የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ነጋዴውንና ሸማቹን እያማረረ ነው
ከትላንት በስቲያ በአንድ ወር ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በነዳጅ ዋጋ ላይ የተደረገው ጭማሪ በተለይም የምግብ ሸቀጦች ዋጋ ከፍ እንዲል በማድረጉ ነጋዴዎችን ሸማቾች እየተማረሩ ነው፡፡
የዋጋ ማስተካከያው በአንድ ሊትር ቤንዚን ላይ አራት ብር ገደማ የጨመረ መሆኑን ተከትሎ የከተማ ታክሲና አውቶቢሶችም ከዚህ በፊት የነዳጅ ዋጋ ሲጨምር ከነበረው የትራንስፖርት ታሪፍ ማስተካከያ እጥፍ በሆነ ሁኔታ እስከ ሰማንያ ሳንቲም የሚደርስ ጭማሪ አድርገዋል፡፡ በዚህ ሳቢያ በአንዳንድ ሸቀጦች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ንረት የተስተዋለ ሲሆን መንግስት ተመን ያወጣላቸው አንዳንድ ምርቶች ደግሞ ከገበያ ጠፍተዋል፡፡
ፒያሳ አካባቢ በሚገኘው አትክልት ተራ ተዘዋውረን እንደ ተመለከትነው እንደ ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ድንችና ካሮት በመሳሰሉት ምርቶች ላይ በአንድ ኪሎ ከዘጠና ሳንቲም አስከ ሶስት ብር ከሃያ አምስት ሳንቲም የሚደርስ ጭማሪ አሳይተዋል፡፡ ሌሎች ምርቶችም ላይ ተመሳሳይ ሁኔታዎች የሚታዩ ሲሆን መንግስት ተመን ያወጣላቸው እንደ ሳሙናና ሻይ ቅጠል የመሳሰሉት ሸቀጦች ደግሞ ከሱቅ መደርደሪያዎች ላይ እየጠፉ መሆናቸውን ለመታዘብ ችለናል፡፡
በአራት ኪሎ አካባቢ ያለን አንድ ባለሱቅ እነዚህን ምርቶች ለምን እንደማይዛቸው ጠይቀነው “መንግስት በአንድ ሳሙና አስር ሳንቲም ብቻ በአንድ ፓኬት ሻይ ቅጠል አምስት ሳንቲም ብቻ እንድናተርፍ ወስኖብናል፡፡ ለምሳሌ ሃምሳ ፍሬ የሚይዝ አንድ ካርቶን ሳሙና መርካቶ ሄጄ ሳመጣ ለራሴ ብቻ ስሄድ 2 ብር ከስልሳ ሳንቲም ስመለስ 2 ብር ከስልሳ ሳንቲም ከፍላለሁ ለሳሙናው አንድ ብር ከሃምሳ ብከፍል በጠቅላላ ወደ ሰባት ብር አወጣለሁ፡፡ እኔ ግን ሃምሳ ሳሙና ቸርችሬ የማገኘው አምስት ብር ብቻ ነው፡፡ ቤት ክራይና ሌሎች ወጪዎችም አሉብኝ፡፡ ታዲያ የሚያከስረኝን ዕቃ ለምን እይዛለሁ;” የሚል ምላሽ ሰጥቶናል፡፡
በዚሁ ጉዳይ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ከተጠየቁ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መሀከል የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው ያማረራቸው አንድ አዛውንትም እንዲሁ ጉዳዩ አሳሳቢ መሆኑን ገልጸው “መንግስት አባይን ከሚገድብልን የነዳጁን ዋጋ ቢገድብልን ይሻለን ነበር” በሚል ሽሙጥ ሀሳባቸውን ገልጸውልናል