የቲያትር ድርሰት እጥረት በኢትዮጵያ ውስጥ እየተከሰተ ነው

ትላንት ጠዋት በሀገር ፍቅር ቲአትር “የድርሰት እጥረት በቲያትር ቤቶች” በሚል ርዕስ የቲያትር ፀሐፍት፣ ተዋንያን፣ አዘጋጆችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ውይይት አደረጉ፡፡

ውይይቱ የድርሰት እጥረትን የተመለከተ ጥናት አድርጎ የመፍትሄ ሃሳብ ያቀርባል ለተባለለት ጥናት አጋዥ የሚሆኑ ግብዓተ ሀሳቦችን ከቲያትር ባለሙያዎች ለማግኘት ታስቦ የተደረገ መሆኑ ተነግሮለታል፡፡ ውይይቱን የመሩት የቲያትር ባለሙያዎች ህይወት አራጌ፣ ኃይለማርያም ሰይፉ እና አንጋፋው የቲያትር ደራሲ ተስፋዬ አበበ ናቸው፡፡

በውይይቱ ላይ ለቲያትር ድርሰት መጥፋት በምክንያትነት ከቀረቡት መሐል የቲያትር ገምጋሚዎች በሙስና መዘፈቅ፣ የብቃት ማነስና ቲያትር ቤቶች ለደራሲዎች ቁርጥ ክፍያ አለመክፈላቸው ይገኙበታል፡፡

አሁን አሁን ደግሞ ቲያትር ቤቶች በመንግስት አስገዳችነት የቲያትር ፀሐፊዎች ሊፅፉባቸው የሚገባቸውን ርዕሰ ጉዳዮች የተወሰኑ ማድረጋቸው የቲያትር ድርሰት እጥረቱን ይበልጥ እንዳባባሰው ተነግሯል፡፡

እውቁ የቲያትር ደራሲ ተዋናይና አዘጋጅ አለማየሁ ታደሰ በስብሰባው ወቅት “የቲያትር ድርሰት እንዲቀርብ የሚነገሩ ማስታወቂያዎች መልካም አስተዳደርን፣ ሴቶች ከወንዶች እኩል መሆናቸውን እንዲሁም ሀገራችን ያለችበትን የእድገት ጎዳና ጠቆም አድርጎ የሚያልፍ የሚሉ አይነቶች በመሆናቸው ለመፃፍ አያነሳሱም፡፡ የፈጠራ ነፃነትን ይገድባሉ” በማለት መንግስት እየተከተለ ያለውን የልማታዊ ቲያትር አካሄድ ጎጂ ጎን አሳይቷል፡፡ ከእሱ ቀጥሎ አስተያየቱን የሰጠው መላኩ የተባለው የቲያትር ባለሙያ “ፀሐፊዎች በሙሉ ልማታዊ ቲያትር እንዲፅፉ መፈለጉ የሚያሳየው በኮንቬንሽናል እና በልማታዊ ቲያትር መሀከል ያለውን ልዩነት አለመገንዘባቸውን ልማታዊ ቲያትር ለመድረስ የሚፈልገው የሕብረተሰብ ክፍል ድረስ ተሂዶ የሚሰራ ነው፡፡ ሰው እንዴት ገንዘቡን ከፍሎ ገብቶ እንዲህ አይነት ቲያትር ሊያይ ይችላል?” በማለት ከጠየቀ በኋላ በዚህ አይነት ከተቀጠለ የቲያትር ድርሰት እና ደራሲ እንደሚጠፉ ገልጿል፡፡

ከቲያትር ባለሙያው ቀጥላ አስተያየቷን የሰጠችው ተዋናይ፣ ተርጓሚና አዘጋጅ አዜብ ወርቁ ስትሆን “መንግስት ለተሰበሰብንበት ችግር መፍትሄ መስጠት ከፈለገ ታክስ መቀነስ ይኖርበታል” ብላለች፡፡ አርቲስት አዜብን ጨምሮ አብዛኛዎቹ አስተያየት ሰጪዎች መንግስት ታክስን በመቀነስ ባለሙያውን ካላበረታታ ፀሐፊው ስለኑሮው እየተጨነቀ መፃፍ ስለማይችል ብቃት ያላቸው የፈጠራ ስራዎች እንደማይኖሩ ገልፀዋል፡፡