ጃፓን ታስረው የነበሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ተፈቱ

ሰሞኑን ከሩቅ ምስራቅ አካባቢ የተሰማው አስደሳች ዜና እኛ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ያለነውን ብቻ ሳይሆን በርካታ ኢትዮጵውያን ያስደሰተ መሆኑን ስንገልጽ የላቀ ደስታ ይሰማናል፡፡ በጃፓን የስደተኛ እስርቤቶች ውስጥ ከሁለት ተኩል ዓመት በላይ ታስረው የነበሩ 17 ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ከጥቂት ቀናት በፊት መፈታታቸው ለእነርሱና ለቤተሰቦቻቸው ብቻ ሳይሆን ሰላምና ፍትሕ ወዳድ ለሆነው ሕዝባችን ከፍተኛ ሞራል የሚያጎናጽፍ ነው፡፡ ይህንን ታላቅ ዜና ነሐሴ 25፣ ቀን 2002 ዓ.ም. የንቅናቄያችን መሪ ለሆኑት አቶ ኦባንግ ሜቶ አንድ ከፍተኛ የጃፓን የፍትሕ ሚ/ር ባለሥልጣን በስልክ ደውለው ያበሰሯቸው ሲሆን እኛም በዚህ አጋጣሚ በአራት ወር ጊዜ ውስጥ ይህንን ዓይነት አፋጣኝ እርምጃ ለወሰደው የሚ/ር መሥሪያ ቤት እንዲሁም ጥረቱ ተጀምሮ እስኪያበቃ ድረስ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ሲያደርግ ለነበረው በጃፓን ለሚገኘው የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ያለንን ከፍተኛ አድናቆት ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

በጃፓን የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን አሰቃቂ ሁኔታ የሰሙት የንቅናቄያችን መሪ አቶ ኦባንግ ከአራት ወራት በፊት ይህንኑ ጉዳይ ለጃፓን መንግሥት ኃላፊዎች ለማስረዳት ወደዚያው አምርተው ነበር፡፡ በወቅቱም ከቶኪዮ ከተማ 100ኪሜ ርቀት ላይ በምሆ-ሺ ዩሺኩ በተባለ የስደተኞች ማጎሪያ እስርቤት ውስጥ ከሚገኙት 6 ያህሉን ኢትዮጵያውያን ጎብኝተው ነበር፡፡ እንደጃፓን ያለ እጅግ የሰለጠነ አገር በእስርቤት ውስጥ ሆነ በውጪ ያሉት ስደተኞች በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ይኖራሉ ብሎ ማሰብ እጅግ አዳጋች ነው፡፡ የእስረኞቹን መፈታት በተመለከተ የፍትሕ ሚ/ር ባለስልጣኗ ለአቶ ኦባንግ ባሳወቀቻቸው ወቅት አቶ ኦባንግም በአሁኑ ጊዜ ከእስርቤት ውጪ ያሉት ኢትዮጵያውያን የመኖሪያ ፈቃድ ለምን እንደማይሰጣቸው ወይም ወደሌላ አገር እንዲሄዱ ለምን እንደማይደረግ ቢጠይቋትም የአሁኑ የስልክ መልዕክቷ ስለተፈቱት ለመናገር እንደሆነና ቀሪው ጉዳይም በሂደት እንደሚታይ አሳውቃቸዋለች፡፡

