ልደቱ ለምን ወደ አሜሪካና አውሮፓ መጣ?

ተፈረደኝ አለሙ

ሰውን በሩቁ ማወቅን የመሰለ መልካም ነገር የለም፤ ምነው ቢሉ ሰውን በቀረቡት ቁጥር ውስጡ ተቀብሮ የተሸሸገው አውሬነቱ አፈጥጦ ይወጣና የነበረ አክብሮት፤ አድናቆት፤ እምነት፤ ሁሉም ነገር ይጠፋና ባዶ መሆኑ ይታወቃልና ነው፡፡

በሃገራችን ያሉትን አንዳንድ የተቃዋሚ ድርጅቶችና መሪዎቹን በሩቅ ስለምናውቃቸው ሲናገሩ ጤፍ ይቆላሉና አፋችንን ከፍተን፤ ንግግር ያውቃሉና (በማር የተለወሰ መራራ ጎምዛዛ ንግግራቸው) ከአፋቸው ለሚወጣው ቃል ሁሉ ጆሯችንን አስረክበን እናዳምጣቸዋለን፡፡

በመሃላና ግዛታቸው ተማምነን፤ ቃላቸውን ተቀብለን፤ እውነት ነው ብለን በመከተል በሄዱበት እንገኛለን፤ በተጠራንበት አቤት፤ ምን እንታዘዝ፤ በማለት ለግብር እራሳችንን እናዘጋጃለን፡፡ ውጤቱን ባያመጡም የመምጫውን መንገድ ያነበንቡልናልና እስኪመጣ እንጠብቃለን፡፡ የተጠበቀው ውጤትም ሳይመጣ ሲቀርና ደብዛው ሲጠፋ ሰበቡን ሲደረድሩልን አሁንም እንደገና፤ ሊመጣ ይችላል፤ አሁን ባይሆንም በሚቀጥለው ብለን ተስፋ ሳንቆርጥ፤ ትንሽ ትንሽ ተስፋችን ቢቀንስም እንጠብቃለን፡፡

ጊዜ አያሳየው የለምና መሪዎቹ ከጊዜ ብዛት የተነሳ ቢጠሯቸው የማይሰሙ፤ ኑሯቸው የተደላደለ፤ ሕይወታቸው የተሟላ፤ የተነሱበትን ዓላማና የየድርጅቶቻቸውን ዓላማና ተግባር፤ ደንብና መተዳደርያ ሕግ ጨርሰው ችላ በማለት አንዳንዶቹም ያን ብዙሃኑ ይሆናል ያገለግለናል ብለው ተናበው፤ አርመው፤ አስተካክለው አውጥተው አውርደው ያጸደቁትን፤ እነዚህ መሪዎች እንዳሻቸው ሲቆርጡ ሲቀጥሉ፤ እንዳስፈለጋቸው ሲያደርጉት፤ ከመተዳደርያ ደንብነት ወደ ግል ማስታወሻ መያዣ ደብተርነተት በመለወጥ ሊጠቀሙበት ይዳዳቸዋል፡፡

