በኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት ከስራ ተሰናበቱ
ኢህአዴግ አራቱም አባል ድርጅቶቹ የሚሳተፉበት የሁለት ወራት ስልጠናና ግምገማ ማድረግ እንደሚጀምር ታወቀ፡፡ መጋቢት 5 ቀን 2003 ዓ.ም የሚጀመረው ይኸው ስብሰባ በሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ የሚደረግ ሲሆን ከአራቱም አባል ድርጅቶች የሚውጣጡ የየድርጅቶቹ ከፍተኛ አመራር አባላት እንደሚሳተፉበት ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡ በዚሁ የግምገማና የስልጠና ወቅት ገዢው ፓርቲ ከትግሉ ጊዜ ጀምሮ እስከ 2002 ዓ.ም ድረስ ያለውን ጉዞ እንደሚገመግም ለአባላቱ ማስታወቁንም ለመረዳት ተችሏል፡፡
ከውስጥ አዋቂ ምንጮቻችን የደረሰን መረጃ እንዳሚያመለክተው የስብሰባው ዋና አላማ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ ድርጅቱ የተቀላቀሉ በርካታ ቁጥር ያላቸው አባላቱን ኢህአዴጋዊ ማንነት ማላበስ ነው፡፡ ምንጮቹ አሁን አሁን ኢህአዲግ ከፍተኛ ስልጣን የሚሰጣቸው አባላቱን ሳይቀር ማመን እንደተሳነውና አዲሶቹ ተሿሚዎችም ቢሆኑ ለድርጅቱ ባዳነት የሚሰማቸው ጥቅም ፈላጊ ግለሰቦች መሆናቸውን ጨምረው ገልፀዋል፡፡ አዲሶቹ ተሿሚዎች ድርጅቱን እንደራሳቸው ድርጅት እንዲመለከቱትና ራሳቸውን ከድርጅቱ ጋር እንዲያዋህዱ ከትግል ጊዜ ጀምሮ ያለውን ሁኔታ የተመለከቱ ስልጠናዎች በሁለት ወር ቆይታቸው እንዲወስዱ እንደሚደረግም ተገንዝበናል፡፡ ለዚህ ዝግጅት ይረዳ ዘንድም ከጋራ ስብሰባው በፊት አራቱም ድርጅቶች ራሳቸውን እንዲገመግሙ ተደርጓል፡፡
ግምገማቸውን ካጠናቀቁት አባል ድርጅቶች መሀል አንዱ የሆነው የኦሮሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ድርጅት /ኦህዴድ/ ቀደም ሲል በወረዳና በዞን ደረጃ ያሉ አመራሮቹ ገምግሞ አብዛኞቹን ከሀላፊነት በማስወገድ በአዲስ እንደተካው ሁሉ ሰሞኑንም ባደረገው ግምገማ ተመሳሳይ እርምጃ መውሰዱ ታውቋል፡፡ ድርጅቱ በናዝሬት ከተማ ከየካቲት 12-20 ቀን 2003 ዓ.ም ድረስ ባካሄደው ግምገማ የኦሮሚያ ገንዘብና የኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ቶሎሳ ደደፉን፣ ምክትላቸውን አቶ ተስፋዬ አበበን፣ የኦሮምያ ፍትህ ቢሮ ሀላፊ አቶ ዮሀንስ ምትኩን ጨምሮ ዘጠኝ የሚሆኑ ባለስልጣናትን ከሀላፊነት አንስቷል፡፡ ባለስልጣናቱ ከሀላፊነታቸው ለመነሳታቸው ኪራይ ሰብሳቢነት፣ የአመለካከት ችግርና የስራ ተነሳሽነት ማጣት በምክንያትነት ቀርቧል፡፡
በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው አስተያየት ሰጪዎች ግን ድርጅቱ ያቀረበው ምክንያት እውነትን ለመሸፈን የተሰጠ ሰበብ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ የተሿሚዎቹን መነሳትም ኢህአዲግ ሊነሳ ይችላል ብሎ ስጋት ላይ ካለው ህዝባዊ አመፅ ጋር ያያይዙታል፡፡ በድርጅቱ መስመር አምነው የገቡ መሆናቸውን የሚጠራጠራቸውንና ክፉ ቀን ቢመጣ ሊከዱኝ ይችላሉ ብሎ የሚገምታቸውን ሰዎች ገለል እያደረገ እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡ ይህንን ሁኔታ ለማስተካከል እየሄደበት ያለውን የማባረርና አዲስ የመሾም እርምጃም ለውጥ የሚያመጣ እንደማይሆን አስተያየት ሰጭዎች ገልፀዋል፡፡ ይህንን ዓምገማ በበላይነት ከመሩት ውስጥ የኦሮምያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳደር አቶ አለማየሁ አቶምሳና የአዲስ አበባ ከንቲቶ አቶ ኩማ ደመቅሳ ይገኙበታል፡፡