“አባ ጳውሎስ” እባኮዎት የምንኩስናዎን ልብስ ያውልቁ

ከመጸሃፈ ሲራክ

እግዚአብሄር ቀድሞውንም ይጥቀም ብሎ ሰውን በህገ ልቦና ፈጠረው። በዚየ ጸንቶ መኖር ባይቻለው ከስጋ ፍርድ ይድንበት ዘንድ ህገ ኦሪትን ሰራለት። በህገ ኦሪት ጸድቆ ወደቀደመ ክብሩ መመለስ ባይሆንለት አንድ ልጁን በስጋ ማሪያም ገልጾ ህገ ወንጌልን ሰራ፤ ስጋውን ደሙን ሰጠ። ሁዋላ ደግሞ ፍጹም መሆን ቢፈልግ ብሎ ስርአትን ምንኩስናን አራተኛ ህግ አድርጎ ሰራለት። ይህን የፍጹምነት መንገድ አንድ ብሎ ሲጀምር ለዚህ ክብር የጠራው የመጀመሪያውን ገዳማዊ አባት አባ እንጦንዮስን ነበር። በመልአኩ በቅዱስ ሚካኤል ዕጅ አምስቱን የጸሎት ጊዜያት ከነስግደት ስርአቱ (ኪዳነ አዳም፤ኪዳነ ኖህ፤ ኪዳነ አብርሃም፤ ኪዳነ ሙሴ እና የሃዲስ ኪዳን 6ኛውንና 7ኛውን የጨመረው እራሱ ነው) አስተምሮ ቆቡን በአክሊለ እሾህ፤ ቀሚሱ የመጎናፀፊያ፤ መቀነቱ የመግነዝ፤ አስኬማው የትንሳኤ ሙታን አንድም መቀነቱና ቀሚሱ አይነቱ ቀድሞ እመቤታችን ብስራተ መለአከን ስትሰማ የለበሰችው በንጽሀ ስጋ፤ ቆቡን በንጽሀ ነፍስ እንዲሁም አስኬማውን በንጽሃ ልቦና መስሎ አልብሶ አመንኩሶታል።

እንግዲህ ምንኩስና ግብሩ አለመ መላዕክት ሲሆን ይህም የፍጹምነት መንገድ ከግብጽ በረሃ ጀምሮ እያደገና እየሰፋ እስከ ሀገራችን ድረስ ለክርስትና ህይወት እስትንፋስ ሆኖ ብዙዎች ሰማያዊ ክብርን የወረሱበት ኢትዮጵያም መሬቱን ከፍለው ገሀነም እሳትን እስከማየት የደረሱ ብጹአን አባቶችን እስከማፍራትየደረሰችበት በዚህ 4ኛ በሆነው የምንኩስና ኪዳን ነው።

ዛሬ ደግሞ ሌላ ቀን ነው። ግንኙነቱ የተቃርኖ ነው። ቤተክርስቲያኑን እንመራለን ብለው እራሳቸውን በጴጥሮስ ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ ቦታ ያስቀመጡ ባለባበስ ሰማያዊ በግብር ምድራዊ የሆኑ መነኮሳትና ጳጳሳት አቡነ ጳውሎስና አንጋሾቻቸው እየሄዱበት ያለው መንገድና እየፈጸሙት ያለው በደል ቤተክርስቲያኑዋ እንደዘመነ አርዮስ በመናፍቃን እጅ መውደቁዋን የሚያሳይ ነው። የቤተክርስቲያን ጉዞ የመስቀል ጉዞ መሆኑን የማይረዳ ክርስቲያን የለም። ብዙዎቹ ገዳማውያን ቀርቶ ገና ያልተጠመቁ ጀማሪ ምእመናን ሳይቀሩ ስለ ክርስቶስ ፍቅር አንገታቸውን በሰይፍ እየተቀሉ በገዛ ደማቸው እየተጠመቁ የእግዚያብሄርን መንግስት የወረሱበት ዘመን ደመ ጥምቀትም ነበር።

