በጥምቀት በዓል የጉለሌ ወረዳ ፖሊስ ምእመናንን ሲያዋክብ ዋለ

ከጉለሌ ነዋሪና የሰበካ ጉባኤ አባል

የጥምቀትን በዓል በየአካባቢው ያሉት አብያተ ክርስቲያናት ቤደብር በደብራቸው በመሆን በጥቅምት 10 ሲወጣ አጅበው ማደርያ መንበሩ ድረስ ሸኝተውና ጸሎትም አድርገው፤ ወደየቤታቸው የሚመለሱት ሲመለሱ፤የሚያድሩትም ያድራሉ፡፡ አብያተ ክርስቲያናቱ በቀኝ በኩል ወጥተው ተመልሰው ወደ ደብራቸው የሚከቱት ግን በግራ መስመር በመመለስ ነው፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት ጀምሮ ግን የቅዱስ ሩፋኤል ቤተክርስቲያን ስርአቱን እንደሌሎች አድባራት ለማካሄድ ችግር ገጥሞት በወጣበት ተመልሶ ሲገባ ከረመ፡፡

የአካባቢው ምእመናንም ለምን ይህ እንደተወሰነና የቤተክርስቲያኑኑ አመራሮችም ምክንያቱን እንዲነገሯቸው በተደጋጋሚ ሲጠይቁ የተሰጣቸው መልስና ሰበብ፤ ‹‹አሁን እንመለስ በሚባልበት የቀድሞው መመለሻ መንገድ ላይ የሙስሊሙ ሕብረተሰብ ስግደት የሚያካሂድበት ቦታ በመኖሩ፤ በዚያ በኩል ሲያልፍ ውዝግብ ተፈጥሮ ስለነበር ከዚያ በቀረበ አቤቱታ የቅዱስ ሩፋኤል ቤተክርስቲያን በወጣበት ቀኝ በኩል ተመልሶ በዚያው መንገድ እንዲገባ ተወስኗል ተባሉ፡፡ በዚህም ላለፉት ሁለት ዓመታት ሙሉ ክርክር ሲካሄድና በምእመናኑና በደብሩ አስተዳዳሪዎች መሀል ጉዳዩ ሲያስቸግር ቆየ፡፡

ጉዳዩን የሰበካ ጉባኤውና ወጣቶቹ እንደገና ለዘንድሮው የጥምቀት በዓል በማንሳት፤ ቀድሞ ለዘመናት ሲደረግ እንደነበረው በቀኝ ወጥቶ በግራ እንዲገባና ሥርአተ ጥምቀቱንም የአካባቢው ነዋሪ እንደሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ምእመናን እንዲያከብሩት በማለት፤ የጠነከረ ጥያቄ በማቅረባቸው፤ነገሩን የሚያጣራ፤የወጣቶችና የአካባቢ ነዋሪዎች ኮሚቴ ተቋቁሞ፤በቅድሚያ የሙስሊሙ ሕብረተሰብ ጸሎት ያደርግበታል የተባለውን ቦታ አስተዳዳሪዎች ጉዳዩን በተመለከተና የተባለውን ሰበብ አንስተው ሲያማክሯቸው የሰጡት መልስ ‹‹ወንድሞቻችን፤ምን ብለን ነው ታቦት በዚህ እንዳያልፍ የምንከለክለው? አናደርገውም፡፡ አብረን እየኖርን፤ማህበር እየተጣጣን፤ለደስታና ለሃዘን አንድ ላይ እየሆንን ምን ብለን ነው ይህን አይነት ነገር የምናነሳው? ወንድሞቻችን፤ እኛ አላደረግነውም፤ ነገሩን የሚያወሩት በሁለታችን መሃል መግባባት እንዳይኖርና በሰላም አብረን እንዳንኖር የሚፈልጉ ናቸው፡፡ እኛማ ባህሉና ስርአቱ የማይፈቅድ ሆኖ ነው እንጂ፤አዘጋጅተን፤ ጎዝጉዘን፤ደግሰን እህት ወንድሞቻችንን አብልተን አጠጥተን ብንሸኝ ደስ ባለን፡፡ ህጉ አልፈቀደም እንጂ፡፡ እና ይህንኑ ቃላችንን ለደብሩ ሃላፊ ጽፈን እንሰጣለን በማለት ሸኙዋቸው፡፡

በገቡት ቃልም መሰረት ወዲያው ይህንኑ ቃላቸውን በህጋዊ ደብዳቤያቸው አስፍረው፤ ለደብሩ ዓለቃ በመላካቸው የደብሩም አለቃ ይህንኑ የሙስሊሙ ማህበረ ሰብ አባላት ደብዳቤና የአካባቢውን ሕዝብ ደብዳቤ አያይዘው ለቤተክቤተክህነት አስተዳደር በማቅረባቸው የአዲስ አበባ ሰበካ ጉባኤም በበኩሉ የቀረቡትን ጥያቆዎችና ከሙስሊሙ ህብረተሰብ ወኪሎች የተላከውን ደብዳቤ በማገናዘብ፤ጥያቀውም አግባብ ያለው በመሆኑ ‹‹በተጠየቀው መሰረት ታቦቱ በቀኝ ክንፍ ወጥቶ፤ በግራ ክንፍ እንዲገባ የተወሰነ ስለሆነ ይህንኑ ተፈጻሚ እንድታደርጉ›› በማለት ትእዛዝ ያስተላልፋል፡፡

