አሻራ – በወርቁ ለገሠ

በዘመን ወይቦ ቀለሙ ባይደምቅም

አሻራ ህያው ነው ቢፍቁት አይለቅም

ዜግነት ቢቀየር ቢገቡ አሜሪካ

ከየት ነህ? መባሉ የማይቀር ነው ለካ!

ክልል ድንበር ሆኖ ቢከፈል አገሬ

ወሎዬ፣ ከፍቾ ሾዌና ጎንደሬ  

ቋንቋ መሥፈርት ሆኖ ሰውን ቢፈርጁት

አማራ፤ ኦሮሞ አኟክ ትግሬ ቢሉት

ደሙ ሲመረመር እምዬ አብሲኒያ

አሻራው ሲነሳ ሃገረ ኢትዮጵያ

መሆኑ አይሻርም ሲኖር በዚች ዓለም

በትውልድ ጸንቶ ይኖራል ዘላለም

በአንቺ ሆዬ ለኔ በባቲ ትዝታ

በአምባሰል ቅኝቶች ለዛና  ጨዋታ

ጊዜ ሳይወስነው ሳይገታው ርቀት

ይነጉዳል አበሻ ይጓዛል አገር ቤት

ቢሳካ ለመኖር ካልሆነም ለቀብሩ

እንደወጣ አይቀርም ይገባል አገሩ

 እንደናት እንዳባት የጣት አሻራችን

ሊለወጥ አይችልም አበሻነታችን

በዘመን ወይቦ ቀለሙ ባይደምቅም

አሻራ ህያው ነው ቢፍቁት አይለቅም

ዜግነት ቢቀየር ቢገቡ አሜሪካ

ከዬት ነህ? መባሉ የማይቀር ነው ለካ!

 በወርቁ ለገሠ (10/17/10)