የሸረሪት ፍቅር – ወርቁ ለገሠ

Black widow spider

መቼም እዚህ አሜሪካ የማይሰማ ጉድ የለም። Black Widow የተባለች የሸረሪት ዝርያ ከፍቅረኛዋ ጋር ያላት ግንኙነት ፍቅር ባፍንጫዬ ይውጣ የሚያሰኝ ነው።

ተክለ ሰውነቱ እንከን ባይወጣለትም ከሴቷ ጋር ሲነጻጸር ወንዱ ሸረሪት አነስተኛ ነው። ሴቷ በፍቅር እንድትደራ ከተፈለገ  ወንዱ ሳይታክት የረቀቀና የተራዘመ ልመና ማድረግ ይጠበቅበታል። ወገብ የሚቆርጠው ልምምጥ ተደርጎም ለአፍቃሪነቱ በጎ ምላሽ  ሳይሰጠው ልቡ በሃዘን ተሰብሮ የሚሄድበት ሁኔታም አለ። ልመናው ፍሬ ሲሰጥ፣ የግሪኩ የፍቅር አምላክ ሲታደገው “እሺ ቤቴ ቤትህ ነው” ብላ በጥበብ አድርታ ከሰራችው የሸረሪት አፓርታማ እንድገባ ትፈቅድለትና የመኝታ ክፍሉን ቁልፍ ትሰጠዋለች። እሱም ጊዜ ሳያጠፋ ይገባና በቋንቋቸው “እወድሻለሁ ፍቅርዬ” ብሎ ከንፈሯን ምጥጥ አድርጎ በመሳም በ16 እግሮቻቸው ተቃቅፈው በፍቅር ባህር ይሰጥማሉ።

መቼም ፍቅር ሲያልቅ አያምርም ሁለቱ ፍቅረኛሞች ከገቡበት የፍቅር ሰመመን እንደተመለሱ ሴቷ ሸረሪት ክፉኛ ስለምትራብ “ፍቅርዬ የሚበላ ይዘሃል?” የሚል ጥያቄ ሲቀርብ ወንድ አፋጣኝ መልስ መስጠት ይጠበቅበታል። በፍቅር የታወረው ሸረሪት ከቤቱ ሲወጣ ቤሳ እንደሌለው ትዝ ሲለው ይርበተበታል። ዝም፣ ጭጭ፣ እርጭ ይላል ቤቱ። ሴት መላ አታጣም አይደል፡

 ወንድ ሲርበተበት አይገባንም እኛ

መራብ የለባትም የሴት ልጅ ፍቅረኛ

የሚለውን ስንኝ ትቋጥርና እንደጦር የሰላ መውጊያዋን ሆዱ ላይ በመትከል ከሰውነቱ ጭማቂ መምጠጥ ትጀምራለች። ዘራፍ ብሎ የመከላከል ዕርምጃ እንዳይወስድ በመጠኑ ከሴቷ አንሶ የተሰራ ፍጡር ነው። ሌላው ደግሞ የሸረሪት ድሩ እግሮቹን ተብትቦ ይይዛቸዋል።፡ በደመነፍስ ፍቅር የሠራበት የሸረሪት አፓርትመንት ውስጥ እግሮቹን በማወራጨት የተፈጸመበትን ግፍ ላለመቀበል ይሞክራል። ሴቷ ሸረሪት ግን “ምነው ፍቅሩዬ ጨለምተኛ ለምን ትሆናለህ? ያሳለፍናቸውን የፍቅር ሰዓታት አስታውስ እንጅ። ለሰጠሁህ ፍቅር የጠየኩትን ዋጋ በጸጋ ተቀበለው። አይዞህ!” እያለች እስከመጨረሻው ህቅታ ደሙን በመምጠጥ ለህልፈት ትዳርገዋለች። ምን ይሆናል ከፍቅር ሰመመን እንደነቃ ሱሪውን ታጥቆ ከጎኗ ፈትለክ ቢል ኖሮ ህይዎቱን ያተርፍና እንደገና ለማፍቀር ዕድል ያገኝ ነበር።

ውድ አንባቢያን- ሸረሪቷ በሰራችው ግፍ ከመገረማችሁ በፊት ይህ አጉል ጠባይ በታላቁ ፍጡር በሰው ይንጸባረቅ ይሆን ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት አንድ የቤልጅግ ፕሮፌሰር በግል ቤታቸው አዲስ የተጋቡ ሙሽሮችን እየጋበዙ ለረጅም ዓመታት ተከታትሏቸዋል። በጥናቱ መሠረት ሴት ሙሽሮቹ ወንዱ ላይ የሚያሳዩት የአሳሳም ዘይቤና መጠን ሸረሪቷ እንደወሰደችው ዕርምጃ ለሞት የሚዳርግ አይሁን እንጅ ሁኔታው በቅርብ እንደሚመሳሰል አስምሮበታል።  ፍቅር እስከ መቃብር ይሏል ይህ ነው።

ቸር ይግጠመን

ወርቁ ለገሠ (11/01/10)