ከብርቱካን መለቀቅ በሁዋላ
የብርቱካን ጉዳይ የመጨረሻው ጫፍ ላይ መድረሱ ግልፅ ሆኖአል።
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ለአውራምባ ጋዜጣ የሰጡት ቃለመጠይቅ ላይ፣ “ብርቱካን አጥፍታለች ከተባለም፣ እስካሁን የታሰረችው ይበቃታል” ብለው ነበር። ጃኮብ ዙማ ስለብርቱካን ጉዳይ መለስን እንዲያነጋግረው በአና ጎሜዝ ተጠይቆአል። ኢትዮጵያውያን በውጭ ሃገር በየአደደባባዩ እየተገኙ ብርቱካን ከወያኔ ማጎሪያ ትለቀቅ ዘንድ፣ ወትውተዋል። ድረገፆች የብርቱካንን ስም ከግንባር ገፅ ለይተውት አያውቁም። እነ ስዬ አብርሃም ቢሆኑ “እንደ አቅማቸው” ካሌንደር አሳትመውላታል። መለስ በሄደበትና ባገደመበት ሁሉ የብርቱካን ስም እንደ ጥላው ተከትሎት እየመጣ መቸገሩንም አስተውለናል።
ያልተመለሰው ጥያቄ “ብርቱካን መቼ ትፈታለች?” የሚለው ብቻ ነበር።
አሁን እሱም ቢሆን መልስ ማግኘቱ ከወደ አዲሳባ እየተሰማ ነው። ብርቱካን ሚደቅሳና የቀድሞ የደርግ ባለስልጣናት የግእዙ መስከረም ከማለቁ በፊት ቃሊቲን ለቀው እንደሚወጡ የወሬ ጭምጭምታ አለ። ዋናው ጉዳይ ግን ይሄ አይደለም። ብርቱካን ይቅርታ ጠየቀችም አልጠየቀች፣ ከእስር መለቀቅ ይኖርባታል። ከአቅሟ በላይ መስዋእትነት ከፍላለች። የብርቱካን መለቀቅ ግን የደስታ ዜና ሊሆን አይገባውም። እንደ አንድ የትግል ግብ መወሰድ የለበትም። ነገ ደግሞ ሌላ ታጋይ ሊታሰር ይችላል። ከሚታወቀው ጠባዩ መለስ በማለዳ ተነስቶ፣ “እስኪ ደግሞ አንድ መደበሪያ ልስጣቸው!” እያለ የሚታሰር ሰው የሚያፈላልግ ይመስለኛል። ተቃዋሚው መሰረታዊ ጥያቄ እንዳያነሳ የታሰሩትን በማስፈታት ስራ ብቻ እንዲጠመድም ይህን እንደ ማዘናጊያ ዘዴ ይጠቀምበታል።
መፍትሄው ወዲህ ነው።
ወያኔ አንድ ሰው ሲያስር፣ ተቃዋሚው በበኩሉ ተቀራራቢ ርምጃ መውሰድ መቻል አለበት። ወያኔ አንድ ሰው ሲገድል፣ ተቃዋሚው ቢያንስ አንድ ባለስልጣን ላይ ተኩሶ መሳት መቻል አለበት። የትግሉን ሚዛን መጠበቅ የሚቻለው ተመጣጣኝ ምላሽ መስጠት ከተቻለ ብቻ ነው። እንደ ብሉይ ኪዳን፣ መፍትሄው “ለአይን – አይን” የሚል ብቻ ነው። የሪፖርተሩ አማረ አረጋዊ ሰሞኑን ያሰፈረው ርእሰ አንቀፅም ይህንኑ የሚጠቁም ነው። እንዲህ ይላል፣
“… ጠንካራ ተቃዋሚ ስንል … ጠንካራ ስድብ፣ ጠንካራ አሽሙር፣ ጠንካራ ጥላቻ፣ ጠንካራ ጩኸት፣ ጠንካራ ሰላማዊ ሰልፍ ማለት አይደለም…”
አማረ አባባሉን የተጠቀመበት ለአሉታዊ መልእክት ቢሆንም፣ በመስመሮች መሃል የምናየው እውነት ግን አለ። ከነዚህ ሁሉ ጠንካራ ድርጊቶች ባሻገር “ጠንካራ ዱላ ያስፈልጋል” እያለን ነው። በዚህ ዘመን፣ ከወያኔ ጋር በዚህ ደረጃ ሊታገል የማይችል ፖለቲከኛ ፖለቲካውን ትቶ ገዳም ቢገባ ይሻለዋል። ሴት እህታችን ለነፃነት ስትታገል ታስራ፣ ወንድ ወንድማችን ስንቅ አቀባይ የሆነበት የተገላቢጦሽ ዘመን ላይ ደርሰናል። ትውልድ አለመኮላሸቱን የምናረጋግጠው በተግባር ብቻ ነው። የወያኔ መርህ ግልፅ ነው። አንድ ሰው የገደለ “ወንጀለኛ” ይባላል። አንድ ሺህ ሰው የገደለ ደግሞ መሪ ይሆናል። እንዲህ ከሚያስብ ሃይል ጋር ምን አይነት ትግል ማድረግ ይገባል?
አማረ አረጋዊ የነገረን፣ “ድድ ሳይሆን ጥርስ ይኑራችሁ” ብሎ ነው። ተቃዋሚው አንድ ደረጃ ራሱን ከፍ ማድረግ ካልቻለ ወያኔ ጥርሱን ጨርሶ በድዱ መግዛቱን ሊቀጥል ይችላል። መቼም ፋሲል ደሞዝ እንዳቀነቀነው የጎንደር እናት ሳልሳዊ ቴዎድሮስን እስክትወልድ መጠበቅ ሊኖርብን አይችልም። ተወልደውም ይሆናል። አይናችንን ገልጠን የማየት ጉዳይ ነው። ከብርቱካን ሚደቅሳ መለቀቅ በሁዋላ፣ አእምሮአችንና ልባችን በአንድ ቅርብ ግብ ላይ ማነጣጠር መቻል ያለበት ይመስለኛል። ኢትዮጵያ የተባለችው ሃገርም ከእስር ልትፈታ ይገባል!!