እንደሚታወቀው ጃፓን ከሰለጠኑ አገሮች ሁሉ ጥብቅ የስደተኛ ፖሊሲ የምታራምድ ሲሆን ይህም እዚያ ለሚገኙ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ መከራ ውስጥ እንዲወድቁ አድርጓቸዋል፡፡ እነዚህ ስደተኞች ከአገራቸው ለስብሰባ፣ ለሩጫ፣ ለስልጠና፣ ወዘተ ከወጡ በኋላ በኢትዮጵያ ባለው ሰብዓዊ መብት ጥሰትና ሌሎችም ፖለቲካዊ ምክንያቶች ወደ አገራቸው ከመመለስ ይልቅ እዚያው ጃፓን እንዲቀሩ የተገደዱ ናቸው፡፡ ከ1978 ዓም እስካሁን ባሉት ዓመታት ከ 3500 በላይ የተለያዩ አገር ስደተኞች የፖለቲካ ጥገኝነት የጠየቁ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ከ100 የማይበልጡት ብቻ ናቸው ፈቃዱን ያገኙት፡፡ ከዚህ ውጪ ያሉቱ ጥገኝነት ጠያቂዎች ወረቀታቸውን በየ3 ወሩ $50 የአሜሪካ ዶላር እየከፈሉ ማሳደስ ግዴታቸው ነው፡፡ ሕጋዊ ፈቃድ የሌለው ሰው ትምህት ቤት ገብቶ መማር፣ በቂ ሕክምና ማግኘት፣ ወዘተ የማይችል ብቻ ሳይሆን በሕዝብ የትራንስፖርት መገልገያ ለመጠቀምም ይፈራል፡፡ ምክንያቱም በገንዘብ እጦት ምክንያት በወቅቱ የስደተኛ ፈቃዱን ያላሳደሰ በሕዝብ ትራንስፖርት ሲገለገል ፖሊሶች ድንገት ይዘው ወረቀቱን ቢጠይቁት ፍጻሜው እስርቤት መውረድ ይሆናል፡፡ ወረቀት አላቸው የሚባሉት ቢሆኑም እንኳን ቤት ለመከራየት ሲፈልጉ አስቀድመው የሥራ ፈቃድ፣ ቋሚ ሥራ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም የጃፓን ዜጋ የሆነ በኃላፊነት መፈረም አለበት፡፡ ይህንን ሁኔታ ከተከታተሉ በኋላ አቶ ኦባንግ በዚያው ከሚገኘው የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ጋር በመተባበር በተደረገው ስብሰባ ላይ በጃፓን የኢትዮጵያውያንን ስደተኞችን ብሶትና ምሬት አድምጠው ነበር፡፡

በስብሰባው ላይ ከተገኙት በርካታዎቹ ወጣቶችና ዕድሜያቸው ከ45 ዓመት በታች የነበሩ ሲሆን ምርታማ መሆን በሚችሉበት ዕድሜያቸው ከንቱ መሆናቸው እጅግ የሚያስቆጭ ነው፡፡ በመካከላቸው ከነበረ አንዱ አቶ ዮሐንስ ዓለማየሁ የተባለ ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ ሲናገር ‹‹እኔ በዚህ አገር ስኖር ከሦስት ዓመት በላይ ሆኖኛል፤ እስካሁን እያንዳንዷን ቀን ያለሥራ ምንም ሳላደርግ የማሳልፍ ሲሆን እጅግ የሚሳስበኝ ግን እስከመቼ በእንደዚህ ሁኔታ እንደምቀጥል ነው›› በማለት ለራሱ መልስ ያላገኘለትን ጥያቄ ጠይቋል፡፡ በመቀጠልም ሌላ የ17 ዓመት ወጣት ተመሳሳይ ነገር ከተናገረ በኋላ ካሁን አሁን ታሠርኩ በሚል ስጋት እያንዳንዷን ቀን እያሳለፈ መሆኑን ከጠቀሰ በኋላ እስርቤት ከሚገባ ሞትን እንደሚመርጥ ተናግሯል፡፡

ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ደግሞ በደረሰባት የመኪና አደጋ እስካሁን በተሸከርካሪ ወንበር ላይ ስትሆን አደጋው በደረሰባት ጊዜ ወደሆስፒታል ብትወሰድም ወጪውን መሸፈን ግን ስላልቻለች በቂ ሕክምና ሳታገኝ ከሆስፒታሉ እንደወጣች ተናግራለች፡፡ አሁን ያለችበትን አስከፊ ችግርና መከራ በምትናገርበት ጊዜም ስሜቷን መቆጣጠር አቅቷት በዕንባ ስትታጠብ ጉባኤተኛውም አብሯት ሲያለቅስ መመልከትን የመሰለ ልብ የሚሰብር ነገር የለም፡፡ ከዚህችኛውም ቀጥላ ሌላኛዋ ስትናገር የኢሚግሬሽን ወረቀቷን በወቅቱ ማሳደስ ባለመቻሏ በተደጋጋሚ ለእስር የተዳረገች መሆኗን ከጠቀሰች በኋላ በእስር ቤት በነበረችበት ወቅትም በሕመም ስትሰቃይ ተገቢውን ሕክምና መድሃኒት ያላገኘች ሲሆን ከዚህ ይልቅ የዕንቅልፍ ኪኒን ይሰጧት እንደነበር በእንባና በምሬት ተናግራለች፡፡

ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ደግሞ ይህችኑ ተከትላ የደረሰባትን ስትናገር በእስር በነበረችበት ወቅት እንዲሁ ሕመም ሲይዛት ቋንቋውን ማንበብ የማትችለውን መድሃኒት ሰጥተዋት ራሷን እንደሳተችና ከዚያም ስትቀጥል ከጃፓን ሊያባርሯት ኤርፖርት በወሰዷት ጊዜ የመንግሥት ባለሥልጣናትን የሚያውቅ አንድ ጃፓናዊ ዘንድ ደውላ ከመባረር እንደዳነች ከተናገረች በኋላ እስካሁ ግን ወረቀቷን ያላገኘች መሆኗን ገልጻለች፡፡

ቀጥሎም ሌላኛው ኢትዮጵያዊ በእስር ነበረችውን ሚስቱን በዋስ ለማስለቀቅ 2000 የአሜሪካን ዶላር ለማግኘት እንዴት እንደተሰቃየና በኋላ ግን በተለያየ አገር በሚገኙ ወዳጆቹ ትብብር ገንዘቡን ማሟላት እንደቻለ ተናግሯል፡፡ የሚስቱ መውለጃ ቀን ደርሶበት (በወቅቱ 7ወሯ ነበር) ግራ የገባው ሌላው ደግሞ ሲናገር ባለቤቱን ሆስፒታል በወሰዳት ጊዜ ወሊድ የጤና ጉዳይ እንዳልሆነ እንደተነገረውና ሚስቱን ለማዋለድ $5000 ዶላር መክፈል እንዳለበት የተነገረው

መሆኑንና ይህንን ለማሟላት ደግሞ ፈጽሞ እንደማይችል በገለጸልን ጊዜ አቶ ኦባንግ ከኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ኃላፊዎች ጋር በመሆን የጃፓንን የስደተኛ ማኅበርን ካነጋገሩለት በኋላ በአሁኑ ወቅት ወጪው ተሸፍኖለት ልጁን በሰላም ሊያገኝ መቻሉን ለማወቅ ችለናል፡፡

ባለቤቱና እርሱ በኢትዮጵያ ሲኖሩ ጋዜጠኞች የነበሩ መሆናቸውን የጠቀሰው ሌላው ደግሞ በኢትዮጵያ ባለው ከፍተኛ የፕሬስ ጭቆና ካገሩ ቢለቅም ግን እስካሁን ሁለቱም የፖለቲካ ጥገኝነት ያላገኙ መሆናቸውን ከገለጸ በኋላ ሲቀጥልም በአንድ ወቅት ባለቤቱ እስር ቤት ገብታ በነበረችበት ጊዜ በሕመም ስትሰቃይ እንደነበር በእንባ የሰጠው ምስክርነት የጉባዔተኛውን ልብ እጅግ የነካ ነበር፡፡

ሌሎችም በርካታ አሳዛኝ እና ስሜትን የሚረብሹ ምስክርነቶች በተሰማበት ስብሰባ ብዙዎች ስሜታቸውን መቆጣጠር እያቃታቸው ሲያለቅሱ ተስተውለዋል፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ክፍል ግን የእነዚህን ሁሉ ጉዳዮች አስፈጻሚ ሊሆን ይገባው የነበረው የኢትዮጵያ ኤምባሲ እነዚህ በደል የደረሰባቸው ኢትዮጵያውያን ለጃፓን ባለሥልጣኖች አቤት ሲሉ ኤምባሲው ከእነርሱ ጋር በመተባበር ለጥያቄያቸው ምላሽ ግፊት ከማድረግ ይልቅ ኢትዮጵያውያኑ ጥገኝነት ጠያቂዎች የሚያቀርቡት ጉዳይ ሁሉ ውሸት እንደሆነና ወደአገራቸው ቢመለሱ ምንም ችግር እንደሌለባቸው እንዲያውም እነዚህ ፖለቲካ ስደተኞች ሳይሆኑ ‹‹የኢኮኖሚ ስደተኞች›› መሆናቸውን በመናገር በመከራቸው ላይ ሌላ ስቃይ እየጨመረ ይገኛል፡፡

