ለካ እንዲህ ይከብዳል – በወርቁ ለገሰ

አልጋ ላይ ሞከረ ምንም አልተመቸው
ሶፋ ላይ ሞከረ ምንም አልተመቸው
መሬት ላይ ሁኝ አለኝ እሱም አልተመቸው
ውጭ እንውጣ አለኝ ወጣሁ ተቻኩዬ
በአበቦቹ መሃል ዛፉን ደገፍ ብዬ
አንዴ ተንበርክኮ አንድ ጊዜ ቆሞ
ወደ ታች ወደ ላይ ወደጎንም ዘሞ
እሱም አላረካው ወደቤት መለሰኝ
አኳኋኑ አሳቀው እኔንም አሳቀኝ
አልጋ ላይ ውጭ አለኝ እኔም ወጣሁለት
ከፍ በይ ዝቅ በይ ሁሉንም ሆንኩለት
መስኮትጋ በሩ ሥር አንዴ ከግድግዳ
ምግብ ቤት ሳሎን ቤት መኝታ ቤት ጓዳ
እቤት ውስጥ በመብራት ውጭ በጸሐይ
ከግራ ወደ ቀኝ ወደ ታች ወደ ላይ
አኳኋኑ ሁሉ በሳቅ ያፈነዳል
ውብ ፎቶ ለማንሳት ለክ እንዲህ ይከብዳል።
Source: Anonymous