ወያኔ የቦንድ ሽያጩን በካድሬዎቹ አማካኝነት እያጧጧፈዉ ነዉ
ወያኔ/ኢህአዲግ ታላቁ «የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ»ን ለመገንባት በሚል እያካሄደ ያለዉ የቦንድ ሽያጭ የዜጎችን ሙሉ ፍላጎትና ተሳትፎ የያዘ ለማስመሰል በካድሬዎቹ አማካኘነት የተለያዩ ዘዴዎችን እየተጠቀመ መሆኑ ታወቀ።
ጉዳዩን አስመልክቶ አስተያየታቸዉን የሰጡን በመንግስት መስርያቤቶች የሚሰሩ ሰራተኞች እንዳስታወቁት በየመስርያቤቱ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ለመነጋገር በሚል ሰራተኞች እንዲሰበሰቡ ከተደረገ በኋላ በአለቆቻቸዉ አማካኝነት አባይን ኢትዮጵያ ለዘመናት ሳትጠቀምበት መቆየቷንና አሁን ግን ይህ ሁኔታ ቀርቶ በአባይ አማካኝነት ድህነት ተረት የሚሆንበት ዘመን ላይ እንደተደረሰ ይተረካል፡፡ ከዚያም አመራሮቹ “በዚህ ታሪካዊ አጋጣሚ ላይ የኛ ሚና መሆን ያለበትን ብንነጋገር” የሚል ተመሳሳይ ጥያቄዎችን ያቀርባሉ፡፡ ጥያቄዉን ተከትሎ ሁለት ሶስት የሚሆኑ ካድሬዎች እጃቸዉን በማዉጣት የወር ደመወዛቸዉን በአመት ለመስጠት እንደወሰኑና በተጨማሪም ከቤተሰብ አባላቸዉ በተወሰኑት ወይም በሁሉም ቁጥር ልክ ቦንድ እንደሚገዙ ይገልጻሉ፡፡ ከእነሱ በመቀጠል የካድሬዎቹ ተልዕኮ ያልገባቸዉና በሰዎቹ ንግግር ስሜታቸዉ የተነካ ሰራተኞች ለሀገራቸዉ አንዳች በማበርከት ፍላጎት ተሞልተዉ ከእነሱ በፊት አስተያየት በሰጡት ሰዎች ሃሳብ እንደሚስማሙ ያስታዉቃሉ፡፡ በመጨረሻም ሀሳቡ የሁሉም ሰራተኞች እንደሆነ ተደርጎ የአቋም መግለጫ ይወጣና በጭብጨባ ይጸድቃል፡፡
ከላይ የተዘረዘረዉን የገዢዉን ፓርቲ ብልጠት የተሞላበት አካሄድ ያስረዱን ሰራተኞች አንዳንድ ሰራተኞች በቦንድ ግዢ ላይ ግንባር ቀደም በመሆን ከዚህበፊት የተጣለባቸዉን ጥቁር ነጥብ ለመፋቅ እየተሯሯጡ መሆኑንና ግማሾቹ ደግሞ የስራ ዋስትናቸዉን አደጋ ላይ ላለመጣል በመስጋት ቦንዱን በመግዛት ላይ መሆናቸዉን ገልጸዉልናል፡፡ ገዢዉ ፓርቲ በዚህ አይነት መንገድ እየተጠቀመ የቦንዱን ሽያጭ ያጧጧፈዉ ደሞዝ ከሚከፈላቸዉ ሰራተኞች ላይ ብቻ ሳይሆን ከአጸደህጻናት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ድረስ ያሉ ተማሪዎች ላይ ጭምር መሆኑም ታዉቋል፡፡ በመሆኑም በየመስርያቤቶቻቸዉ ገንዘብ ያዋጡ ሰራተኞች ለልጆቻቸዉም እንዲያዋጡ እየተገደዱ በመሆናቸዉ ቅሬታ በማሰማት ላይ ይገኛሉ፡፡ ተማሪዎቹ በየክፍላቸዉ እንደየት/ቤቱ ሁኔታ የተለያዪ የገንዘብ መጠን ያላቸዉ ቦንዶች እንዲገዙ በመደረጉ ቅሬታ እንደተሰማት የገለጸችልን አንዲት ወላጅ “ይህ አመት ሲያልቅ ተማሪዎቹ ይበታተናሉ፡፡ ይህ እየታወቀ ከአምስት አመት በኋላ የሚመለስ ገንዘብ አዋጡ ማለት ያስገርማል፡፡” ብላለች፡፡
ወላጆች በድርጊቱ ቢማረሩም ወያኔ ግን ቀጥሎበት የመንግስት ት/ቤት ለሚማሩ ተማሪዎች በፕላዝማ አማካኝነት ስለግድቡ የተብራራላችዉ ሲሆን የክፍልሀላፊ መምህራኖቻቸዉም ተጨማሪ ማብራርያ እንዲሰጡበት ተደርጓል፡፡ ሆኖም ተቋዋሚ መሆናቸዉ የሚታወቅ የከፍል ሀላፊ መምህራን ተማሪዎቹን እንዳያወያዩ የተደረገ ሲሆን ታማኝነታቸዉ ጥያቄ ምልክት ዉስጥ የወደቀ የክፍል ሀላፊ መምህራንም ብቻቸዉን ተማሪዎቹን እንዳያወያዩ ስለተፈለገ ከገዢዉ ፓርቲ ተአማኒነትን ያገኙ መምህራን አብረዋቸዉ ሆነዉ የመቆጣጠር ስራ አከናዉነዋል፡፡ ገዢዉ ፓርቲ ሊመጣ ያለዉን አመጽ በመፍራት አቅጣጫ ለማሳት ያመጣዉ እንደሆን እየተነገረለት ያለዉ አባይን የመገደብ አጀንዳ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተነቃበት በመምጣቱ ቦንዱን ላለመግዛት የሚያንገራግሩ ሰራተኞች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱም ታዉቋል፡፡ የቦንድ ግዢን በተመለከተ በተደረገ ስብሰባ ላይ በግልጽ ቦንድ እንደማይገዙ ካስታወቁ ሰራተኞች መሀል የኢትዮጵያ የደህንነት መረብ ኤጀንሲ ሰራተኞች ይጠቀሳሉ፡፡