ጫትና ቁልቋል ይለመልማሉ
ከእቁባይ
ውድ አጋሮቼና የምለውን ሁሉ እንደፈጣሪ ቃል አክብራችሁ የምትቀበሉኝ ከብቶቼ ሰላም!
አንዳንድ ሰዎች ከብቶቼ ማለቴን እንደስድብ ይቆጥሩት ይሆናል፡፡ ከብቶቼ ስላችሁ የበታቾቼ አድርጌ እንዳየኋችሁ አድርገው ሊነግሯችሁ ይነሳሉ፡፡ አትስሟቸው፡፡ ከነሱ ከተንኮል ሌላ ምን ይጠበቃል ብላችሁ ነው፡፡ እኔ ከብቶቼ ስላችሁ ደጎች ገሮች፤ የምትነገሩትን እንዳለ የምትቀበሉ፤ ሂዱ ስትባሉ የምትሄዱ፤ ቁሙ ስትባሉ የምትቆሙ፤ ተቀመጡ ስትባሉ የምትቀመጡ፤ ለምሳሌ ፕሬዜዳንት ብዬ እንዳስቀመጥኩት ማለቴ ነው፡፡ እና አትስሟቸው፡፡
የዛሬው ስብሰባችን አጭርና ግልጽ ነው፡፡
ሁላችሁም እንደምታውቁት፤ ባታውቁትም ታውቃላችሁ ብያለሁና ስለምታውቁት፤ ሃገራችን ከምታፈራቸው ፍሬዎችም ሆነ አዝርእቶች መሃል መጥፎና ጥሩ አለ፡፡ ለምሳሌ ከጥሩውና ሁላችሁም ልትወዱትና ልትንከባከቡት የሚገባችሁ ጫት፤ አዎን ጫት አለ፡፡ አያችሁ ስሙ እንኩዋን እንዴት ደስ እንደሚል፤
ጫ ት ስሜት ይነካል ትርጉሙ ደሞ
ጫ ማለት ጫላ ትርጉሙም ይበልጣል ሲሆን
ት ደግሞ ትግራይ ማለት ነው በአንድነት ሲነበብ ታዲያ ምን ይሆናል እስቲ ሁላችሁም ትርጉሙን በአንድነት ጮክ ብላችሁ በሉት
‹‹ይበልጣል ትግራይ!!››
እሰየው እንዲያ ነው እንጂ፤ ማለትም ‹‹ትግራይ ይበላጣል›› ሆነ!
ልክ ናችሁ፡፡ አስቀድሞ ቃል ነበረ ቃልም እውነት ሆነ የተባለውም እኮ ይሄ ነው፡፡ ይሄን ሰምተው ታዲያ እነዚህ ተቃዋሚ የሚባሉ ጉዶች ቃሌ ብለው ተነሱብን፡፡ ቃሉ አሁን ያልነው ነው በቃ!! በመጸሃፉም ያለው ያ ነው፡፡
ስለዚህም አንድ ውሳኔ ዛሬ ማስተላለፍ ይኖርብናል፡፡
ከዛሬ ጀምሮ በምንም ሰበብና ምክንያት በማንኛችንም ቤት በግላችን ለኛም ይሁን ለልጆቻችን አለያም ለእንግዳ ብርቱካን የሚባል ፍሬ እንዳይቀርብ፡፡
ቤታችን ጨርሶ እንዳይገባ፡፡
ጠላቶቻችን አውቀው ብርቱካን ቫይታሚን አለው ለጤንነት ጠቃሚ ነው እያሉ ሊያሳስቱን፤ ሊየያስወድዱን ነው ጥረታቸው፡፡ አትስሟቸው፡፡ ለራሳችንም ሆነ ለእንግዳ ወይም ለልጆቻችን ከዚያ አሁን ካልኩት ፍሬ ያልተናነስ ጥቅምና ጣእም ያለው ቁልቋል አለልንና ሃሳብ አይግባችሁ፡፡
ስለዚህም በዚህ በአንድ ሃሳብና ውሳኔ እንስማማ የዚያ ስሙን የማንጠራው ፍሬ ዘር ጨርሶ እንዳይበቅል ሁላችንም ተግተን እንስራ፤ ይህን ተግባራዊ የሚያደርጉ በቢ ፒ አር የሰለጠኑ ተቃዋሚዎቹ ትርኪምርኪ እያሉ የሚያጥላሏቸው አንበሶቻችን ተሰባስበው ሥራ ላይ ውለዋል፡፡
ዓላማችን ትራንስፎርሜሽን እያልን መጮህ ነው፡፡አውቃለሁ አብዛኛዎቻችሁ ትርጉሙ አይገባችሁም፤ ዋናው ጥቅም ደግሞ እሱ ነው፡፡ እኔም ብሆን ብዙም አልገባኝም ግን ለማደናበርያ ጠቃሚ ነውና እንቀበለዋለን፡፡
ይህን ትራንስፎረሜሽን ለማኮላሸት ትራንስፎርመሩን ለማቃጠል ጠላቶቻችን አይተኙምና በርትተን እንጠብቀው፡፡ ቢያንስ ያ ያልነው ፍሬ ድራሹ እስኪጠፋ፡፡
እርግጥ አንዳንዶቻችሁ ቅር ሊላችሁ ይችላል በተለይም የህክምና ባለሙያዎች፤ አታስቡ ስላላወቃችሁት ነው እንጂ ቁልቋል ያለምንም ጥርጥር ሊተካው እንዲሚችል ምርምር ያካሄዱ የቢ ፒ አር ባለሙያዎች ደርሰውበታል፡፡ ስለዚህም ጫትንና ቁልቋልን በመደባለቅ ጭማቂውን መጠቀም ከምንም በላይ ለጤንነት ለእድገት ፍቱን ነውና በዚሁ የዛሬውን ስብሰባችንን በማጠቃለል ተግባራዊነቱን በመከታተል እንዲያስፈጽምም አባዱላን ሰብሳቢ አድርገን ወክለናል በበላይ ሆና ሂደቱን እየተከታተለች የውጭ ገበያውንም የምታጠናልን ደሞ የሁላችንም የሆነችው ብቸኛ እንስት ጀግናችንና በንግዱ ዓለም ሰልጥናበት ቅርስና ሃብት በማካበት ተወዳዳሪ ያልተገኘላት የጋራ ንብረታችን አዜቤ ናት፡፡
አመሰግናለሁ፡፡
በሚሌኒየሙ ሂደት ጫትና ቁልቋል ይለመልማሉ!!