እየሱስ ክርስቶስን ለመምሰል በሚደረገው የፍጹምነት ጉዞ መንገድ የሆነውን ሥርአተ ምንኩስና ከንቱ ለሆነ የዚህ አለም ክብርና የዘረኝነት ተስቦ የተጠቀሙበትን እነ አባ ጳውሎስ የይሁዳ የግብር ልጆች እንደመሆናቸው ዛሬ ቤተክርስቲያናችንን በእግዚአብሄር ስም ሳይሆን በሰይፍ ያስተዳድራሉ።

በዚህ ድርጊት ልባቸው የተሰበረና የቤቱ ቅናት ያቃጠላቸው ሊቀ-ሊቃውንት አለቃ አያሌው ታምሩ ለእውነት በመቆም የሚከተለውን የግዝት ቃል አስተላልፈው ነበር።

“ከዛሬ ጀምሮ በብፁህ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ እና ተባባሪ በሆኑት ሊቃነ ጳጳሳት እጅ ቡራኬ እንዳትቀበሉ፡ እንዳትናዘዙ፡ስማቸውን በጸሎተ ቅዳሴ የሚጠሩ አባቶች ቀሳውስት ካህናት ካሉም የአምልኮተ ጣኦት አራማጅ ናቸውና ተጠንቀቁዋቸው፡ ምክር ስጡዋቸው እምቢ ካሉም ተለዩአቸው። በዓል ሲመታቸውም የአሮን የወርቁን መታሰቢያ ሆኖ በቤተክርስቲያን ሊከበር የማይገባው ስለሆነ ጳጳሳት ይህንን ድርጊት አውግዘው ከስልጣናቸው ካላነሱ ምእመናን እንዳትዛዙአቸው፤ ደሙን ባፈሰሰ አምላክና ስም ቤተክርስቲያንን በሚመራና በሚጠብቅ በመንፈስ ቅዱስ ስም ጥያቄዬን አስተላልፋለሁ። በዚህም ተባባሪ የሆኑትንና ኣቡነ ጳውሎስን በምድር ያሰራችሁት በሰማይ የታሰረ ይሆናል ሲል በሰጠው ቃል በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስልጣን በጴጥሮስ ውጳውሎስ በማርቆስ በቄርሎስ በባስሊዮስ በቴዎፍሎስ በተክለህይማኖት ዘደብረሊባኖስ ቃል ኀጥእ ደካማ በምሆን በኔ በቀሲስ ወልደ ጊዮርጊስ ቃል አወግዣለሁ። ይህንን ህግ የተቀበሉና ከስራ ላይ ያዋሉ ሁሉ እንደ አሪዎስ፤ እንደመቃሪዎስ፤ እንደንስጥሮስ፤ እንደፍላቢዎስ፤ እንደ ኬልቄዶን ጉባኤና ተከታዮቹ እሱራን ዉጉዛን ይሁኑ። በማይፈታው በእግዚያብሄር ስልጣን አስሬአለሁ። ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይሁን።”

አለቃ አያሌው ታምሩ ዘዲማ ጊዎርጊስ

ከዚህ የፍርድ ቃል በታች የወደቅን ስንቶቻችን ነን? ማስተዋሉ ካልተወሰደብን በቀር በለምጽ የተመታው ክርስቲያናዊ ህይወታችን እንደተገለጠ መጸሀፍ ነው፣

ዛሬ የቀደምት አባቶቻችን ገድላቸው አፈታሪክ በሆነበት፣ የደገኛ አባቶቻችን የነቅዱስ ዮሀንስ አፈዎርቅና አትናቴዎስ ዘእስክንድሪያ ድካማቸው ከንቱ የሆነበት፣ ቅዱስ ሲኖዶስ እውነተኛ የፍርድ መፅሀፍ ይዘው እውነተኛውን ቃል ለመናገር ጉሮሮዋቸው አጥንት የሆነባቸው አባቶች የሞሉበት፣ ቤተክርስቲያንን ያስተዳድሩ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እነሱን ጳጳሳት አድርጎ የሾመበት አላማ ግቡን የሳተበት፣ አቡነ ጳውሎስ ግን ብቻቸውን የነገሱበትና ጸጋ እግዚያብሄር የተለየበት ቤት መሆኑን ይህ ዘመን አሳይቶናል።

