትዳር ሲመሰርት ባይሳካ የመውጫ ብልሃት ማቀድ ወንጀል አይደለም። ስንቶች ናቸው ሞትኩልህ ሞትኩልሽ ብለው ሜዳ ላይ ጠለውን የጠፉ? ቤቱ ይቁጠረው። ለጥቅም ተብሎ የሚመሰረት ትዳር ፍጻሜው አያምርም። ሰው ደግሞ የፕሪናፕ ውል መጠየቁ መልካምነት እንጂ ክፋት የለውም። ዋናው ነገር አብሮ መኖር ሲጀመር የሚታየው መተጋገዝና መዋደድ የአሁኑና ሊመጣ ያለውን የትዳር ዘመን ውህደት ጠቋሚ ይሆናል።
የሄለንን ሁኔት ሳስብ አንድ ዘፈን ትዝ አለኝ። የዘፈኑ ግጥም እንዲህ ይላል
ለትርፍ ነው እንጂ ጎራውን መዞሬ
ለማሳ ማሳማ ምን አለኝ ሃገሬ
ለዛሬው ይብቃኝ።
ቸር ይግጠመን
አደፍርስ ተሰማ