የዛሬ አራት ወር አቶ ኦባንግ የእነዚህን ኢትዮጵውያን ጉዳይ ለመከታተል ወደጃፓን ባቀኑበት ወቅት ከአገሪቱ የፍትሕ ሚ/ር፣ ከአምነስቲ ኢንተርናሽናል – ጃፓን እና ከጃፓን የስደተኞች ማኅበር ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር በጉዳዩ ላይ የተነጋገሩ ሲሆን አሻይ ሺምቡን እና ማዪኒቺ ከተሰኙ ከፍተኛ ተነባቢነት ካላቸው የጃፓን ጋዜጦች ጋር ቃለምልልስ አድርገው ነበር፡፡ እነዚህ ሁሉ ተግባራት አሁን ለተፈቱት እስረኞች በጎ ተጽዕኖ አሳድረዋል ቢባልም በጃፓን እና በተለያዩ አገሮች ተበታትነው የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በተመለከተ አሁንም ብዙ የሚቀር አለ፡፡ ለመሆኑ ኢትዮጵያውያን ለምንድነው እንደዚህ እየተሰቃዩ ከሰው በታች የሆነ ኑሮ የሚያሳልፉት? በቅርቡ በሳውዲአረቢያ እስርቤት 5 ኢትዮጵያውን ስደተኞች ሕይወታቸው አልፏል፡፡ ሌሎች የተሻለ ሕይወት ለመኖር ብለው ለተለያዩ አደጋዎች፣ ለወሲብ ንግድ፣ አሰቃቂ ለሆነ የቤትሥራ፣ ግዳጅ ሩካቤ፣ ወዘተ በመጋለጥ በመካከለኛው ምስራቅና በሌሎች አገሮች የመከራ ፍዳቸውን እየተጋቱ ይገኛሉ፡፡ ከግብፅ ድንበር ተሻግረው ወደእስራኤል ለመግባት የሚሞክሩ በግብፅ የድንበር ፖሊሶች እየተተኮሰባቸው እዚያው ሲቀሩ ሌሎችም በበረሃው እንደወጡ ቀርተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ያለውን የመብት ረገጣና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለማምለጥ ብለው እጅግ አስከፊ ለሆነ የስደት ኑሮ የተጋለጡ ወገኖቻችን በታንዛኒያ፣ በኬኒያ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በሱዳን፣ ወዘተ ምንም የተስፋ ጭላንጭል በሌለው ሁኔታ ከሰው በታች የሆነ ኑሮ እየገፉ ይገኛሉ፡፡ ይህ ሲሆን የሚመለከቱ በርካታ ወገኖቻችን ግን በአገር ውስጥ ያለው ሁኔታ ከምንም አይበልጥም በማለት በየቀኑ ከኢትዮጵያ ለመውጣት የሚያግዳቸው ነገር አለመኖሩን ስናይ ይህ የሕዝባችን መከራ የሚያቆመው መቼ ነው ብለን ከመጠየቅ ያለፈ ተግባር እንድንፈጽም ሊያስገድደን ይገባል፡፡ ለለውጥ እያንዳንዳችን ካልተነሳን፣ ለሚደርሰው ግፍ እምቢ ካላልን ህወሃት እና አቶ መለስ መቼም የሚሰጡን እንዳልሆነ የምንዘነጋው አይደለም፡፡ እስከ መቼ ነው ዝምታን መርጠን ውርደትን ተቀብለን የምንኖረው? መቼ ነው የወገናችን ጥቃት የእኛ አድርገን በመውሰድ ለወገናችን ድምጽ የምንሆነው? መቼ ነው እንዳንዳችን ለሁላችን፤ ሁላችንም ለእያንዳንዳችን የምንቆመው?

በጃፓን በሚገኙ ኢትዮጵያውን ላይ የደረሰውን ሰቆቃ በማጋለጥ ወገኖቻችን ከእስር እንዲፈቱ በግላቸው ከፍተኛ ጥረት ላደረጉ ኢትጵያውያን ከፍተኛ አድናቆታችንን እየገለጽን በተለይ ደግሞ አደይአበባ በጃፓን የኢትዮጵያውያን ማኅበር ሊቀመንበር የሆኑትን አቶ አበበ ዘውገ እና አብረዋቸው ይሠሩ የነበሩ ሌሎች ወደ አሥር የሚጠጉ ትጉሕ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ምስጋና እናቀርባለን፡፡ እነዚህ ወገኖቻችን የአቅማቸውን አበርክተው ለእነዚህ በደል ለደረሰባቸው ኢትዮጵያውያን ያላቸውን በማበርከት ይህንን አኩሪ ተግባር ፈጽመዋል፡፡ አዲሲቷ ኢትዮጵያም እንደነዚህ ባሉ መልካም የወገን ተቆርቋሪዎች ትመሠረታለች፡፡ ጥያቄው ግን እርስዎ ከእነዚህ አንዱ ለመሆን ለዚህ የተቀደሰ ተግባር የበኩልዎን ለማበርከት ፈቃደኛ ነዎት? ከሆኑ ዛሬውኑ የንቅናቄያችንን ድረገጽ solidaritymovement.net በመጎብኘት የአቅምዎን እንዲያበረክቱ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

(ለተጨማሪ መረጃ [email protected])