ሳይገባን ክርስቲያን በሚለው ስም የተጠራን እኛ ዛሬ በዚህ በመጨረሻው ሰኣት ስለእግዚያብሄር ፍቅር ይህን አለም ጥለው የመነኑ መነኮሳት ራእይ አያችሁ፣ ትንቢት ተናገራችሁ፣ ተብለው ሊቀ ጳጳሱ በሚያዘምt ቸው በንጹህ ኢትዮጵያዉያን ደም የደለቡ የትግሬ ወታደሮች የሚታደኑበት፣ በአታቸው የተደፈረበት ወቅት መሆኑን ይህ ዘመን አሳይቶናል።

ለሀገራቸው በጎ የዋሉ ዘመን የመሸባቸውና በክብር ያረፉ ዜጎች እንኩዋን “የአማራ ፊውዳል አስከሬን ጥርቅም” ለኛ ምናችን ነው? በሚል በዮሴፍ ቤተክርስቲያን በተቀበሩ ሙታን ላይ እየደረሰ ያለውን መከራ ተከትሎ የሚወርደው የራሄል እንባ የግፉን ፅዋ ገና ሊሞላው እንዳልቻለ ያየንበት ይህ ዘመን ነው። ለመሆኑ ከፈርኦን እስከ ናቡከደነፆር፤ ከናቡከደነፆር እስከ ሄሮድስ፤ ከሄሮድስ እስከ ድቅልጢያኖስ፤ ከድቅልጢያኖስ እስከ ዮዲት፣ ከዮዲት እስከ አህመድ ግራኝ፣ ከአህመድ ግራኝ እስከ ሞሶሎኒ ፣ በእግዚያብሄር ልጆች ላይ ከወረደው ግፍና መከራ ሁሉ ባለፈው ሃያ አመት በርስዎና እርስዎ ድርሳነ ሳጥናኤልን እየደገሙ ባሰየጠኑዋቸው የቤተ መንግስት ጉዶች ልጆቾዎ ያልተፈጸመ ምን የቀረ ግፍና መከራ አለ ይሆን? ወዲህ ባለታሪክና ሉአላዊ ዜጋ እንዲሁም ክርስቶስ ዋጋ የከፈለላችዉ መባላችን የት ላይ ነበር ?

ክርስቶስ በስጋ ማርያም መምጣቱ የሰውን ባህሪ ከራሱ ጋር ለማስታረቅ ነበር። በሃጢያት ያጣነውን የእግዚያብሄር ልጅነት ይመልስልን ዘንድ ነበር። በሌላ አነጋገር የሰው ልጅ የእግዚያብሄር ልጅ ይሆን ዘንድ፤ የእግዚያብሄር ልጅ የሰው ልጅ ሆነ ማለት ነው። የእግዚያብሄር ልጅነት የመጨረሻው ጸጋ መሆኑ ነው። ለእግዚያብሄር ልጅ የመሆን መብት የተገኘው ደግሞ በክርስቶስ እንደሆነ ሃዋርያው ሲገልጽ “የእግዚያብሄር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደሰጠን እዩ እንዲሁም ነን… ወዳጆቼ ሆይ አሁን የእግዚያብሄር ልጆች ነን ምን እንደሆንን ገና አልተገለጠም። ዳሩ ግን ሲገለጥ እርሱ እንዳለ እናያዋለንና እርሱን እንድንመስል እናውቃለን በርሱም ይህን ተስፋ የሚያደርግ ሁሉ እርሱ ንጹህ እንደሆነ ራሱን ያነጻል” 1ኛ ዮሐ. 3