ከእነዚህ መሪዎች አንዳንዶቹ የያዙት እምቢ ሲላቸውና በአጋጣሚ የተንጠላጠሉበት የአመራር ወንበር ሊከዳቸው ሲርገፈገፍ ያን ወንበር አሳልፎ ከመስጠት ቆሜለታለሁ ብለው ምለው የተገዘቱበትን ዓላማ አሳልፈው በመሸጥ ከፍም ዝቅም ወደማይል በተቃዋሚ ስም ገዢ ፓርቲን አገልጋይነትን ይመኛሉ፡፡ ምኞታቸውም የተሳካ እንዲሆን በሚመሩት ፓርቲ ውስጥ የሚመከርበትን እቅድና ስትራቴጂ ገና የተፈራረሙበት ቀለም ሳይደርቅ ክህደታዊ ሽያጫቸውን ማዳለል ይጀምራሉ፡፡ ያለው ተጫራች አንድ ብቻ ነው፡፡ እነዚሁ የተቃዋሚው ድርጅት አመራሮች እንተካዋለን፤ ኢሰብአዊ፤ ኢዴሞክራሲያዊ ነው፤ ፍትሃዊነት ይጎድለዋል በማለት የሚከሱት፤ የሚወቅሱት፤ የሚወነጅሉት ድርጅት ነው ለመግዛት ብቸኛ ተጫራች ሆኖ የሚጠብቀው፡፡ አሁን አሁን ሻጮቹ ተበራክተው ጨረታው በማቆልቆሉ ቀደም ብለው ራሳቸውን በፊት ለፊት፤ ድርጅታቸውን በጓሮ በር የሸጡት፤ ዋጋ ስለረከሰና አገልግሎታቸውም ተራ እየሆነ፤ ሌሎች የበለጠ ያልተበላ እቁብ ይዘው በመቅረባቸው ልጣጭ የሙዝ ቆዳ የሆኑትን ጥሎ አዲሶቹን ያልበሰሉትን አስጠግቶ እንደመዥገር ያላቸውን እቅድና አካሄድ እየመጠመጠ ነው፡፡ እነዚያ ቀደም ያሉት የሙዝ ግፋፊዎች ደራቁቻ ሆነው፤ ጥቅም አልባ ስለሆኑ ገዢው ባለሃብት ወደ ቆሻሻ መጣያ ጥሏቸዋል። በዚህም ጊዜ ስለሁኔታው ለገበያ አማካሪዎቹ ሰብስቦ ሲያስረዳ፤

‹‹ሁላችንም ከዚያ ቆሻሻ መጣያ የወጣን አይደለን? ልዩነታችን በመሃላችን ያለው ጉዳይ እንጂ ከዚያ ያልወጣ ከመሃላችን ማን አለ፡፡ ከሌሎቹም ጋር የማያስማማን እኮ አመጣጣችን ባለመስማማቱ ነው፡፡ እኛ ግን ከአንድ የቆሻሻ መጣያ ቅርጫት ስለወጣን የበለጠ የቆሻሻ መጣያ ንብረትና የከሰረ ተብለን ተለይተን መቀመጣችን ነው፡፡ እኔን እንደምሳሌ አድርጌ ላቅርብ፡፡ ከቆሻሻ መጣያ ነው የወጣሁት፤ ያውም እጅጉን ከዘቀጠውና ከተጨማለቀው ቆሻሻ መጣያ፡፡ ከዚያ በመውጣቴ አሁን ያለሁት አናት ካለው መቀመጫ ነው፡፡ ሌሎቻችሁም በተመሳሳይ መመዘኛ እየተለካችሁ ቦታችሁን ይዛችኋል። እድገታችሁም በዚያው መጠን ይሆናል፡፡ ከዚህ ባለፈ ደሞ ከተለየ ቦታ ወጥተው አሁን ግን ከኛ ለመቀላቀል ሲሉ ወደ ቆሻሻ መጣያው ገብተው እንዲወጡ የተደረጉት እንደጠቃሚነታቸው ቦታ ተሰጥቷቸው አግልግሎታቸው ሲያልቅ ደሞ ወደሚገባቸው ቦታ ይጣላሉ፡፡ ምንም ቢሆን ከናንተ እኩል አይሆኑም፡፡ ስለዚህም ቀደም ብለው ለአገልጋይነት የመጡት ግልጋሎታቸው ስላለቀ ተጥለው አዳዲሶች መጥተዋልና በሚጣሉት ቦታ ተተክተዋል፡፡››

