የወያኔን አምባገነናዊ አገዛዝ ለመገርሰስ ኢትዮጵያውያን እንነሳ!

በቃ! ጋዬ! ባስ! ይአከል!

ዋሽንግተን ዲሲ መጋቢት 1፣ 2011- “ማንም ሰው ዝናብን ማቆም ከቶ አይቻለውም” እንዲሉ፣ የመካከለኛውን ምሥራቅና ሰሜን አፍሪካ የናጠው የለውጥ ማዕበል በመለስ ዜናዊና ግብረ አበሮቹ ሊቆም አይችልም። በቅጥፈት የታጀበ የኢኮኖሚ ዕድገት ዲስኩር፣ መሠሪ የከፋፍለህ ግዛ ፖለቲካ ወይም የአሸባሪዎች ጥቃት ፕሮፓጋንዳ 80 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ነፃነት፣ ሰብዓዊ ክብር፣ የዲሞክራሲያዊ መብትና የተሻለ ህይዎት ከመጠየቅ አያግዳቸውም።

“ ከእንግዲህ ይብቃ!” በቃ፣ ጋዬ! ባስ! ይአከል! የምንልበት ጊዜ ነገ ሳይሆን ዛሬ ነው።

ኢትዮጵያውያን ሆ ብለን በመነሳት መፃዔ ዕድላቸውን መወሰን አለብን። በገጠር፣ በከተማና በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ህብረት በመፍጠር መለስ ዜናዊንና የወያኔ ሥርዓቱን ማስወገድ ይኖርባቸዋል። ለ20 ዓመታት የሰፈነ ጎሰኛና አምባገነናዊ ሥርዓት ማክተም አለበት! ለ20 ዓመታት የዘለቀ ግድያ… 20 ዓመታት ያስቆጠረ ሙስና፣ 20 ዓመት ሙሉ የተካሄደ የሥልጣን ብልግና በቃ! ይበቃል… 20 ዓመት የተንዛዛ አሠራር፣ ብልሹ አስተዳደር ይበቃል!

መለስ ዜናዊ የሀገር ጥፋትና የህዝብ ዕልቂት ሀዋርያ ነው። በተከተለው ዕብሪተኛ የፖለቲካ መሥመር ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ ለብዙ ሺህ ህይዎት መጥፋት ምክንያት ሆኗል። ያደረሰው አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በውጭ መንግሥታት፣ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ፣ ዓለም አቀፍ የሰው ልጆች መብት ተሟጋችና በኢትዮጵያ የሰው ልጆች መብት ካውንስል ተመዝግቦ ይገኛል። በተባበሩት መንግሥታት በኩል ጉዳዩን ለዓለም ዓቀፍ ወንጀል ችሎት ለማቅረብ በቂ መረጃ አለ። ለምሳሌ በ2005 በተደረገው ምርጫ 200 ሰላማዊ ሰዎችን በአደባባይ ረሽኗል፣ 780 የሚሆኑትን አቁስሎ ወደ 50 ሺህ የሚጠጉትን ደግሞ ለዕሥርና ለዕንግልት ዳርጓቸዋል።

በ2010 መለስ ዜናዊ የተጭበረበረ ምርጫ ከማካሄዱ ባሻገር በዩናይትድ ስቴትስ ለአምባገነን ሥርዓቱ የሚሟገት ጠበቃ ገዝቷል፣ 99.6 በመቶ የፓርላማ መቀመጫዎችን አሸነፍኩ በማለት ዲሞክራሲያዊ ምርጫን ማላገጫ አድርጎታል። ላለፉት 20 ዓመታት የተከተለው የተዛባ ፖሊሲ አብዛኛውን የሀገሪቱን ክልል ጉዳት ላይ የጣለ ሲሆን አሁን ለተከሰተው የዋጋ ግሽበት፣ ባንክ ዝርፊያ፣ ሥራ አጥነትና ስዴት ምክንያት ሆኗል። ተግባር ላይ የዋለው የተሳሳተ የግብርና ፖሊሲ እየጨመረ ከሚሄደው የህዝብ ቁጥር ጋር የሚጣጣም ባለመሆኑ በ2010 መጨረሻ ላይ ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ በህይዎት ለመቆዬት የምግብ ዕርዳታ አስፈልጎታል። ይህ ከለጋስ አገሮች የተሰጠ ምግብ የሥርዓቱ ደጋፊዎች ላልሆኑ ዜጎች የሚነፈጋቸው መሆኑ ተረጋግጧል።

መለስ ዜናዊ ዜጎቻችንን ከቀያቸው በማፈናቀል በአገራችን የሚገኙ ለም መሬቶችን ለውጭ ዜጎች በአልባሌ ዋጋ በመቸብቸብ የህዝብ መፈናቀልና የአካባቢ ውድመት እያስከተለ ነው ። 80 ሚሊዮን ህዝብ የሚኖርባትን አገራችንን ያለባህር በር እንዲትቀር አድርጓል። በሙስና የተዘፈቁና ከአንድ አካባቢ የመጡ ግለሰቦች የኢትዮጵያን የመከላከያ ሠራዊት ቁልፍ የአመራር ሥፍራዎች እንዲይዙ ተደርጓል። ለዚህ ነው የዓለም አቀፍ የሲቪክ ለውጥ በኢትዮጵያ እንቅስቃሴ የ20 ዓመቱ አረመኒያዊ አገዛዝ መፍረስ አለበት ብሎ የተነሳው። የመለስ ዜናዊ አምባገነናዊና ዘረኛ አገዛዝ ማክተም አለበት።

የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበራት፣ የሃይማኖትና የትምህርት ተቋማት፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ ሠርቶ አደሮች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ወጣቶች በሙሉ፤ የግብፅ፣ ቱኒሲያና ሊቢያ ወንድሞቻችሁና እህቶቻችሁን ፈለግ በመከተለ ሠላማዊ ትግል ለማካሄድ በቆራጥነት እንዲትነሱ ጥሪ እናቀርባለን

የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት፣ የፖሊስና የደህንነት አባላት ከህዝቡ ጎን በመቆም በዘረኛውና አምባገነኑ መለስ ዜናዊ ሊሰነዘር ከሚችለው ጥቃት እንዲትከላከሉ፣ የግብፅና ቱኒሲያ ሠራዊት አርዓያነት በመከተል በወንድሞቻችሁና በእህቶቻችሁ ላይ ማናቸውንም የሃይል ጥቃት ዕርምጃ ከመውሰድ እንዲትታቀቡ ጥሪ እናቀርባለን።

በአገራችን የዲሞክራሲያዊ ለውጥ ማምጣት ይቻል ዘንድ በመላው ዓለም የሚገኙ የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበራት በውስጥም ሆነ በውጭ አገር ከሚንቀሳቀሱ ዲሞክራሲያዊ ሃይሎች ጋር በመተባበር የሞራልና ማቴሪያል ዕርዳታ እንዲታደርጉ ጥሪ እናቀርባለን።

በቃ! ጋዬ! ባስ! ይአከልL!

ለበለጠ መረጃ የሚከተለውን ኢሜይል አድራሻ ይጠቀሙ፡ [email protected]