እግዚያብሄር ለመረጣቸውና ለወደዳቸው ሁሉ ይህንን የፍቅሩን ጸጋና በረከት በልቦናቸው ውስጥ እንዲኖር አድርጉዋል። ፍቅሩ በልቦናችን እንዲኖር ያደረገው የሰጠን የተስፋው ቃል የማይቀርና እውነተኛ መሆኑን ከመመስከር ጋር ነው። ስለዚህ በተሰጠንም በመንፈስ ቅዱስ የእግዚያብሄር ፍቅር በልባችን ስለፈሰሰ ተስፋ አያሳፍርም የተባለው።

በዚህም ነፍስና ስጋ፤ ሰውና መላእክት፤ ሰማይና መሬት ጭምር ታረቁ። ይህ እለት ቀድሞ በሐመረ ኖህ በምሳሌ የታየውና እርጊቢትዋ በዘንባባ ያበሰረችው ሰላም ተፍጻሜተ ትንቢት ነው። የእውነተኛው ሰላም ጥላ ነው። በመስቀሉ ሰላምን አደረገ እንደተባለው። ሲኦል እንደተማረከው።ሰይጣን ድል እንደተነሳው። ሞት ሆይ መውጊያህ የት አለ ሲኦል ሆይ ድል መንሳትህ ወዴት አለ? ብሎ ነብዩ ሆሴእ እንደጠየቀው። መቃብር እንደደነገጠው።

እንግዲህ አሮጌው ሰውነታችን ተወግዶ ባዲስ ሰውነት የምንፈጽመው በጎ ምግባር ለእግዚያብሄር የምናቀርበው በጎ ማአዛ ያለው ሰውነታችን መሆኑ ግልጽ ነው። ቅዱሱን እግዚያብሄርን በሃጢያተኛ ሰውነት መዋሃድ አይቻልም እና።ለዚህም ነው በአለም ተቀምጠው ምጽዋትን በመመጽወት ከሚኖሩ ክርስቲያኖች ይልቅ ሰውነታቸውን በጥም በረሀብ በስግደት በጸሎትና በትግሀ ሌሊት ቀጥቅጠው ለእግዚያብሄር የተቀደሰ መስዋእት ያደረጉ መነኮሳት ክብራቸው የበዛ የሚሆነው። በዚህም ክርስቶስ ለኛ ያለው የተገለጠበትን ጸጋ ልጅነትን የሰጠበትን እና ራሱን በጎ መስዋእት አድርጎ ያቀረበበትን መዋእለ ስጋዌ ፈለግ ተከትለው በስሙ የተጠመቁበትን ክርስቶስን በግብር የመሰሉት። “ተመሰሉ በእግዚያብሄር ከመውሉደ ፍቁራን” እንዲል ቅዱሱን እግዚያብሄርን የመምሰል ህይወት ለሚናፍቁ መልካም አርአያ በመሆን ለአልጫው አለም ጨው፤ ለጨለማው አለም የተራራ ላይ መብራት በመሆን በሞት አዘቅት ውስጥ የሚዳክሩትን ሁሉ ህይወት ላለው የክርስትና ህይወት ያበቁት። በዚህም ክርስትና በሰው ህይወት ላይ ሲገለጥ ምን እንደሚመስል መአዛውም እንደምን መልካም እንደሆነ ምሳሌ ሆነዋል። የዚህ ሁሉ የበረከት ምንጭ የሆነውን እግዚያብሄርንም ተከብረው አስከብረዋል። ምክንያቱም ለአንድ ሰው የጸጋና የበረከት ሚስጢር ማወቅና ማመን በራሱ ቀላል ነገር አይደለም። የመጀመሪያው በረከት እግዚያብሄር ከጸጋ የወረድነውን እና የቀኝ እጁ ስራ የሆነውን አዳማውያን ጠፍተን እንዳንቀር በልጁ አማካኝነት የሚያመለክት ነው። ስለዚህ እግዚያብሄር እኛን ነውር የሌለብን ቅዱሳን አድርጎ ወደሱ ሊያቀርበን በፊቱ ሊያቆመን በፍቅሩም ሊያኖረን ማሰቡን እና በልጁም አማካኝነት ይህን እንደፈጸመው ቃሉ ያስረዳል። የጌታችን ትንሳኤ በቅዱሳን ደቀመዛሙርቱ በምድር ከተገለጠና ከተሰበከ የሃዋርያት ድምጽ በምድር ዳርቻ ሁሉ ከደረሰ፤ ክርስትና ማፍራት ከጀመረ፤ ከቤተ እስራኤል ቅዱስ ጳውሎስ ያህል ሐዋሪያ ከተጠራና ቤተ ክርስቲያን ከአይሁድ ዛኒጋባ ወጣ ወደ ብሄረ አህዛብ ከተስፋፋች በሁዋላ ክርስቲያን ከስሙ ጀምሮ እስከ ተግባሩ የክርስቶስን ስምና ተግባሩን ተሸክሞ የሚኖር መሆኑ በተግባር ታይቱዋል። ቅዱስ ጳውሎስም “የእየሱስ ህይወት በህይወታችን ይገለጽ ዘንድ ሁል ጊዜ የእየሱስን መሞት በስጋችን ተሸክመን እንዞራለን” 2ኛ ቆሮንቶስ ምዕ 4 እንዳለ።