ነበር ያሉት፡፡

ቀጥለውም ‹‹በነገራችን ላይ የሚሰሙ ሁሉ ለምን እንደሚገረሙ አይገባኝም፡፡ ስለመልካም ኑሮ ለማውራት አስቀድሞ የመጣሁበትን በማስቀደም ስለሆነ መሆኑን እንዲረዱልኝ እፈልጋለሁ፡፡ ያን ለማድረግ ካልፈቀዱና ካፈሩበት ደሞ የምለግሳቸው ምክር ማንም ሊቃወመኝ ይችላል ቁም ነገሩ አድማጭ ማግኘቱ ላይ ነው እኔ ተቃውሟቸውን ቆሻሻ መጣያ ውስጥ ጨምሩት ነው የምላቸው›› በማለት አሳርጓል፡፡

እንግዲህ ልብ በሉ፤ አሁን ምርጫ 2002 ተጠናቆ ወደ ውስጥ የሚገባውና ወደ ውጭ የሚጣለው ተለይቷል፡፡ አሁንም ቢሆን ተመጠው፤ ታኝከው፤ ተተፍተው፤ ተረግጠው አልበቃንም ያሉት የተለየ ተልእኮ ይዘው ከሃገር ውጪ በመንከራተት ላይ ናቸው፡፡ የማስመሰያ ዘዴያቸው ሁሉ ስለታወቀባቸው ደሞ በሄዱበት ሁሉ ውርደት ቀለባቸው ሆነዋል፡፡

አንዳንድ የዋህ ወገኖች፤ ለምን ከውጪ ካለው ‹‹ኢትዮጵያዊ›› ድጋፍ ያገኛሉ? ሲል ይሰማል፡፡ ለዚህ እኮ መልሱ ቀላል ነው፡፡ የተቃዋሚ ድርጅት ደጋፍ እየተባለ መከረኛው የእውነት ነጻነት ፈላጊ፤ የምር ዴሞክራሲ የጠማው፤ የሰብአዊ መብት መጣስ ያነገፈገፈው ወገን ለትግሉ ሲል፤ ለፍትህ ሲል፤ ለነጻነት ሲል ከቤተሰቡ አፍ ነጥቆ ለዚህ ክቡር ተግባር እያዋጣ ይሰጣል። የሚቀበሉት ደሞ አሁን በዲያስፖራው ውስጥ ሆነው ከሀዲዎችን በዲያስፖራው መሃል ልዩነት እንዲፈጥሩ ከአሳዳሪዎቻቸው ተልከው የመጡትን እነ ክህደቱን ለማስተናገድና የራሳቸውን ኪስና የቤተሰባቸውን ሆድ ስለሚሞሉበት ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ለእውነተኛው ትግል፤ ለኢትዮጵያ አንድነት፤ ለሃገር ልማት፤ ለወገን ነጻነት፤ ለፍትህ፤ ለዴሞክራሲ ግንባታ ቆሙ ማለት በራሳቸው ጥረው ግረው ወጥተው ወርደው መብላት ማለት ስለሆነ ሞት መስሎ ነው የሚታያቸውና ከጸረ ሃገር ጸረ ወገን ጋር ቆመው ሕዝብና ሃገር ሲሞቱ እነሱ ለመኖር ነው ሃሳባቸው፡፡

ልደቱ በምርጫ ማግስት አንዳችም ተቃውሞ ሳያሰማ፤ ለወጉ ያህል እንኳን ምርጫው ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ አልነበረም ስለዚህ ይደገም እንኳን ሳይል ወያኔ አሸነፈ ሲባል ቀጣዩን የመከፋፈል ተግባሩን ለማካሄድ በጌቶቹ ምርቃት አግኝቶ ይቅናህ በርታ ተብሎ ተተፍቶበት ድል ጀባ ተብሎ ነው የተላከው፡፡
ልደቱ ዋነኛው ልጅ ሞቶ እንግዴ ልጁ ነው ያደገውና ያልተወለደውን ሰው እንዲተካ ሲባል በቤተሰቡ ልደቱ፤ ልፋቱ፤ ክህደቱ፤ የተባሉ አማራጭ ስሞች ቀርበው ልደቱ የተመረጠለትም ለሞተው ምትክ በመሆኑ ነው፡፡

