የመኢአዴ ዋና ጽ/ቤት በከባድ ውጥረት ላይ ይገኛል
በሁለት በተከፈለው የመኢአዴ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መካከሌ በተፈጠረው አሇመግባባት ጥር 2/2003 ዓ.ም ጠዋት ጀምሮ የፓርቲው ጽ/ቤት በከባድ ውጥረት ውስጥ መሆኑን የዓይን እማኞች ገለፁ፡፡
በአዲስ አበባ የሚገኘው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአዴ) ጽ/ቤት በከባድ ውጥረት ውስጥ የወደቀው በአመራር ላይ የሚገኘው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በሁለት ቡድን ተከፍሎ አባላቱ የተካረረ ጸብ ላይ በመድረሳቸው መሆኑ ለመረዳት ተችሏል፡፡
ለፀቡ መክረር ዋናው ምክንያት የሆነው የፓርቲው ፕሬዚዲንት ኃይለ ሻውል ቅዳሜ ታህሳስ 30/2003 ዓ.ም ያካሄደት ሹም ሽር መሆኑ ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ፡፡ ይኸውም ፕሬዚዳንቱ አቶ ማሙሸት አማረንና ኮ/ል ታምሩ ጉልላትን ከሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነታቸው ማገዳቸው፣ ዶ/ር ታድዮስ ቦጋለን ወደ አንድ ቀጠና ኃላፊነት ዝቅ እንዲሉ ማድረጋቸው፣ አቶ ገብረፃዲቅቅ ኃይለማርያምን ከፓርቲው አባልነት ማባረራቸውና ወጣት ታጠቅ እና አቶ ሚሊዮንን ማገዳቸው፣ እንዲሁም የነአቶ ያቆብ ልኬን ቡድን ለማጠናከር በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ውስጥ አቶ ማህተመ በኩረንና ሌሎችንም መመደባቸው መሆኑ ታውቋል፡፡
ጥር 2/2003 ዓ.ም የአጋጁ ቡድን አባላት እነ አቶ ያዕቆብ ልኬ ቢሮውን ለመረከብ ወደ ጽ/ቤት በሄዱበት ወቅት አቶ ማሙሸት አማረና ዶ/ር ታዲዮስ ቦጋለ ከተወሰኑ ወጣቶች ጋር በግቢው ውስጥ በተጠንቀቅ ቆመው በመጠበቃቸው እነ አቶ ያቆብ ወደ ቢሮ ለመግባት አለመቻላቸውንና ሁለቱም ቡድኖች ተፋጠው መቆማቸውን በሥፈራው የነበሩ ሰዎች ገልጸዋል፡፡
ሁኔታው ያሰጋቸው አቶ ያዕቆብ ለፖሊስ ባደረጉት የድረሱልን ጥሪ የራዲዮ መገናኛ የያዙ ሁለት ፖሊሶች በጽ/ቤቱ አብረው መቆየታቸው ታውቋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የነአቶ ማሙሸት አማረ ቡድን አባላት የሆኑት አቶ ግርማ ነጋ የፓርቲውን ማህተምና ሌሎች ሰነዶች ይዘው በአቶ ገብረ ጻድቅ መኪና ከአካባቢው መሰወራቸውን እና የጥበቃ ኃላፊ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ደርቤም የሁለንም ቢሮዎች ቁልፎች ይዘው መጥፋታቸውን ከውስጥ አዋቂዎች ለመገንዘብ ተችሏል፡፡
እነ አቶ ያዕቆብ ልኬ በቅርብ የተካሄደውን የጠቅላላ ጉባዔውን ሂደት አስመልክቶ የይሁንታ መረጃ ከምርጫ ቦርድ ለመውሰድና ጽ/ቤቱን ተረክበው ፓርቲውን ለመምራት የሚያስችላቸውን ድጋፍ ለማግኘት ምርጫ ቦርዴ በመሄዴ ጥረት ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው የተመለሱ መሆናቸውን በአቅራቢያቸው የነበሩ ሰዎች ይናገራሉ፡፡
አመሻሹ ላይ ፖሊስ ግቢውን ሲለቅ የነአቶ ያዕቆብ ልኬ ቡድን አባላትም አብረው የወጡ መሆናቸው እና በአሁን ወቅት ቢሮው በነአቶ ማሙሸት ቁጥጥር እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ታህሳስ 30/2003 ዓ.ም አቶ ተስፋዬ ደርቤ ከመኢአዴ ጽ/ቤት በፖሊስ ተይዘው ፖሊስ ጣቢያ ከቆዩ በኋላ በዋስ መለቀቃቸው ይታወሳል።