ያለውጤት የተበተነው የሚኒስትሩና የቴሌ ሰራተኞች ስብሰባ
የኢንፎርሜሽንና ኮሚኒኬሽን ሚኒስትር አቶ ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል ትላንት ጠዋት በአምባሳደር ሲኒማ ካልተመደቡ የቴሌ ሰራተኞች ጋር ያደረጉት ስብሰባ ያለ ውጤት ተበተነ።

በዕለቱ በተደረገው ስብሰባ ላይ ከተጠበቀው በላይ ሰራተኞች በመገኘታቸው የአዳራሹ ወንበሮች ሞልተው ስብሰባውን ቆመው ለመከታተል የተገደዱ ሰዎች ቁጥር ከተቀመጡት እንደማይተናነስ የሰርካዲስ ምንጮች ገልፀዋል።
ምንጮቹ ይህ የሆነበት ምክንያት የስብሰባው አጀንዳ ላልተመደቡት ሰራተኞች የሞትና የሽረት ጉዳይ በመሆኑና ከአዲስ አበባ ውጪ የሚገኙ የቴሌ ሰራተኞች ባይጠሩም በስብሰባው በመገኘታቸው እንደሆነ ጨምረው ገልጸዋል። ስብሰባውን በንግግር የከፈቱት አቶ ደብረጽዮን በንግግራቸው መግቢያ የስብሰባው አላማ አዲሱ ኢትዮ–ቴሌኮም ስላካሄደው የሰራተኞች አመዳደብ ማብራሪያ መስጠት መሆኑን አስታውቀዋል። በመቀጠል አቶ ደብረ ጽዮን አመዳደቡ ችግር ያለበት መሆኑን እንደሚቀበሉ ከተናገሩ በኋላ ቅሬታ ያቀረቡ ሰራተኞች ጉዳያቸው እየተጣራ ተገቢ ሆኖ ሲገኝ ወደ አዲሱ ኢትዮ – ቴልኮም የሚገቡበት ሁኔታ እንደሚኖር አስረድተዋል።
አቶ ደብረጽዮን ያም ሆኖ ሁሉም ሰራተኞች በኢትዮ–ቴሌኮም ይታቀፋሉ ማለት እንዳልሆነ ካብራሩ በኋላ የማይመደቡ ሰራተኞች በኢንተርፕራይዞች እንደሚታቀፉ ገልጸዋል፡፡ ሚኒስትሩ በኢንተርፕራይዞች መታቀፍ የማይፈልጉ ሰራተኞች ደግሞ ካሳ እየተከፈላቸው እንደሚሰናበቱ አክለው ከገለፁ በኋላ ሰራተኞቹ ጥያቄዎች ካላቸው እንዲያቀርቡ ለቤቱ እድል ሰጥተዋል።
በዚህ ወቅት በርካታ እጆች የታዩ ሲሆን ከዛ ውስጥ 20 የሚሆኑት የመናገር እድል አግኝተው አስተያየታቸውን አቅርበዋል። ከነዚህ ተናጋሪዎች ውስጥ ከአንድ ወንድና ካንዲት ሴት በስተቀር ሌሎቹ በመሉ አመዳደቡን የተቃወሙ ሲሆን ደግፈው ሊናገሩ የሞከሩት 2 ግለሰቦች በተሰብሳቢው ጩኸት ንግግራቸውን ለማቋረጥ ተገደዋል፡፡ ሁሉም አስተያየት ሰጪዎች ንግግራቸውን ከመጀመራቸው አስቀድሞ ከዚህ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ ስማቸውንና መለያ ቁጥራቸውን ሲናገሩ ተስተውሏል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መሀል የዜና አገልግሎት ክፍላችን ያነጋገራቸው ሰራተኞች ይህን ያደረጉት ጉዳዩ ከትእግስታቸው በላይ በመሆኑ ከእንግዲህ ምንም ነገር እንደማይፈሩና እንደማይታገሱ ለመንግስት ለማስታወቅ በመፈለጋቸው መሆኑን ገልጸውልናል፡፡ ለስብሰባው አስተያየታቸውን ካቀረቡት መሀል አንዱ የሆነውና ከአዋሳ እንደመጣ የገለፀ ወጣት ሳይመደብ የቀረበትን ምክንያት “ሁሉም ጎሳውን እየመረጠ ሲመድብ እኔ የአዲስ አበባ ልጅ በመሆኔና አዲስ አበባ የሚባል ጎሳ ባለመኖሩ አየር ላይ ቀርቻለሁ፡፡” በማለት ገልፆታል፡፡
