የወያኔ ካድሬዎች የ«በቃ!»ን መፈክር ለማጥፋት እየተሯሯጡ ነው
በኢትዮጵያ ውስጥ ለ20 አመታት የዘለቀውን የወያኔ/ኢህአዴግን አገዛዝ በመቃወም “በቃ” በሚል መሪ ቃል በቱኒዚያ፣ በግብጽና በሌሎችም ሀገራት እንደተከሰተው አይነት ህዝባዊ አመጽ አካሂዶ ኢትዮጵያንም ነጻ ለማውጣት እንቅስቃሴ መጀመሩ ይታወቃል፡፡ ይህን እንቅስቃሴ ተከትሎ ስለ ንቅናቄው መራ የሚሰጡ በራሪ ወረቀቶችን በስፋት ከመበተን ባሻገር በመዲናዋ አዲስ አበባና በሌሎችም ከተሞች አደባባይ ላይ ህዝብ በብዛት በሚሰበሰብባቸው ስፍራዎች ላይ “በቃ” የተሰኘው መሪ ቃል በቀይ ቀለም ተጽፎ ይታይ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በማስቀየሻ ስልቶችና በማስፈራራት ህዝባዊ አመጹን ለማምከን ያልተሳካ ሙከራ ሲያደርግ የቆየው የወያኔ/ኢህአዴግ አገዛዝ አሁን ደግሞ ካድሬዎቹን በማሰማራት በሀገሪቱ ዋና ዋና ቦታዎች ላይ የተጻፉትን የበቃን መፈክሮች በመሰረዝ ላይ ነው፡፡
ከአዲስ አበባ ወደተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች ሲሄዱ የትራንስፖርት አገልግሎት ለማግኘት፣ ከተለያዩ ከተሞች ወደ አዲስ አበባ ሲገቡ ደግሞ ጉዞአቸውን የሚጨርሱት ስፍራ በመሆኗ በርካታ ሰዎች በየቀኑ በሚጎበኟት አውቶቢስ ተራ አካባቢ ከቀናት በፊት የበቃ መፈክሮች አጥለቅልቀውት ነበር፡፡ ዛሬ ግን በዛው አካባቢ በተለይ ሚጣቅ ሆቴል ፊትለፊት በሚገኘው የአውቶቢስ ተራ ዋና አደባባይ ላይ ተጽፎ የነበረውን የበቃ መፈክር የወያኔ/ኢህአዴግ ካድሬዎች በነጭ ቀለም አጥፍተውታል፡፡
ይህን የታዘበው ሪፖርተራችን የዚህ ተግባር ትርጓሜ ምን ሊሆን ይችላል የሚል ጥያቄ ለአንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር ጥያቄ አቅርቦላቸው ነበር፡፡ (ለደህንነት ሲባል ስማቸው አልተገለጸም) የሰጡት መልስም “ኢህአዴግ ስራውን በሚገባ ስለሚያውቅ የወቅቱ ህዝባዊ አመጽ በኢትዮጵያ ሊከሰት ይችላል በሚል በከፍተኛ ስጋት ውስጥ እየተናጠ ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ የሰሞኑ ተግባራቱ ሁሉ የሚያመላክቱት የፍርሀቱ መጠን ገደብ እንዳለፈ ነው፡፡ አሁንም ይሄንን መፈክር ስለሰረዘ ህዝባዊ አመጹ ሊሰረዝ አይችልም፡፡ ይልቁንም የእንቅስቃሴውን ግዝፈትና ህዝባዊነት የሚያሳይ ነው፡፡” የሚል ነው፡፡ በመጨረሻም “ኢህአዴግ በጓደኞቹ ላይ ከደረሰው ውርደት የሚያመልጠው ከዚህ ሁሉ መደናበርና መሸበር ይልቅ ህዝብ እንደማይፈልገው አውቆ ስልጣኑን በጊዜ ለህዝቡ ሲያስረክብ ብቻ ነው” በማለት መክረዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ አደባባይ ላይ የነበሩት የ«በቃ» መፈክሮች እየተሰረዙ መሆኑን ተከትሎ ብዙ ሰው በሚያየውና ከኢህአዴግ ደህንነቶች በቀላሉ ሊገኝ በማይችልበት እንደ መጸዳጃ ቤት ያሉ ሰዋራ ስፍራዎች ላይ መፈክሮቹ እየተጻፉ ይገኛሉ፡፡ ሪፖርተራችን ስፍራው ድረስ ሄዶ እንዳረጋገጠው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲት 6 ኪሎ ካምፓስ በበርካታ የመማሪያ ክፍሎች ግድግዳ ላይ መፈክሮቹ ተጽፈዋል፡፡