ለወያኔ ሰቆቃ ምላሻችን ምንድነው?
ከማወቅ ጥሩ
በወያኔ የወንጀል ምርመራና የእስር ቤቶች አስተዳደር ውስጥ የሚሰሩ አገር ወዳድ የፓሊስ፣ የፌደራልና የደህንነት ባልደረቦች በኢትዮጵያ እስር ቤቶች እየተፈፀመ ስላለው ሰቆቃ የላኩት ሪፓርት ይፋ ከሆነ ወዲህ በርካታ ኢትዮጵያዊያን እንቅልፍ አጥተዋል። “ምን እናድርግ?” የሚሉ ጥያቄዎችም
ተበራክተዋል።
ሪፓርት አቅራቢዎቹ ራሳቸው ከእኛ ምን እንደሚጠብቁ ግልጽ በሆነ አቀራረብ አብራርተውልናል። እነሱ ያሉንን እንደገና እናጢነው።
እኛም ይህን ሪፓርት ለእናንተ ለወገኖቻችን ስንልክላችሁ አንድ ሰሞን ጉድ ብላችሁ እንድትረሱት አይደለም። እኛ በራችንን ዘግተን፤ ጨለማን ተገን አድርገን አልቅሰናል። እናንተም እንደ እኛ አልቅሱ … አልቅሳችሁ ግን ዝም እንድትሉ አይደለም። በተለይ በውጭ ሃገር የምትገኙ ኢትዮጵያዊያን በዚህ ሃገር እስር ቤቶች ውስጥ የሚፈፀመውን በዘር የተደራጀና በዘር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት፤ በግለሰቦች ላይ የሚዘንበው ሰቆቃ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የዓለም የቀይ መስቀል ድርጅት፣ የህይውማን ራይትስ ወች፣ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ የጂኖሳይድ ወች ድርጅት፣ በሄግ የሚገኘው የዓለም ዓቀፍ ፍርድ ቤት፣ የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት፣ የአውሮፓ ፓርላማ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሌሎችም በሰው ልጆች ላይ የሚፈፀሙ ግፎችን የሚዘግቡ፣ ወንጀለኞችን ለፍርድ ለማቅረብ የሚታገሉ ሁሉ እንዲያውቁት እንድታደርጉ ነው። “ምን ዋጋ አለው?” ትሉን ይሆናል። አዎን ዛሬ ምንም ዋጋ ላይኖረው ይችላል። ብዙዎቹ መንግስታትና ድርጅቶች የወያኔን ግፈኝነትና ጨካኝነት ያውቃሉ። … ይህንን እያወቁ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ወያኔ ለሚፈጽመው ወንጀል ተባባሪ መሆንን መርጠዋል። ወያኔን በከፍተኛ ደረጃ በገንዘብ የሚደጉሙት በዲፕሎማሲ መድረክ እክል እንዳይገጥመው ድጋፍ የሚያደርጉለት ሆነው አርፈውታል። …
ይህንን መረጃ ስንልክ ዛሬውኑ አንድ ነገር ይሆናል ከሚል ቅዠት አይደለም። ነገ የሚባል ነገር መኖሩን መርሳት የለብንም። የዛሬ የሃገራችን እብሪተኛ ገዢዎች ነገ ቀን ሲጎድልባቸው እነዚህን መረጃዎች አሰባስበው ከሳሽ ለመሆን የሚሽቀዳደሙት እነዚህ እንደ ወያኔ ይሉኝታ የማያውቁ የምዕራብ ሃገሮች ስለሆኑም መረጃው በእጃቸው ቢገባ ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም ለማለት ነው። አቅም ያላችሁ ይህንን ዘገባ ተርጉማችሁ ለምዕራብ የሚዲያ ሰዎች፣ የሰው ልጅ መብት ሲጣስ ለሚያሳስባቸው የፓርላማ ተመራጮች፣ የሲቪል መሪዎች አድርሱልን።
በእናንተ በወገኖቻችን በኩል የሚደረገው ይህ ብቻ አይደለም። ይህ ብቻም በቂ አይሆንም። … ከወያኔ ዘረኝነት የሚመጣ ጭካኔ ያላረፈበት ዘር በሃገሪቱ ውስጥ አይገኝም። የኦሮሞው፣ የጋምቤላው፣ የኡጋዴኑ፣ የሲዳማው፣ የጉጂው እና የሌላውም ዘር ስቃይና መከራ ምድሪቱ ከምትሸከመው በላይ ሆኗል። ይህንን ተረድታችሁ ይህንን በሁሉም የሃገሪቱ ህዝብ ላይ የሰለጠነ የዘረኞች ጭካኔ እንዲያከትም ተባብራችሁ እንድትነሱ ነው።
