“አቶ መለስ ስለደነፉ የሚቀነስም ሆነ የሚጨመር ነገር የለንም” – አንዱአለም አራጌ

በሰሜን አፍሪካ ተጀምሮ በርካታ አምባገነን መንግስታትን በማስደንበር ላይ ያለው ህዝባዊ አመጽ በኢትዮጵያም ሊከሰት ይችላል በሚል ግምት የኢህአዴግ ባለስልጣናት በርካታ እርምጃዎችን ሲወስዱ ቆይተዋል፡፡

የመጀመሪያውና ውጤት አልባ የሆነው የማስቀየሻ ስልት “በመሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች” ላይ የተደረገው የዋጋ ተመን ሲሆን የኤርትራን መንግስት በጦርነት ከስልጣን እናወርዳለን፣ አባይን ገድበን የሃይል ማመንጫ እንገነባለን፣ የቴሌ የዋጋ ታሪፍ ቀንሰናል የሚሉ ትልልቅ ርዕሰ ጉዳዮችን በሚዲያ በሰፊው በመንዛት የህዝቡን የትኩረት አቅጣጫ ለማስለወጥ ቢሞክርም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

እነዚህን በመሣሠሉ የማስቀየሻ ስልቶች በሀገሪቱ ሊከሰት ይችላል ተብሎ የሚገመተውን ህዝባዊ አመጽ ለማክሸፍ የማይቻል መሆኑን የተገነዘበው ኢህአዴግ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን በተለይም የመድረክ አባላትን ለእስር ዳርጓቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ የሚዲያው ፕሮፓጋንዳ፣ የማስቀየሻ ስልቶቹና የእስር እርምጃዎቹ ህዝባዊ አመፁን ከመፍራቱ ጋር ስለ መያያዙ በግልጽ ሲናገር አልተደመጠም፡፡

ጠ/ሚሩ መጋቢት 27፣ 2003 ዓ.ም በፓርላማ ተገኝተው የተናገሩት ግን ሁሉንም አንቅስቃሴዎች በግልጽ ያመላከተ ነው፡፡ ከንግግራቸው ጋር ተያያዥነት በሌለው ሁኔታ ‹‹የመድረክ አባላትን በተለይ አንድነት ፓርቲን ማስጠንቀቅ እፈልጋለሁ። የኢትዮጵያ መንግስት ማየትና መስማት የተሳነው መንግስት አይደለም… አመጽ የምታስነሱ ከሆነ ዋጋ ትከፍሉበታላችሁ›› በማለት በመድረክ አባላት በተለይም በአንድነት ፓርቲ ላይ ማስፈራሪያና ዛቻ ሰንዝረዋል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች አባላት በሙሉ የአሸባሪ ድርጅቶች አባላት ናቸው ለማለት “የኦነግንና የሌሎቹን አሸባሪ ድርጅቶች አባል የሆኑትን ሰዎች ሁሉ ብናስር በተቃዋሚዎች መንደር ጭር የሚል ነገር ይጠራል” ሊሉ ገልፀዋል፡፡

የንግግራቸውን ትርጉም ከድርጅታቸው የ20 አመታት ተግባሮች መረዳት እንደሚቻለው ይህ ማስፈራሪያቸው አይቀሬ ነው የሚባለው ህዝባዊ አመጽ በኢትዮጵያም ቢነሣ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ላይ የከፋ እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጃታቸውን የሚያሳይ እንደሆነ በርካቶች እየተናገሩ ነው፡፡

በአንድነት ፓርቲ ላይ የተሰነዘረውን ዛቻ አስመልክቶ ያነጋገርናቸው የፓርቲው ዋና ፀሐፊ አቶ አንዷለም አራጌ እንደገለፁት ‹‹ሰውየው ፍርሃት ውስጥ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ንግግራቸውም የሚያሳየው ከዚህ በፊት የሚሄዱበትን የተለመደ መንገድ ለመተግበር እንደተዘጋጁ ነው›› ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ተግባር ጠቃሚ አለመሆኑን ‹‹የፈለጉትን ማድረግ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በእኛ ላይ የሚወስዱት እርምጃ ከችግር አያድናቸውም፡፡ ጥያቄው የህዝብ ሆኖ ሳለ የተቃዋሚዎች አጀንዳ ለማድረግ ከመሞከር ይልቅ ራሳቸውን ገምግመው ለመታረም ቢሞክሩ የተሻለ መፍትሄ ነው፡፡›› ሲሉ መክረዋል፡፡

አንድነት ፓርቲ ላይ በተለየ ሁኔታ ዛቻ የተሰነዘረበትን ምክንያት አቶ አንዱአለም ሲያስረዱ፡፡ ‹‹አንድነት በአሁኑ ወቅት እያደገና ስር እየሰደደ ያለ ፓርቲ ነው፡፡ የ5 አመት ስትራቴጂክ እቅድ አዘጋጅተን በሰፊው እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ በዚህ ሳቢያ እያገኘን ያለነው የህዝብ ተቀባይነት አስፈርቷቸው ሊሆን ይችላል፡፡›› ብለዋል፡፡

አቶ አንዱአለም ከሶስት አመት በፊት በኢህአዴግ የስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ላይ ‹‹ተቃዋሚዎች እግር እስኪያወጡ እንጠብቃለን እግር ሲያወጡ እንቆርጣለን፡፡›› መባሉን እንደሰሙ ገልፀው ‹‹አሁንም እሳቸው የሚፈልጉት ብቻቸውን የሚናገሩበት፤ ብቻቸውን የሚገዙባትና በፍፁም ጨለማ የተዋጠች ኢትየጵያን መፍጠር ስለሆነ የእኛን መጠናከር አይፈልጉትም፡፡ ይሁን እንጂ አቶ መለስ ስለደነፉ የሚጨመርም ሆነ የሚቀነስ ነገር የለንም፡፡ በእቅዳችን መሠረት ስራችንን እንሰራለን፡፡›› በማለት አስተያየታቸውን አጠቃለዋል፡፡