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ በበኩሉ ምደባው የትምህርት ደረጃ ታይቶ የተሰራ ነው እንዳይባል ይህን ለማለት የማያስችሉ ሁኔታዎች የሞሉበት መሆኑን በስራ ልምድ እንዳይባል ደግሞ በአብዛኛው የተመደቡት 19 ሺህ እና 20 ሺህ ቤት የመለያ ቁጥር ያላቸው አምናና ካቻምና የኢህአዴግን የአባልነት ፎርም እየሞሉ መስሪያ ቤቱን የተቀላቀሉ ሰራተኞች መሆናቸውን በመግለጽ በምደባው ላይ ትልቁን ሚና የተጫወተው የኢህአዴግ ካድሬ መሆን እንደነበር አስረድቷል። አንድ አስተያየት ሰጪ ደግሞ በአዲሱ ኢትዮ–ቴሌኮም የታቀፉ ሰራተኞች ወደ አዲሱ ቢሮአቸው ከገቡ በኋላ ያልተመደቡት ሰራተኞች እጣ ፈንታ ምን እንደሆነ ከመንግስት በኩል ሳይገለጽ በመቆየቱ እስከአሁን አንድ ሴትና ሁለት ወንድ ሰራተኞች ተስፋ በመቁረጥ ራሳቸውን እንዳጠፉ ገልፆ “ የተፈፀመብንን ይህንን ታላቅ ሴራ ለታሪክ እንተወዋለን “ በማለት ንግግሩን ቋጭቷል፡፡
በስብሰባው የቀረቡት የአብዛኞቹ ሰራተኞች አስተያየት በአንድ ሲጠቃለል አመዳደቡ የተሰራው በዘመድ አዝማድ፣ በጎሳና በኢህአዲግ አባልነት መሆኑን የሚገልጽ ነበር፡፡ ስብሰባው በእንዲህ አይነት ምሬት የተሞላባቸው አስተያየቶች ታጅቦ እስከ 5፡10 ከዘለቀ በኋላ ሰራተኞቹ “አቋማችን አንድ አይነት በመሆኑ መልስ ይሰጠን” በማለታቸው አቶ ደብረጽዮን ጥያቄዎቻቸውን ለመመለስ ቢሞክሩም መልሱ ካላረካቸው ሰራተኞች ጋር ሊግባቡ ግን አልቻሉም። አቶ ደብረ ጽዮን ”በኢንተርፕራይዞቹ ለመደራጀት የምትፈልጉ ትደራጃላችሁ” በማለት ሰራተኞቹን ለማግባባት ሲሞክሩ ከሰራተኞቹ ”አንፈልግም” የሚል የጩኸት ድምጽ በመሰማቱ ሚኒስትሩ ”ገንዘብ የምትፈልጉ ተሰልቶ ይሰጣችኋል” የሚል አማራጭ አቀረቡ፡፡ ይሄኔ ሰራተኞቹ ”የምንፈልገው እሱን ነው ” በማለታቸው ግራ የተጋቡ የሚመስሉት አቶ ደብረጽዮን ውስን ቁጥር ያላቸው ሰራተኞችም ቢሆኑ ለመደራጀት ከፈለጉ እንደሚያደራጁአቸው ቃል ገቡ።
አሁንም ከሰራተኛው የተሰማው ድምጽ ግን ” በጭራሽ አንፈልግም ” የሚል ነበር። ሰራተኞቹ በህብረት ድምፃቸውን ከማሰማት አልፈው አንዳንዶቹ ከመቀመጫቸው እየተነሱ አቶ ደብረጽዮን 3 አራት ጊዜ ሰራተኛውን የዋሹ በመሆናቸው ምንም ነገር ከእርሳቸው መስማት እንደማይፈልጉ በመግለጽ ስብሰባውን ረግጠው መውጣት ጀመሩ፡፡ የተቀሩትም ”ከመደባችሁ መድቡን አለበለዚያ ካሳችንን ስጡና አሰናብቱን” የሚል ተመሳሳይ ጥያቄ በማቅረብ ስብሰባውን እየጣሉ በመውጣታቸው ስብሰባው ሳይጠናቀቅ 5፡30 ላይ ተቋርጧል።
የዝግጅት ክፍላችን ጉዳዩን ለማጣራት ባደረገው ጥረት ምደባው አድሎአዊ ከመሆኑ ባሻገር የሞቱ፣ ከስራ የለቀቁና ከሀገር የወጡ ሰዎች ሳይቀሩ የተመደቡበት የግብር ይውጣ ስራ ጭምር እንደተሰራበት ለመረዳት ችሏል።