ከልሳነ ግፉዓን ድርጅት የተሰጠ መግልጫ
አገራችን ኢትዮጵያ የመብት ረገጣዎች ለዘመናት ያልተለያት፣ የፍትህና የነፃነት እጦት ጎልቶ የሚታይባት ብትሆንም፡ በተለይ ግን የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጭ ግንባር በትረ መንግሥቱን ከጨበጠ ወዲህ፡ የመብት፣ የፍትህ፣ የነጻነት አፈናና ረገጣ በከፋና ዘግናኝ በሆነ መልኩ እንደ ቀጠለ እኛ የዚያች አገር ተወላጆች ቀርቶ፡ የዓለም ህብረተሰብ በግልጽ የሚያውቀውና በሰፊው የዘገበበት ጉዳይ ነው። በተለይም የተፈጥሮ ግዛትነቱ የጎንደር መሆኑ በሚታወቀው በወልቃይት ጠገዴ በሚኖር ንጹሕ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ላይ የወረደውና አሁንም በከፋ መልኩ ተጠናክሮ እየቀጠለ ያለው አሰቃቂና ዘግናኝ ግፍና ሰቆቃ ለማስረዳት በቂ ቃላቶች አላገኘንላቸውም፡፡ የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጭ ግንባር በበርሃ በነበረበት 16ዓመት፣ እንዲሁም ሰልጣን ከተቆጣጠረ 20 ዓመት ሙሉ በወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ላይ፡ ግድያ፣ አፈና፣ ያለአግባብ እስራት፣ የንብረት ዝርፊያ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ማፈናቀል፣ የመሳሰሉትን ከመፈጸም ባሻገር፡ የሃገሬውን ሕዝብ የመኖርያና የእርሻ ቦታ በመንጠቅ ከትግራይ ብቻ ሰፋሪ እያስመጣ በመስጠት ሕዝቡ ቀዩን እየለቀቀ እንዲሰደድ ሆኗል (አንድን ወገን አጥፍቶ በሌላ የመተካት ዘመቻ–Genocide!)። ዛሬ የወልቃይት ጠገዴ ተወላጆች አርሰው የሚበሉበት ቦታ ከማጣታቸው የተነሳ፡ ለድህነት ተዳርገዋል፣ አዛውንቶች መጥለያ አልባ ቀርተዋል፡ ወጣቱ ቦዘኔ ሆኗል፣ አቅም ያገኘውም አገር ለቆ ለከፋ ስደት ተዳርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለስልጣናቸው አስጊ ነው ብለው ያመኑበትን ወይም የጠረጠሩትን ደግሞ፡ ሰበብ አሰባብ እየተፈለገ ማሰር፥ መግደል፥ መደብድብ የእለት ተእለት ተግባር ሆኗል።
ሰሞኑን በቱኒዝያ የተቀጣጠለው በግብጽ የተደገመው በከፍተኛ ፍጥነት በሰሜን አፍሪካና በመካከለኛው ምስራቅ በመዛመት ላይ ያለው የህዝብ አመጽ፣ ያርበተበተውና እንቅልፍ ያሳጣው የመለስ ቡድን፣ የአፈናና የግድያ የማስጠንቄቂያና የማስፈራርያ፥ የመገናኛና የሚድያ ቁጥጥሩ ከመቸውም ጊዜ በበለጠ አጠናክሯል። ለዚህም እንደ ማስረጃ ሊሆን የሚችል፡ በቅርቡ በወልቃይት ጠገዴ ልዩ ስሙ አድምላጭ ጆርጊስ ከተባለው ቦታ ውስጥ በወጣት ካሳሁን ይደግ ገ/ማርያም የተፈጽመው ግድያ ነው። ወጣት ካሳሁን በተለያዩ ግዚያት ባልበቃቁ ምክንያቶች ሲታሰርና ሲፈታ፣ በቅጣት ስም የርሱንና የወላጆቹን ንብረት ሲዘረፍ ቢቆይም፤ በጥር 15/2011 ቦንብ ለማጥመድ፡ በመንግሥትና በሕዝብ መገልገያ ተቋማት ላይ ጉዳት ለማድረስ ማቀዱን ተከታትለን ደርሰንበታል፡ በሚል የሃሰት ውንጀላ ይታሰራል። በጥር 30/2011 ወላጅ እናቱንና፡ ወንድሞቹን ወጣቱ ወደታሰረበት ቦታ እንዲመጡ ይደረጋል። ልጃችሁ ከዛሬ ጀምሮ ከዚህ አካባቢ አይታሰርም፡ ራቅ ወዳለ እስር ቤት እንዲላክ ከበላይ ትዕዛዝ ደርሶናል በማለት ቤተስቦቹ እንዲሰናበቱት ይታዘዛሉ። ወላጅ እናቱ እያለቀሰች፡ ቤተዘመዶቹ ቆሽታቸው እያረረ ከፖሊስ ጣቢያው እንዲለቁ ይደረጋል። በሚቀጥለው ቀን ማለት ጥር 31/2011 ዓ/ም ጥዋት ላይ ቤተስቦቹ ወደ ጣቢያ እንደገና እንዲመጡ በፖሊስ ይታዘዛሉ። ከጣቢያው እንደደረሱ ይሄውና ልጃችሁ መርዝ ጠጥቶ ከታሰረበት ክፍል ውስጥ ሞቶ ተገኜ የሚል አሳዛኝ መርዶ በጣቢያው አዛዥ ይነገራቸዋል። ወላጅ እናቱም ለመሆኑ ከእስር ቤት ውስጥ ገብቶ ማን መርዝ ሰጠውና ሞተ የሚል ጥያቄ ቢጠይቁም እብሪተኛው መልሳቸው ግን “… በቃ! ሬሳሽን ወስጅና ቅበሪ..” ነበር።
ልሳን ግፉዓን ድርጅት፡ የወጣት ካሳሁን አሟሟት ሲመረምር፣ መንግሥት በጭካኔ መርዝ ካጠጣው በኋላ፡ በጣረ ሞት ላይ እያለ ሁለት እጆቹ የፊጢኝ ወደኋላ አስረው ለይስሙላ ሃኪም ቤት እንደወሰዱትና ሐኪሙ ወጣቱ እንደማይተርፍ ከነገራቸው በኋላ የታሰረውን እጁ ሳይፈቱ ወደ እስር ቤቱ እንደመለሱትና ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ እስር ቤቱ ውስጥ ሒወቱ እንዳለፈች ለማውቅ ችለናል።
ይህ ከላይ የተጠቀሰውና ከዝያም የከፋ ግፍና በደል ለወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ሆነ ለመላው ሀገራችን አዲስ ነገር አይደለም የተለመደ እንጅ በመሆኑም፤
o በአዲስ አበባው ማእከላይና በጠቅላላው በሃገሪቱ እስርቤቶች ውስጥ በወገናችን ላይ አረመናዊ ጭካኔ የተሞላበት ስቃይ ማድረስን፤
o ለም የኢትዮጵያ መሬቶችን ከምስኪን ገበሬ በመንጠቅ ለባእዳን የውጭ ሃብታሞችን በመሸጥ ገበሬዎችንና በተሰቦቻቸውን ጭምር ለርሃብ መዳረግን፤
o በሃገራችን የኢንፎርመሽን ነጻነት እንዳይኖር በሚድያ ላይ እጅግ ከፍተኛ አፈና ማካሄድን፤
o ከቱኒዝያው አመጽ መዛመት ፍርሃት የተነሳ ከሶስት በላይ አብሮ በጎዳና መታየትን መከልከል፣ እመጽን ያነሳሳሉ ተብለው የሚጠረጠሩትን አፍኖ ማጥፋትናን ማስፈራራትን፤
o በየበቱ በመሄድ ለወላጆች ልጆቻቸውን በአመጽ እንዳይሳተፉ ኋላ ከማዘን አሁን ማስጠንቀቅ እንዳለባቸው መለፈፍን፤
o አመጽ ቢነሳ ሕዝብን ለመፍጀት ጦሩንና አልሞ ተኳሾችን በተጠንቀቅ የማስቀመጥን ተግባር ስራዬ ብሎ ለተያያዘው ለወገንተኛው የመለስ ቡድን፣ ልሳነ ግፉዓን ድርጅት አጥብቆ ይቃወማል፣ ያወግዛልም!! ለኢትዮጵያ ሕዝብ መብት መከበር ለሚደረገው ሁለንትናዊ ትግል ልሳነ ግፉዓን ድርጅት ከመሰል አጋሮቹ ጋር በመሆን የዜግነትና የድርጅት ግዴታውን በብቃት ይወጣል!!
የዜጎች ሰብአዊ መብት ይጠበቅ!!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!