በተሰጠው የውሳኔ ትእዛዝ የተደሰቱት የሩፋኤል ቀሳውስትም የሙስሊሙ ህብረተሰብ አባላት የላኩትንም፤ የአዲስ አበባ ሰበካ ጉባኤ ጸ/ቤትም የሰጠውን ትእዛዝ፤ በሩፋኤል ደብር ለተገኙት ምእመናን ጥቅምት 8 ቀን 2003 ዕሁድ እለት ለተሰበሰበው አህዛብ የደስታው ደብዳቤ በንባብ ሲያሰሙ ምእመናኑም ደስታቸውን በእልለታና በጭብጨባ ተቀበሉት ደስታ ሆነ፡፡

ይህንኑ መሰረት በማድረግም ታቦቱ መልስ ያደርጋል በተባለበት ግራ ክንፍ ያሉ ነዋሪ ወጣቶች፤ መሄጃ መንገዱን በባንዲራ በማሸብረቅና በአካባቢው ለወራትና ከዚያም በላይ በየቦዩ ተጠራቅሞ ያለውን ቆሻሻ በመጥረግ፤ ጽዱ አካባቢ ፈጥረው፤ ነዋሪዎችን በማስተባበር ዳቦ በማስጋገር፤የታቦቱን አጃቢዎች ጠበል ጠዲቅ ለማቅመስ ዝግጅታቸውን አከናውነው ሁሉም ነገር በየደጃፉ ተዘጋጅቶ የታቦቱን መመለሻ ሰአት ይጠብቅ ጀመር፡፡

ታቦቱ እንደቀድሞው ባህልና ስርአት በግራ እንዲመለስ የሆነ እንደሆነ በደጃፌ ስለሚያልፍ አበላለሁ አጠጣለሁ በማለት ስለት ያስገቡም ስለነበሩ ዝግጅቶ አልቆ እየጠበቁ ነው፡፡

ታቦቱም መልስ ጀመረ፡፡ ወጣቶቹ ከአካባቢው ባሰባሰቡት ገንዘብ ሁለት ረጃጅም ቀይ አበባ ምንጣፍ ገዝተው ታቦቱ እየተራመደበት እንዲያልፍ አንጥፈው ወደ ግራ ማሳበርያው ላይ ሲጠብቁ አሳዛኝ ያልተጠበቀ ሁኔታ ተከሰተ፡፡

የጉለሌ ወረዳ 8 ፖሊስ አዘዥ ብርሃኔ የተባለው ፖሊሶች አሰልፎ፤ አድማ በታኝ መኪና አስመጥቶ፤ ታቦቱ ወደግራ መታጠፉን ትቶ በወጣበት ቀኝ በኩል እንዲመለስ ትእዛዝ ይሰጣል፤ ወጣቶቹም የተሰጣቸውን ህጋዊ ወረቀት በማሳየት በዚህ ነው መሄድ ያለበት ቢሉት ይሄው ፖሊስ አዛዥ ታቦቱን እንደተራ እቃ በመግፋትና አቅጣጫውን በማስለወጥ ከቆመበት ምንጣፍ አስወርዶ ወደ ቀኝ እንዲሄድ ገፍትሮ ሂዱ አለ፡፡

ወጣቶቹም ለምን የሚል ጥያቄ ቢያነሱና ይህን እንዲያደርግ የታዘዘበትን ደብዳቤ እንዲያሳያቸው ቢጠይቁ፤አሻፈረኝ በማለት ታቦቱ በወጣበት እንዲመለስ ሲያደርግ፤ ታቦቱን አጅበው ወደ ቤተክርስቲያኑ ለመሄድ የተሰበሰቡት ምእመናን፤ ታቦቱን ትተው በግራ በኩል ወደየቤታቸው ሲሄዱ፤ ታቦቱ ብቻውን ቀሳውስቱ ብቻ አጅበውት፤ ከሩጫ ባለነሰ አካሄድ ስርአተ ታቦቱ ተደፍሮ ወደ ቤቱ እንዲገባ ሲደረግ፤ያን ሁሉ ውጣ ውረድ ያሳለፉትና መንገዱን በቄጠማና በባንዲራ ሲያስጌጡ ቆሻሻውን ሲያጸዱ የሰነበቱት ወጣቶች ምርር ስቅስቅ ብለው ወደ ዓምላካቸው እያለቀሱ ‹‹አንተ ፍረድ›› አሉ፡፡

የፖሊሱ አዛዥ በጉዳዩ ላይ አስቀድሞ ተዘጋጅቶበት ወጣቶቹን ባንዲራውን በማዘጋጀታቸውና ለባለኮከቡ ባንዲራ ቦታ በማሳጣታቸው ለመደብደብ ካስፈለገም ደም ለማፍሰስ ተዘጋጅቶ የመጣ መሆኑን የተረዱት ወጣቶች፤ ግድ የለም የተደፈረው የፈጣሪ ጽላት ነውና ፈጣሪ ይፈርዳል ብለው አንጀታቸው እያረረ ወደየቤታቸው ከመግባታቸው በፊት ግን፤ ያንጠለጠሉትን ባንዲራ አውርደው ባሉኖቹን አፈንድተው በዚህም ምሬታቸውን ገልጸው ወደየቤታቸው ገቡ፡፡

የወያኔ ፖሊሶች የሚሰሩትን በማጣታቸው አሁን ደሞ ታቦት በየት ወጥቶ በየት እንደሚገባ በመወሰን ረብሻ ለማስነሳት ጥረት ቢያደርጉም ሕዝቡ ግን በትእግስት ምሬቱን ውጦ አልፎታል፡፡ አንድ የፖሊስ አባል ግን ሲናገር እንደተሰማው ‹‹አሁን ነበር እንደቱኒዚያ ማድረግ፤ ከሰው ጋር ያጣሉን አልበቃ አላቸውና ደሞ ከፈጣሪ ጋር ሊያጣሉን ተነሱ፡፡ ደግነቱ ፈጣሪ ለራሱ ጥበቃ ረዳት አይፈልግም ቅጣቱን ያውቅበታል›› ብለዋል፡፡