በሀይማኖት ያለመከባበር አንድነታችንን ያናጋል!

ተፃፈ-ከአባቦራ

ሰሜን አፍሪካን እያናወጠ ያለውን የለውጥ እንቅስቃሴ ተከትሎ ሀገራችን ውስጥ ተሞክሮው ሊተገበር ስለመቻሉ መላምቶች (ምኞቶችን) ከሰሞኑ በተለያዩ ነፃ ድኅረ-ገፆቻችን እያነበብን ነው፡፡

የሰብዐዊ መብት ረገጣ በከፋበት፤በጎጥ የተደራጁ ፅንፈኞች ኢኮኖሚውን በተቆጣጠሩበት፤ ባለሀገር በሀገሩ ባዕድ በተደረገበት ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ህዝባቸውን አክብረው በሚገዙ መሪዎች በሚከሰት መጠነኛ ስህተት ለውጥን መፈለግ የዜጎች ሙሉ መብት ነው፡፡

በስልጣን ጥም የፖለቲካ ድርጅቶች ከሚያደርጉት መገለባበጥ የተለየ ጣዕምና ለዛ ያለው የህዝብ አመፅና እርምጃ የክብርን ዋጋ ይጨምራል፡፡

ሀያ ሶስት ዐመት በተቆለፈ ብረት ህዝባቸውን የቀጠቀጡት የቱኒሲያው ፕሬዘዳንት ‘ዘይነል-አቢዲን’ ወደጅዳ ከመኮብለላቸው አምስት ቀን ቀድሞ ባደረጉት የቴሌቭዥን ንግግር “…ህዝቦቼ ሆይ አሁን ነው ያወቅኋችሁ!…” እንዳሉት ሁሉ አምባገነኖች የናቁት ህዝባቸውን ሲረዱና በጡጫው ሲደቆሱ ነው መልካሙ!ተከትሏቸው የሚመጣውም ከነሱ ትምህርት በመውሰድ ህዝብን እንዲያከብር፣መብቱን እንዲጠብቅና በትረ-ስልጣኑን ሲረከብ የገባውን ቃል እንዲጠብቅ ያስገድዱታል፡፡

በ1964(እ.ኤ.አ)የሱዳኑን ጄኔራል አቡድ ከገለበጠው ህዝባዊ አመጽ በኋላ የመጀመሪያው አረባዊ የህዝብ እርምጃ እንደሆነ የሚነገርለት የቱኒሲያውና የግብፁ ለውጥ በባህልና ሀይማኖት ትስስር ባላቸው የተቀሩት ሀገሮች ብቻ ሳይሆን በአምባገነን አስተዳደር ለሚማቅቁ ሁሉ የፈነጠቀው ጮራ አለ! ከምዕራባውያን ዕርዳታ ውጭ መንግስትን ማስወገድ እንደሚቻል ላንቀላፋው አለም አሳይተዋል፡፡

ከታሪክ እንደምንረዳው ለጭቁኖች ድል አድራጊነት መሰረቱ መጨቆንን አሻፈረኝ ማለትና ለነፃነት አስፈላጊውን መስዋዕትነት መክፈል ጭምር ነው፡፡የቱኒሲያው መሀመድ ቦእዚዚም ያደረገው ይህንን ነበር፡፡ በዩንቨርሲቲ ምሩቅነቱ ስራ ማጣቱ ሳይሆን፤ ደካማ እናቱን እንዳይጦር አትክልት መቸርቸር መከልከሉን በመቃወም ነው ራሱ ላይ ቤንዝን አርከፍክፎ እሳት የለቀቀው!ምንም እንኳ አፈር ተጭኖበት ለውጡን ባይመለከት ህይወቱ ለጉስቁል ቱኒሲያውያን ነፃነት አጎናፅፋለች!

በቱኒሲያና ግብፅ እየተተገበረ፤በተቀረው የአረቡ አለም በጥንቃቄ እየተቀመረ ያለው ይህ ለውጥ መካከለኛ ምስራቅ ውስጥ በአጭር ጊዜ ውጤት የማሳየቱ ምስጢር በክልሉ ያሉት መሪዎች ከሌላው የከፉ አምባገነኖች ሆነው አይደለም፡፡ ከሀገራችን ተነስተን በዑጋንዳ አቋርጠን ዚምባቡዌ ቆም ብለን አለምን ብንቃኘው የትምክህት ሰረገላ ተፈናጠው ህዝባቸውን በእሳት ጅራፍ ቼ እያሉ የሚጋልቡ አፄዎች ብዙ ናቸው!

