አባይ ከካይሮ መልስ፤ ወደ ጣና ፍሰስ! (ግጥም)

የጎንቻው

በፈጠረህ ምድር አፍታ ስትድህ፤
ከርሰ-ምድር ገባህ ፏፏቴ አጢሰህ፤
ሰርገህ በቤታችን ምሽግ ቆፍረህ፤
አንጋዳ ገደሉ ማቆራረጫህ፤ መመላሻህ፤
ያጠላልፈናል ወልጋዳ እትብትህ፤
ስንት ድልድይ ናደ አፍለኛው ጐርፍህ፤
የራሳችን ምታት ሆዳችን፤ ቆርጠህ፤
ጊዮን ዙሪያ ጥምጥም መቀመቅ ወርደህ፤
አባይ አጥፊያችንም መዳኛችን ነህ።

የአገር አከርካሪ አጥንት ሰብረህ፤
ከዳተኛው አባይ ተጠያቂ ነህ፤
በጓዳ ጐድጓዳው ጠብታ አልቀረህ፤
ከሸጥ ከጅረቱ፤ ከማዕዱ አጥበህ፤
በጠለለው ውሃ ጣናን አቋርጠህ፤
አንተ ‘ደራሽ-ሙላት’ አድ’ዋ ነቅለህ፤
ምነው አደፈረስክ ‘ቀይ-አፈር’ ቀድተህ፤
ደለል እንኳ አታስቀር ድንጋይ አንጥፈህ፤
ለአገር ጥሪት ሳተው ንፉግ ጠራርገህ፤
አእዋፍ እንሰሳ ሰብል አስጠማህ፤
ኢትዮጵያን ሞጣጠህ ለባዕድ አቀናህ።
ሁለት ‘ሜሌኒያ’ እናትህን ግጠህ፤
መፈጣጠሪያዋን ሽሏን አግዘህ፤
አገር ምድረ-በዳ አጽሟን አራቁተህ፤
ፈሰስክ በሰው አገር ውለታም የለህ፤
በል ተሰብሰብ አባይ ጣና ሲጠራህ።
ታቅበናል እና በእሙን እንዳናይ፤
ከ‘ካይሮ’ ተመለስ ወንዛችን አባይ፤
አጉርፍ ወደ ጣና ከአብራክህ ክፋይ፤
ዓሣ በለስ ይዘህ ጥደፍ ወደ ላይ፤
በሄድክበት ናልን አድባራችን ሆይ፤
ጥማችን አርሰው ሞረሽ በአገር ላይ፤
ድረስ በቁርጥ ቀን አትሁን ቃል-አባይ፤
ሚስጥር አቀብለን ከ‘ካይሮ’ ሙዳይ፤
ማተብ፤ ኪታብ፤ ጽፈህ፤ ጻድቅ፤ የነብይ፤
በቀስተ ደመናው ጠቅሰህ ራዕይ፤
የ‘ታሒሩን’ ጀብድ፤ እንድንተነብይ፤
ድል እንድናበስር ‘መስቀል’ አምባላይ።
በ‘ፈርዖን’ ግዛት ‘ባቢሎን’ መንደር፤
ምድር ታርዳለች ሕዝባዊ ሹም-ሽር፤
እስኪ አባይ አካፍለን የ’ግብጹን’ ሚስጥር፤
እንዴት ‘ሙባረኩን’ ጣሉት ቀይ-ባሕር፤
‘ጽጌረዳ አበበ’ አሸዋማው ምድር፤
ወጣቱ አዘመረ የበልግ ክምር፤
እስኪ እንጠራቀም እንድንቆጠር።
ባህር በከፈለው በ‘ሙሴ’ በትር፤
አባይ ታዝዘሃል ፊትህን አዙር፤
እስኪ ፍሰስ፤ንፈስ ሰማያችን ቋጥር፤
በምድራችን ያጐርፍ አባይ ተጨመር፤
ከ‘ካይሮ’ ተመለስ ውረድ በሸገር።

የጐንቻው ! 11/02/11 [email protected]