ሌላው ፍላጎታችን ዜጎች ይህንን መንግስት እንደ ጤነኛ መንግስት በመውሰድ ከዚህ መንግስት ጋር እስካሁን የገቡበትን ማናቸውንም ግኑኝነት በቅጡ እንዲፈትሹ ነው። በእኛ እምነት ከዚህ መንግስት ባለስልጣናት ጋር የሚወዳጁ፤ ከዚህ መንግስት ጋር ተሻርከው የሚነግዱ፤ በዚህ መንግስት ግብዣዎች ላይ የሚገኙ፤ ይህ መንግስት የሚጠይቃቸውን የሚፈጽሙ የሃገሪቱ ዜጎች ከምን ዓይነት ጨካኝ አረመኔ ሰዎችና መንግስት ጋር እየሰሩ እንደሆነ እንዲያውቁት ነው። … ከዚህ ወንጀለኛ መንግስትና ባለሥልጣናት ጋር ስራችንና ኑሯችን ከሚያስገድደን በላይ መወዳጀት እራሱ ወንጀለኛ ሊያደርገን እንደሚችል ማወቅ ይኖርብናል።
በእውነቱ ከዚህ በላይ ምን ማለት ይቻላል? እነዚህ አገርወዳድ ዜጎች በኢትዮጵያ እስር ቤቶች ውስጥ እየተፈጸሙ ያሉ ሰቆቃዎችን፤ የሰቆቃ ፈጻሚዎችን ስም፤ በወያኔ ዳኝነትና በሰቆቃ መካከል ስላለው ትስስር ሁሉንም በዝርዝር ገልፀውልናል። እነሱ እንዳሉት ለአንድ ሰሞን “ጉድ” ብለን፤ ከንፈሮቻችንን መጥጠን፤ በየግላችን አልቅሰን ዝም እንዳንል ማድረግ ያለብንን ጭምር ዘርዝረው ጽፈዋል።
እኚህ አገር ወዳዶች የጣሉብንን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁዎችና ብቁዎች ነንን?
መልሳችን “አዎን!” ከሆነ ለጥሪዓቸው ተግባራዊ ምላሽ እንስጥ፤ በፀረ ሰቆቃ ትግል እንሳተፍ። በየደረስንበት በወገኖቻችን ላይ የሚደርሰውን ግፍ እናጋልጥ።
በቦሌ፣ በካሣንቺስ፣ በአራት ኪሎ፣ በፒያሳና በጉለሌ “የጨዋ” መኖሪያዎች የሚመስሉ ቪላዎች ወገኖቻችን ፍዳቸውን የሚያዩባቸው ድብቅ እስር ቤቶች መሆናቸው አንዘንጋ። ቡና ቤቶችና የባህል ሙዚቃ ቤቶች ጩኸት አገር ሰላም የሆነ ቢያስመስሉም እዚያው እጎናቸው ያለው ቤት ውስጥ ግን የሰዎችን አፍ ከካልሲ ወትፈው በኤሌክትሪክ ሽቦ በመጥበስ የሚዝናኑ አውሬዎች እንዳሉ አንዘንጋ። የወያኔ ድብቅ እስር ቤቶች ያሉት በየሰፈሩ እንጂ ሩቅ ቦታ አይደለም። አንዳንድ ወገኖቻችን በገዛ መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ በቤተሰቦቻቸው ፊት ተሰድበዋል፣ ተረግጠዋል፣ ታስረዋል፣ ተደብደበዋል። ደጋግን እንደገለጽነው በማናቸውም ምክንያት ሰቆቃ መፈጸም እጅግ የተወገዘ እና ምህረት የማያሰጥ ዓለም ዓቀፍ ወንጀል ነው። የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ሰቆቃ ፈፃሚዎች ፍርዳቸውን ማግኘታቸው ፈጽሞ አይቀርም። ሰቆቃንን ያስተናገዱ የወያኔ ካድሬ−ዳኞች፣ አቃብያነ ህግ፣ ፓሊሶችና ሌሎችም ሹማምንት ተገቢውን ቅጣት ማግኘታችው በጭራሽ አይቀርም። ያኔ “ታዝዤ ነው የፈጸምኩት” ማለት እንደማያዋጣ ዛሬውኑ እንነግራቸዋለን። ይህ ቀን መምጣቱ በጭራሽ አይቀርም። ያኔ ተጠያቂዎቹ ከላይ የተጠቀሱት ብቻ አይደሉም። “ምን ማድረግ እችላለሁ?” እያሉ ከንፈሮቻቸው መጠው የቀሩትም ቢሆን ከተጠያቂነት፤ እጅግ ቢያንስ ከህሊና ፀፀት አያመልጡም።
ያ ቀን መች ነው? ያ ቀን በቶሎ እንዲመጣ ምን እናድርግ? መረጃውን ያደረሱን ወገኖቻችን “ስቃይና መከራ ምድሪቱ ከምትሸከመው በላይ ሆኗል!!! …. የዘረኞች ጭካኔ እንዲያከትም ተባብራችሁ ተነሱ” ብለውናል። የኛ ምላሽ ምንድነው?