ቃል
ቃልና የቃል ምሥጢር
ይከብዳል አሉ ከሰማይ ከምድር፤
በቃል ነውና “ይሁን” ተብሎ የሆነ
ሁሉም ፍጡር፣ ሁሉም ነገር የታመነ።
ወይ ጉዴ! – – – –
የአፍ ወለምታ ልማዴ! – – – –
‘’ቃል ቋቅ! – – -‘’ ባለበት ዘመን፣ ‘’ቃል’’ አልኩ እንዴ?
ለነገሩም ‘”የአፍ ወለምታ በቅቤ አይታሽም” ላሉት
ይጭነቅ እንጅ ለአበው፣ ቃል የሰው ማንነት-ህይወት
የሀይማኖት ማተብ-ግማድ አድርገው ላመኑት፤
ለ’ኔ ዘመንም፣ የአፍ ወለምታ ታሽቶ በአፍ ወለምታ
ይቀርባል ‘’ቃል’’ ሆኖ ለወዳጅ፣ ልሳን ተከፍቶ ልብ ሳያመነታ።
ተክሊል ካባ ተላብሶ፣መኮፈሱም ሆነ ‘መምበር’ መጨበጡ
ቱጃርነትም ሆነ ውዳሴ-መዝሙር፣ ዘምሮና ፅፎ-ቦርሾ መደመጡ
‘’ቃል’’ ካላበሉ አይታሰብም ሀቅን አንቆ ካልረገጡ።
ታዲያ ምን ከብዶኝ ‘’ቃል’’ ማለቴ – – — ?
ምን ‘’ህሊና’’ አለ በሰውነት አከላቴ – – -?
‘’የተናገሩት ቃል ከሚጠፋ የወለዱት ልጅ ይጥፋ’’ እንዳሉት
እንድ ቅድመ-አያት ወገኖቼ እንደኣለፋት
‘’ቃል’’ የለኝ ‘’ሀቅ’’ የሚነገር በአንደበት
‘’በስጋ’’ ተወለድኳቸው እንጅ የ’ ነርሱን የመንፈስ-ምግባር አልወረስኩት።
የዘምኑ ‘’ቃል – – -ቃለ-ቀሊል’’ ተናጋሪ-ሰሚም አያቅማማም
‘’እህ! – – -’’ ባይ ጆሮ ጠቢ እንኳ’ በአድባር-በሰፈሩ ቢጠፋም
የገደል ማሚቶ ያስተጋባውን፣ አነበናቢ የወሬ ቋት አያልፈውም።
ይሁን እንጅ ‘’ቃል’’ ግን ሕያው ነውና ትውልድ-ዘመነ አይሽረው
አነብናቢ-ጆሮ ጠቢ እንጅ ከሳሚና ጠፊው።
የእኔ ብጤውስ አነብናቢ፣ ጆሮ ጠቢ የገደል ማሚቶ
‘ረክሶ-አርክሶ፣ ገምቶ ከሚኖር አግማምቶ፤
ይሻለው ነበር ቢጠፋ በቃሉ
ሞት የኋላ-ኋላ መሆኑ እየታወቀ ‘’ፍፃሜ-ለኩሉ’’
‘’ቃል’’’ ብሎ – – – በቃል መኖሩም ሆነ መታመኑ
እንድ ጊዜው ስለሆነ እንደ ትውልድ ዘመኑ፤
በመቅደስ ቤቱ ሳይቀር በመድረክ ተውኔቱ
‘’ቃል ቋቅ! – – -‘’ ባለበት ዘምን ‘’ቃል’’ ማለቱ
በ’ርግጥ የራስ እንጅ የሌላ አይደልም መቅሰፍቱ።
– – – – // – – – –
ፊልጶስ / ሆላንድ (e-mail: [email protected])