በአረቡ አለም የለውጡ ምስጢር በሀገራቶቹ የሚኖረው ህዝብ መከባበርና መስማማት ነው! የብዙ ብሄሮች ወይም ሀይማኖቶች ስብጥር ያልሆነው ይህ ህዝብ በተግባራዊ እርምጃዎቹ እንደአንድ የእግር ኳስ ቡድን ይናበባል፡፡ ከአራት ሳምንት ባልበለጠ ጊዜ የእስክንድሪያው ቤተ-ፀሎታቸው በቦምብ የተመታባቸው የግብፅ ክርስቲያኖች ከሙስሊሙ ወገናቸው በመተባበር የሆስኒ ሙባረክን ወንበር እየነቀነቁ መሆናቸው እንደምሳሌ ልንወስደው እንችላለን፡፡

ከዚህ አንፃር በሌላው ደምና ህይወት ለውጥን በሚጠብቁ የፖለቲካ ድርጅቶቻችን ለጊዜው ተስፋ ቆርጠን የህዝባችንን ትስስር ብንመረምር ህብረታችን ጠንካራ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ መፈቃቀሩ ኮስምኖ መከባበሩና መቻቻሉ ‘ካንገት በላይ’ እንደሚባለው እየሆነ ነው፡፡የዚህ ክፍተት ተጠያቂው ገዢው መንግስት ብቻ አይደለም፡፡ገዢው መንግስት ከፋፍሎ የመግዛት እስትራቴጂን ይጠቀማል በሚለው እስከተስማማን በዚህ በኩል የሚፈፅማቸው ወንጀሎች ሁሉ የሚገርሙ አይደሉም፡፡

ችግሩ ያለው እኛው ተጨቆንን የምንለው ወገኖች የጭቆናችንን እግረ-ሙቅ በራሳችን ላይ እያጠበቅን መሆኑ ነው፡፡ህዝብ አርነትን ሊቀዳጅ ህብረት ያሻዋል፤ህብረት የሚመጣው ደግሞ ከመከባበር ነው!እያንዳንዳችን የሌላውን ስም፣ቤተሰብ፣ቤተ-ዘመድ፣ጎሳ፣ብሄር፣ ሀይማኖትና የተቀሩት እሱነቱን ማክበር እስካልቻልን በጋራ የሀገር ጉዳይ ለመወያየት ጠረጴዛው አይኖርም!

ለብሄር ብሄረሰቦች የመብት ጉዳይ ትኩረት የሰጠነውን ያህል በሀይማኖታችን መከባበሩን አሳዛኝ በሆነ መልኩ ችላ ብለነዋል፡፡ይባስ ብለን መተነኳኮሱን በርትተንበታል!

ዕውቀቱ ባላቸው አባቶች የሀይማኖት ንፅፅር ውይይት ባይጠላም በአሁኑ ጊዜ በድህረ-ገፆች እየተስተዋለ ያለው የራስን ሀይማኖት እያነሱ የሌላውን መፈጥፈጥና ማዋረድ እጅግ አደገኛ መዘዝን ያስከትላል፡፡ዛሬ ልጓም ካልተበጀለት ነገ ወደ ታላቅ ብጥብጥ ሊመራን ይችላል!

ጃንዋሪ 20/2011 በኢትዮጵያን ሪቪው (Ethiopian review) ድህረ-ገፅ የተለጠፈው ‘የጴንጤው ተሳዳቢና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን’ የሚለው ፅሁፍ ባሁኑ ወቅት የአደጋ ነጋሪት ከሚጎስሙ አክራሪዎች ባንዱ የተዘጋጀ ነው፡፡አቶ አደፍርስ ተሰማ በተባሉ ሰው የተፃፈው ይህ አፍራሽ ፅሁፍ የኦርቶዶክስ ሀይማኖትን ሲያብጠለጥል ለከረመ የፕሮቴስታንት ፓስተር ተግሳፅ ተብሎ የቀረበ ቢሆንም ያነጣጠረው የእስልምና ሀይማኖትን በማኮሰስና ማውገዝ ላይ ነበር፡፡