ልደቱ ጠዋት ለቁርሱ ተንኮል፤ ቀን ለምሳው ተንኮል፤ ማታ ለእራቱ ተንኮል ነው ከምግቡ ጋር የሚቀርብለት፡፡ ስለዚህም ሁለመናው ተንኮል ነው፡፡ ፈጣሪ ተንኮልን ሲፈጥር መጀመርያ ሙከራውን ያደረገው በክህደቱ ላይ ለመሆኑ ማስረጃ መቁጠር ጨርሶ አያስፈልግም ተግባሩ ምስክር ነውና፡፡

በምርጫ 97 ወቅት ሚያዝያ 30 ላይ በተካሄደው ሕዝባዊ ስብሰባ ወቅት አቅርቦት የነበረው ሃሳብ በቀረበላቸው የማገናዘብ እውቀት ባላቸው ባይታገድ ኖሮ እልቂት የማይቀር ጉዳይ ነበር፡፡

ልደቱ ሚያዝያ 28 ቀን በተደረገው የሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ ላይ ስለ ሰልፉ ሁኔታ ውይይት ሲደረግና ምደባ ሲካሄድ አቅርቦት የነበረው ሃሳብ ‹‹ጥቂት ሰዎች ወደ ቤተመንግሥቱ እንዲገቡና ብጥብጥ አንስተው ድንጋጤ ይፍጠሩ። ያን ጊዜ የወያኔ ሹሞች ጥለው ይወጣሉ›› የሚል ሲሆን የተሰጠው ምላሽም ‹‹እንዲህ አይነቱ ሃሳብ መነሳትም የለበትም። በዚያን ሰአት ምናልባትም በግቢው ውስጥ የሚኖሩት ጥበቃዎቹ ስለሆኑ ሰው ያልቃል። ደሞስ ጥቂት የምንለውን በምን ልንለካው ነው። ማንስ ሊያስተባብር ነው፡፡ በጭራሽ አይደረግም የሚል ተቃውሞ ሲመጣበት በቁጣና በእልህ እየተንጨረጨረ ‹‹እናንተ እንቃወማለን እያላችሁ እየፈራችሁ፤ ትግሉን እያዳከማችሁ፤ ወደ ኋላ እየጎተታችሁት ነው፡፡ ሞት ተፈርቶ ትግል አይቆምም፡፡ እና ቢሞትስ ለነጻነት መሞት ሞት አይባልም፤ 10 ሺህ ሰው ሞቶ ሚሊዮኖች ነጻ ይውጡ›› ነበር ያለው፡፡ ለዚህም አመራሩ ‹‹አንድም ሰው ሳይሞትና ደም ሳይፈስ ይህ ያቀድነው ሕዝባዊ ስብሰባ መጠናቀቅ አለበትና ያንተ ሃሳብ ተቀባይነት የለውም›› ተብሎ ተሸነፈ፡፡

በሕዝባዊ ስብሰባውም ወቅት ከሌሎች ተለይቶ፤ አታድረጉ የተባለውንና ስምምነት ላይ የተደረሰበትን ገሸሽ በማድረግ የሰፈሩን ልጆች ለአጃቢነት አሰልፎ፤ እሱ አናቱ ላይና በትከሻው ላይ የኢትዮጵያን ባንዲራ አንግቶ በፒክ አፕ መኪና ላይ ጉብ ብሎ እንደ አንድ የሃገር መሪና ብቸኛ ጀግና በመምሰል ለእለቱ የተዘጋጀውን ሕዝባዊ ስብሰባ ለራሱ ክብርና ሞገስ ማግኛ ለማድረግ የጣረና እራሱን በዚያ ሁሉ ሚሊዮን ሕዝብ መሃል ያቀለለ ሰው ነበር፡፡