ይህ የሚያሳየው ሁለንተናችን ለእግዚያብሄር የተሰጠ ወይም በደሙ የተገዛን የደም ዋጋ መሆናችንን አምነን መላ ሰውነታችንን “እግዚያብሄርን ደስ የሚያሰኝና ህያው ቅዱስም መሰዋእት አድረገን ማቅረብ የሚገባን” መሆኑን ለማመልከት ነው። ሃዋሪያው ጳውሎስም “ከክርስቶስ ጋር ተሰቅያለሁ” ሲል ራሱን ክዶ መስቀሉን ተሸክሞ ህይወቱን ለክርስቶሳ አሳልፎ መስጠቱን በዚህም በዘመኑ ከነበረው የፈሪሳውያን ባህልና አሸዋው ልባቸው ከወለደው ደረቅ አስተሳሰብ ጋር ያደረገውን የተጋድሎ ህይወት ሲገልጽ ነው።

እንግዲህ ሦሥተኛውን ኪዳን ይፈጸም ዘንድ አንድ በክርስቶስ ስም የተጠመቀ ክርስቲያን ክርስቲያን በመሆን ሊኖረው የሚገባው ገጽታ ይህን መምሰል ካለበት እራሱን ከአምላኩ ጋር በአራተኛው የኪዳን ህግ ማለትም ከአለም ድሎትና ፍትወት የተለየበትን የቆብ ምልክቱንና የተገነዘበትን ሰንሰለቱን በውስጡ ታጥቆ መሞቱን ካወጀና በስርአተ ምንኩስና ራሱን ከአምላኩ ጋር ካቆራኘ በሁዋላ ሊሄደው የሚገባው ክርስቲያናዊ ጉዞ ምን መምሰል እንዳለበት ማወቅ አይከብድም።ቀደም ባለው የኦሪቱ ዘመን እስራኤልዘስጋ ከስደት ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲመለሱ አስራ አንዱ ነገድ እጣ ተጣጥለው መሬታቸውን ሲወስዱ የቀረው አንድ ነገድ (ቤተ ሌዋውያን) ግን እርስታቸውን እግዚያብሄርን አድርገዋልና ምድረ እርስትን አልተካፈሉም።