ፓስተሩ በኦርቶዶክስ ሀይማኖት ላይ ለሰራው ስህተት አስታራቂ በሆነ መልኩ ማስተማር የሚጠበቅባቸው ፀሀፊ የእስልምና ሀይማኖትና አማኙን ሀላፊነት በጎደለው መልኩ ሲወርፉ፤ ፓስተሩን ደግሞ በወንጌላችን እንስማማ እያሉ ሲማፀኑ ተስተውለዋል፡፡

ስምን መልዐክ ያወጡታል እንደሚባለው አቶ አደፍርስ ድርጊቶ እንደስምዎ ነው፤ብዬ ክብርዎን ልነካ አልወድም፡፡ ፓስተሩን ሊቀጡበት ይገባ የነበረ በትር ሌላው ላይ ማሳረፎ ድፍረትዎን ከማጠያየቁ አልፎ ተራራን በትንፋሽ ፈቅ ለማድረግ ከመሞከር አይለይም፡፡ እኔም ሆንኩ አቶ አደፍረስ የምንወክለው ራሳችንን እንደመሆኑ የግለሰቡን ስህተት እንደኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን አለያ ምዕመናኑ ስህተት መውሰድ አይገባም፡፡ቤተ-ክርስቲያኗም ሆነች አማኟ ይህን መርዘኛ መልዕክት እንደሚያወግዙ እርግጠኛ ነኝ!

“…እስልምና ሀይማኖት ተብዬው መስጊድ ውስጥ ገብቶ በአምልኮ ላይ ያሉ ምዕመናንን በፈንጂ ያጋያል፡፡አንድ እስልምና አማኝ ሌላውን ይገድላል፡፡ዞሮ ተመልሶ ደግሞ …እስልምናን ይሰብካል፡፡ …”

ከዜና አውታሮች የቃረሙትን እንደመረጃ በመመርኮዝ ከላይ የተጠቀሰውን ሲፅፉ ይህ ትራጄዲ የሚዘወተርባቸው ኢራቅና አፍጋኒስታን ማን ወደሞት ማሳነት እንደቀየራቸው በሀቅ ሊያስቀመጡ አልደፈሩም፡፡ የጠቀሱትን ወንጀሎች እየፈፀሙ ያሉት ሞሳድና ሲ.አይ.ኤ ላለመሆናቸውም እርግጠኛ
አይደሉም፡፡

በእስልምና ሀይማኖትና በሽብር መካከል ያለው ርቀት በክርስትና ሀይማኖትና በሽብር መካከል ካለው ፍፁም ተመሳሳይ ነው፡፡

ሽብር ሀይማኖት የለውም! ሽብር የግለሰቦች ወይም የቡድን እንጂ የሀይማኖት ግብር አይደለም!በአለም ላይ እንደሰደድ እሳት ክልሉን በማስፋት ላይ ያለውን ሀይማኖት ተከታይ ሞራለ-ወልካፋ ሆኖ እንዲኖር በምዕራባውያን መገናኛ ብዙሀን የሚለፈፈውን መመርኮዝ መፍትሄ አያመጣም፡፡ ፍልስጤማውያን ለሉዐላዊነታቸው የሚያደርጉት ተጋድሎ በሽብር ከተፈረጀ ወዲህ የሽብርን ትርጉም ከመዝገበ-ቃላት ለመፈለግ የሚደክም የለም!

አስር አመት ባልሞላ ጊዜ በአሸባሪነት ውጊያ ጭምብል የእስልምና ሀይማኖትን ለማጥፋት በመቶዎች ቢሊዮን ዶላርና በሺህ የሚቆጠሩ ወታደሮቻቸውን ለሰዉት ‘ባለጊዜዎች’ አለምአቀፋዊውን ጉዳይ እንተውና ወደሀገራችን እንመለስ፡፡

“…ዛሬ በወያኔ ገፋፊነት አስከፊው እስልምና ስር ሰዶ ክፋት የተሞሉ መስጊዶች ምድሪቱን ባጣበቡበት ሰዐት አንድ ፈጣሪን እናመልካለን የሚሉ ለወንጌል አዳሪዎች ሊጎናተሉ አይገባም፡፡…”