ሰውዬው በተለያየ ወቅት በኢትዮጵያ ሕዝብና የነጻነት ትግሉ ላይ ያደረሰው በደል እንዲህ በቀላል የሚፋቅ አይደለም፡፡ በተደጋጋሚ እራሱን ቢሮ ውስጥ እያሰረ ተደበደብኩ፤ ታፈንኩ፤ አትውጣ አሉኝ፤ ሌላም ሌላም በማለት አታሎናል፡፡ እንደምሳሌ የማነሳው በምርጫ 97 ወቅት መስቀል አደባባይ ባለው ቢሮ ውስጥ ታፈንኩ ባለበት ወቅት ወ/ሮ አና ጎሜዝና ዶር ሃይሉ አርአያ ወደ ቢሮው ሲሄዱ ያጋጠማቸው ጉዳይ ልደቱ በቢሮው ውስጥ እንዳለና ወ/ሮ አና ጎሜዝ ሊገቡ እንደሚችሉና ዶ/ር ሃይሉ ግን መፈተሽ እንዳለባቸው አስረድተው ወ/ሮዋ ከገቡ በኋላ ግን ዶ/ርን በፍተሻ ስም አንገላቷቸው ጎሻሾሟቸው፤ እንዳይገቡም ከለከሏቸው፡፡ ወ/ሮ አና ጎሜዝ ሲመለሱም ዶ/ር መኪና ውስጥ ገብተው ነው ያገኟቸው። መታፈኑን በተመለከተ ግን ወ/ሮ አና ጎሜዝ እንዳልገባቸውና ወደ ቢሮው ምግብም እንደሚገባ ስልክም በመነጋገር ላይ እንደነበረና ከክፍል አልወጣም ያለውም ልደቱ እራሱ እንደሆነ ሰበቡም አንዲት የቢሮው ሰራተኛ በመታሰሯ መሆኑን ነበር የተናገሩት፡፡ ዜናው ግን ታፈነ፤ ከቢሮ መውጣት ተከለከለ፤ ምግብም አይገባም ተባለ ነበር የተባለው፡፡ ይህ ደሞ ልደቱ እራሱ ለዜና ማሰራጫዎች ከላከው የፋክስ መልዕክት የተመሰረተ ነበር፡፡

አሁንስ ልደቱ ለምን ወደ አሜሪካና አውሮፓ መጣ? ሰበቡ ምንድን ነው? ደሞስ ለምን አሜሪካ ተመሳሳይ ሕዝባዊ ጥሪ አላደረገም? እና ሌሎችም ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ፡፡ ለሁሉም ጥያቄዎች መልሱ አንድ ብቻ ነው፡፡

‹‹የወያኔን የአምስት ዓመት ፕላን ተቀባይነት ለማሰጠትና ስለ ዝነኛውና መመርያና ጥናታዊ ጽሁፍም ስለሌለው‹‹ትራንስፎርሜሽን›› ለማስረዳትና እግረ መንገዱንም ዲያስፖራውን ለመከፋፈል፤ ለማዘናጋት፤ ከቆመበት ዓላማና ራዕይ በአቀንቃኞቹ አማካይነት ይህን ላማድረግ ነው›› በሚል መደምደም ይቻላል፡፡
የሚሉሽን ባላወቅሽ ገበያ ባልወጣሽ››የተባለውን የአበውን አባባል ዘንግቶ፤ ትላንት ያደረገውን ደባ ረስቶ፤ በትግሉ ላይና ሃገርና ሕዝብ ተስፋ ላይ ያፈሰሰውን ማዳፈኛ ተንኮሉን ችላ በማለት መልኩን ቀይሮ የትም ቢሄድ ከሃቀኛ ኢትዮጵያዊያን እይታ ጨርሶ ሊሸሸግ እንደማይችል አሁን ይገባው ይሆን፡፡ ‹‹ውሃ ቢወቅጡት እምቦጭ›› ነው እሱ፡፡