መምህራን ለ3 ዓመታት ሲወስዱት የነበረው የሙያ ማሻሻያ ኮርስ ዋጋ ቢስ ሆነ

መንግስት ላለፉት ሶስት አመታት መምህራን እንዲወስዱት አድርጎት የነበረው ተከታታይ የሙያ ማሻሻያ (continuous professional development) ኮርስ ምንም አይነት ዋጋ እንደሌለው ታወቀ። ይህንን ያስታወቁት አዲሱን ተከታታይ የሙያ ማሻሻያ በተመለከተ ስልጠና የወሰዱ የየትምህርት ክፍሉ ተጠሪ መምህራን ናቸው። የዲፖርትመንት ተጠሪዎቹ ሰሞኑን በየትምህረት ቤቱ ከመለስተኛ ደረጃ ጀምሮ ለሚገኙ መምህራን ስልጠና በሰጡበት ወቅት መምህራኑ ላለፉት ሶስት አመታት ሲወስዱት የነበረውን ኮርስና የኮርስ መፅሐፍ እንዲገመግሙት አድርገዋል። በዚህ ወቅት መምህራኑ የኮርሱ መፅሐፍት በጣም በወረዱ ይዘቶች የተሞሉ፣ ሳቢነት የጎደላቸው፣ የሚያቀርቧቸው ምሳሌዎች የመምህራኑን ክብር የሚነኩና የፀሀፊዎቹን ማንነት የማይገልፁ መሆናቸውን ተናግረዋል። እንደመምህራኑ አስተያየት ይህ ሊሆን የቻለበት ዋና ምክንያት የኮርሱ መፅሐፎች ዝግጅትም ሆነ ግምገማ ላይ መንግስት የጉዳዩ ባለቤቶች የሆኑትን መምህራንን ሊያሳትፍ ባለመፍቀዱ ነው።

ባለፈው ማክሰኞና ረቡዕ በቀጨኔ ደብረሰላም ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ውስጥ የተሰጠውን ስልጠና የተከታተለችው የሰርክአዲስ የዜና አገልግሎት ጋዜጠኛ ያነጋገረቻቸው መምህራን የኮርሱ መፅሐፎች ደካማ ጎናቸው የበዛ መሆኑን ገልፀው ኮርሱን ላለመውሰድ ቢያንገራግሩም የሙያ ፍቃድና የደረጃ ዕድገት ሊያገኙ የሚችሉት ኮርሱን ሲወስዱ ብቻ እንደሆነ በ/ት ቢሮ ሀላፊዎችና በርዕሳነ መምህራን አማካኝነት ስለተነገራቸው ይህንኑ ሲያደርጉ እንደነበር አስታውቀዋል።

ከመምህራኑ አስተያየት ለመረዳት እንደተቻለው በርካታ መምህራን ተከታታይ የሙያ ማሻሻያ ኮርሱን በሚገባ አልወሰዷችሁም በሚል የደረጃ ዕድገት ላይ ችግር ሲፈጠርባቸው የቆየ ቢሆንም አሁን ደግሞ መንግስት በራሱ ጊዜ የኮርሶቹን አይረቤነት በመግለፅ መምህራኑን ለመለኪያነት እንደማያገለግሉ እየገለፀ ነው። አንድ ስሙን ለመጥቀስ ያልፈለገ መምህር ለዜና አገልግሎት ክፍላችን ‹‹መንግስት ባለሙያዎችን ሳያማክርና በሚገባ ጥናት ሳያደርግ ለእርሱ ቅርብ በሆኑ ሰዎች ያዘጋጀው ኮርስ መፅፎች በጣም አሳፋሪ ነበሩ። በኮርስ አንድ መፅሐፍ ላይ ከነበሩት መልመጃዎች ውስጥ አንዱን የእውነት /ሀሰት ጥያቄ አስታዉሳለሁ፡፡ ጥያቄው ኤች አይቪ ኤድስ በመሳሳም ይተላፋል የሚል ነው፡፡ ይህ ጥየቄ እየቀረበ የነበረው በዲፕሎማና በዲግሪ ደረጃ ለነበሩ መምህራን ነበር፡፡ ያኔ ይሄ እንዴት ይመጥነናል ብንል ሰሚ አላገኘንም። በመሆኑም ሶስት አመታትን ሙሉ ቢያንስ በሳምንት ሁለት ሰዓታት ያህል ሞራላችን እየተጎዳ ኮርሱን ስንከታተል ነበርር። ኮርሱን ከሙያ ፍቃድ ጋር ባያገናኙት ኖሮ አንድም መምህር ዞር ብሎ አያየውም ነበር፡፡ ይሄው አሁን ደግሞ ያለፉት ኮርሶች ቀርተዋል። «ከሙያ ፍቃድም ሆነ ከደረጃ ዕድገታችሁ ጋር አይያያዙም።» በማለት አዲስ ያዘጋጁትን ሌላ መፅሐፍ አደሉን። የመጀመሪያው ቀን ኮርሱን ገምግሙት ሲሉን ከዚህ በኋላ የሚሰጣቸውን አስተያየት ወስደው መምህራንን ሊመጥን የሚችል መፅሀፍ ሊያዘጋጁ መስሎን ነበር። አሁንም ግን የበፊቱን ስህተታቸውን ደገሙ። የሀገር ሀብትና ንብረት እንዲሁም የመምህሩ ጊዜ በመንግስት እየተቀለደበት ነው›› በማለት የተሰማውን ምሬት ገልፃዋል።

ሁለት ቀናት የፈጀውን ስልጠና ለስልጠናው ተካፋዮች የምስክር ወረቀት በመስጠት መጠናቀቁ ታውቋል።