አቶ አደፍርስ-ከላይ የተቀመጠው ፅሁፎ በሀምሳ ሶስቱ ግርግር ካገር ወጥተው እንዳልተመለሱ አስብ ዘንድ ገፋፍቶኛል፡፡ ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ የምንሊክ ቤተ-መንግስትን ሳይረግጥ ኢትዮጵያ ውስጥ የሙስሊሙ ቁጥር ከሰላሳ አምስት ሚሊዮን በላይ እንደነበረ ከአዋቂ የዋሉ ቀን ይሰሙታል፡፡ አለምአቀፋዊ ዝናን በመሻት ባለፈው አመት ሴፕቴምበር አስራ አንድ ቅዱስ ቁርዐንን አቃጥላለሁ ላለው ንክ ‘ፓስተር ቴሪ’ ጋዜጠኞች ላቀረቡለት ጥያቄ “ቅዱስ ቁርዐንን አንብቤ አላውቅም፤ግን ላቃጥለው እፈልጋለሁ”ብሎ የሰጠው አስገራሚ ምላሽ ያለምንም ዕውቀት ስለመስጊዶች ከፃፉት ከእርስዎ ተመሳሰለብኝ! በቤተ-ክርስቲያኗ ሌላ ወገን ‘ማህበረ-እርኩሳን’ እየተባሉ ከሚጠሩት የ‘ማህበረ-ቅዱሳን’ አንዳንድ ጋጠ-ወጥ አባላት ቀድሞ የሰማነውን ነው የደገሙልን!

በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የጥቂት መስጊዶች ግንባታ ላብከነከናቸው አቡነ ጳውሎስ እንዳስቀመጡት በአዲስ አበባ ከተማ ያሉ መስጊዶች ሁሉ የያዙት የመሬት ስፋት የቦሌው መድሀኔአለም ቤተ-ክርስቲያን ከያዘችው የቆዳ ስፋት ያነሰ መሆኑን አይዘንጉ!ከሀገሪቱ ህዝብ ግማሽ በላይ ከመሆኑ አንፃር አዲስ አበባ ውስጥ ያሉት መስጊዶች የከተማዋን ሙስሊም አንድ ከመቶ ፍላጎት አላሟሉም፡፡የሀይማኖቱ ህግ ደግሞ እንደቱሪስት ባሻው ወቅት ሳይሆን ማንኛውም ምዕመን መስጊዶችን በቀን አምስት ጊዜ እንዲጎበኝ(እንዲሰግድ) ያዛል፡፡

አንድ ገፅ ላልሞላው ሀላፊነት የጎደለው ፅሁፎ ብዙ ገፅ መመለስ ይቻላል! የእናትም የአባቴም ወላጆች(አያቶቼ)የእስልምና ሀይማኖትን ቢቀበሉም በክርስትናቸው የፀኑ የወንድምና እህቶቻቸው ልጅና የልጅ ልጆች የስጋ ዘመዶቻችን ናቸው!እምነታችን የየግላችን ሆኖ በሌላው ማህበራዊ ጉዳይ ጥብቅ ትስስር አለን፡፡የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ ማንበብ ለማይችለው የአባቴ አጎት ልጅ መፅሀፍ-ቅዱስን አነብለት ነበር!

እንደኔው ብዙው ኢትዮጵያዊ ልቁረጥ ቢል በማያስችለው የዝምድና ገመድ ተሳስሯል! እስላሙ ከክርስቲያኑ፤ ክርስቲያኑ ከእስላሙ ደምና የደም ስር ናቸው!አንዱ ካለሌላው ህይወትና ውበት የላቸውም! የእስልምና ሀይማኖት ቀኖና (ሸሪዐ) የሌላ ሀይማኖት ተከታይ ቢሆንም እንኳ በማንኛውም መልኩ የምንገናኘው ሰው ሙሉ መብቱን እንድንጠብቅ ያስጠነቅቀናል፡፡ ለዚህም ነው ታላቁ ነብይ መሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) መዲና ይኖሩ ከነበሩ አይሁዶች ይገባበዙ፤ ይበዳደሩ፤ በደስታና ሀዘናቸው ከጎናቸው ይቆሙ የነበረው!