በስጋ ለተሰራ ሃጢያት በእንሣት ደም መርገመ ስጋን ያነጹ ዘንድ ስልጣን የተሰጣቸው ሌዋውያን ካህነት ይህን ያህል ከአለም ሀብትና ንብረት ከተለዩ የቅዱሱን የእግዚያብሄርን ልጅ ደም በመሰዊያው ፊት የሚፈትቱት በስጋና በነፍስ ላይ ስልጣን ያላቸውና የመንግስተ ሰማይን ቁልፍ በእጃቸው የያዙ የአዲስ ኪዳን ጳጳሳት ወመነኮሳት ምን ያህል ራሳቸውን ከዚህ አለም ሀብትና ክብር መለየት ይገባቸው ነበር ይሆን? ለመሆኑ ክርስቶስ የእሾህ አክሊል ከደፋ በሁዋላ ወደ አለም ተመልሶአልን? ወደመቃብር ነው የወረደው። እነ አባ ጳውሎስ ትናንት ከቅኔ ዘረፋ ከንቱ ውዳሴ ሲወርድላቸውና እበላ ባዮችም እግዚያብሄርን ትተው እሳቸውን ሲያሞግሱ የልተቃወመ ህሊናቸው ቆይቶ ፎቶአቸውን ዛሬ ደግሞ ሃውልታቸውን አስቆማቸው። ነገ ደግሞ እድሜ ከሰጠን ገና በህይወተ ስጋ ሳሉ ፅላት እንዳይቀረጽላቸው፣ መልከአ ጳውሎስ እንዳይጻፈላቸው ያስፈራል። ከንቱ ውዳሴ መንበረ ስላሴን እንደሚያስመኝ ከክፋት ልጆች ሁሉ አባት ከዲያቢሎስ የታየ ሃቅ ነው። ዛሬ እነርሱ በጥይተ ከላ( Bullet proof) መኪና ሲሄዱ እና የቤተክርስቲያኒቱን አንጡራ ሃብት የዘረኞች መጫወቻ ሲሆን በገጠር አቢያተ ክርስቲያናት ካባ ጠፍቶ በሴት ቀሚስ ይቀደሳል፤ በሴት ዣንጥላ ታቦት ይወጣል፤ መገበሪያ ጠፍቶ ስብሃተ እግዚአብሄር እየተስተጉዋጎለ በተክርስቲያናት እየተዘጉ ነው።ክርስቶስ ወደ እየሩሳሌም ሲገባ ሰረገላ አዘጋጁልኝ እንዳላለ ይልቁንም በተናቀች የአህያ ውርንጭላ መሄዱን ረስተዋል። በትርጉዋሜ ዮሃንስ እንደተጻፈው ሰለአዳም የተረገመችውን መሬት በቅዱሳተ እግሮቹ ይቀድሳት ዘንድ ያለጫማ በባዶ እግሩ ተመላለሰ የሚለው ቃል ዛሬ ለነሱ ተረት ነው።

ምንኩስናቸው ለስልጣን መውጫ ሳይሆን ህጉን አክብረው ንጽህናቸውን ጠብቀው በተጋድሎ እየኖሩ በአእምሮ ጠባይ የማይመረመር የክርስቶስን ጸጋ እንዲያገኙበት፤ ልኡል በፍህ ወደሚሆን ብርሃን እስኪጠጉ ድረስ ሚስጢር የሚያዩበት ከዚህ አለም በሞት ሳይለዩ የጥልቅና ሰማያዊ ሚስጢር ባለቤቶች የሚሆኑበት፤ ከመሎት በሚሰጥ በተወደደ ብርሃን አሸብርቀው ወደ ልኡል ብርሃን የሚወጡበት፤ እንደ ትጋታቸውና እንደመጠበቃቸው መጠን የክርስቶስን ብርሃን ተዋህደው በመልክ ጌታችንን የሚመስሉበት እንዲሆኑ ነበር። የጎሳ ተስቦ ከንቱ ውዳሴና እብሪት ክፉ ነው። ስለሆነም ዛሬ እነ አባ ጳውሎስ ወዳሉበት ወርደዋል። የነገውን ለማወቅ ደግሞ ነብይ መሆንን አይጠይቅም። እግዚአብሄር ፍጹም ነው፣ በፍርዱ ስህተት የለበትም!!!

ወስብሃት ለእግዚአብሄር!!!

መጸሃፈ ሲራክ ነኝ

ከምድረ ባርባሮስ