የሀይማኖት አባትና ካድሬው ባልተለየበት ይሄ አጉል ዘመን ከፖለቲካው ግርግር ፍርፋሪ የማንጠብቅ ዜጎች የሀገራችንን አንድነት ከሚያናጋ የሀይማኖት ጉንተላ ራሳችንን እናርቅ፡፡ውስጠ-ምስጢሩ የምዕራባውያን ግፊት ቢሆንም፤ ሲነገር እንደምንሰማው ሱዳንን ለሁለት የገመሳት የሀይማኖት አለመከባበር መሆኑን ልብ እንበል፡፡ዝምታ ነገሮችን ወዶ ከመቀበል ብቻ የሚመነጭ አይደለም፡፡ በጊዜው መፍትሄ ቢበጅለት እንደትርፍ የጣት ጥፍር የሚቆረጥ እጢ፤ካንሰር ሆኖ በገላ ከተሰራጨ በኋላ ለማከም መሞከሩ የበሸተኛውን ህይወት ሊቀስፍ ይችላልና ‘ሳይቃጠል በቅጠል’ እናድርገው! ኢትዮጵያችን የሁላችንም ደሴት ናት!ባንዲራችን የሁላችን አርማ ነው!በሀይማኖት ስም ባይተዋርነት መፍጠር ይወገድ!በሀገር አንድነትና ህብረት የሁሉም ሀይማኖቶች ሀላፊነት እኩል ነው!

የሙስሊሙን ተሳትፎ ያገለለ ትግል ለድል እንደማያበቃ እንተማመን! ከአፍሪካ የዳቦ ቅርጫትነት ተረት ጀርባ ከቧጋችነት ፈቅ ለማለት ጋሬጣ የሆነብን ግምባር ቀደም ጠላታችን ድህነትንም ይሁን በአምባገነንነት የተፈናጠጡብን ገዢዎች ድል ለመንሳት በቅድሚያ ህዝቦቿ መተማመንና መከባበር ይገባናል!

ህብረታችንን ለመጠበቅ የማንኛችንም የሚዛን ጣራ ኢትዮጵያዊነት ብቻ ይሁን! ሀይማኖትና ብሄርን ግላዊ ጉዳዮች እናድርጋቸው! በነፃ ድህረ-ገፆቻችን ወንጌላዊ ምክሮችን ማንበብ የተለመደ እንደመሆኑ ከጉዳያችን ተዛምዶ ያለውን የታላቁ ነቢይ መሀመድ(ሰ.ዐ.ወ) ምክር ማስታወስ እወዳለሁ፡፡ “… ባህር ላይ እየተጓዘች ካለች መርከብ ውስጥ ከታችና ላይ ባለው የተለያየ ወለል ከተቀመጡ ተጓዦች የታቸኞቹ ውሀ ተጠሙ፤ የሚጠጣው ውሀ የሚገኘው ከላይኛው ወለል መሆኑ ያሳነፋቸው፤ ለምን ወደላይ በመውጣት ራሳችንን እናደክማለን?ከመርከቧ አካል ትንሽ ቀደን ከባህሩ እየቀዳን እንጠጣ ብለው መርከቧን መቦርቦር ተያያዙ፤ ከላይኛው ወለል ያሉ ተጓዦች ድርጊቱ እኛን አይጎዳንም ብለው ችላ አሏቸው፤፤መርከቧ ስትሰምጥ እነሱም አብረው አለቁ!…” እኛም መርከባችን ኢትዮጵያችንን ይቅር በመባባል፣በመቻቻልና በመከባበር እንጠብቃት!

የመናገር፣ መፃፍና ሀሳብን መግለፅ መብት መከበር ቢኖርበትም የህዝቦችን ህብረትና አንድነት ችግር ውስጥ እንደሚከት እስከታመነበት ገደብ መኖሩ አይጠላም፡፡ስለሆነም የመገናኛ ብዙሀኖች በአጠቃላይ፤ የድህረ-ገፆች በተለይ ሀይማኖትን በተመለከተ አፍራሽና ተንኳሽ መልዕክቶች ላይ ቁጥጥር ቢያደርጉ መልካም ነው!

አቶ አደፍርስ ተሰማ በፅሁፋቸው ማጠቃለያ በወርቃማ ቃላት እንዳስቀመጡት ሁሉ “…የተጣመመ ሀሳብ እሰጣ-ገባ ከመግጠም ይልቅ ወንጌሉ ‘ግራህን በጥፊ ሲመታህ ቀኝህን ስጥ’ እንዳለው ልዩነትን በማጥበብ ለጋራ መስራት ጠቃሚ ነው እላለሁ፡፡”
ሰላም እድገትና ብልፅግና ለሀገራችንና ለህዝባችን ይሁን!

ተፃፈ-ከአባቦራ
ጅዳ-ሳዑዲ አረቢያ
E-MAIL: [email protected]