እንዬ፦ በሚኒሶታ የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት ነጋዴ

ወደ አሜሪካ የመጣችው በ1987 ዓ.ም እንደ እ.ኤ.አ ነበር። ያን ጊዜ ባለቤቷ በወቅቱ በነበረው የፖለቲካ ትኩሳት ምክንያት በሱዳን በኩል ከሃገር ወጥቶ አሜሪካ ከጓደኞቹ የገባበት ጊዜ ነበር። እሷ ግን እንደባለቤቷ ስደትን ሳትቀምስ ቀጥታ አሜሪካ ደረሰች።

ኢትዮጵያ እያለች አስተማሪ የነበረችው የዛሬዋ “ሕይወት በሚኒሶታ” አምድ እንግዳችን አሜሪካን ጋር እንደመጣች ለአንድ ለሁለት ዓመት ብቻ ተቀጥራ የራሷን ሥራ ፈጥራ መሥራት እንደጀመረች አውግታናለች። ብዙዎች ለሚኔሶታ ነጋዴዎች በተለይ ሴቶች አርአያ ናት የሚሏትና ያሰበችበት ለመድረስ እንቅልፏን የማትተኛዋን እንዬ ፋንታ የዛሬዋ እንግዳችን አድርገን በግል ሕይወቷና በንግድ ሥራዋ ዙሪያ አነጋግረናታል። እንዬ ባለትዳርና የ4 ልጆች እናት ናት።

ዘ-ሐበሻ፦ እንዬ ሃበሻ እዚህ ስቴት ውስጥ ብዙ ባልነበረበት ወቅት እንዴት የራስሽን ቢዝነስ ለማቋቋም ተነሳሳሽ?

እንዬ፦ ቤተሰብ ስትመሠርት ልጆች ምናምን ይመጣሉ። እዚህ ሃገር ልጆች ለማሳደግ እጅግ ከባድ ነው። ቤተሰብህን እንደልብ ማምጣት አትችልም፣ በወቅቱ ሥራ ተቀጥረህ የምትሰራው በ3.50 ዶላር ነው ስለዚህ የልጅ መጠበቂያ ዋጋውም በጣም ውድ ነው፣ በዛ ላይ የልጅ ጠባቂ እጥረት በጣም ስላለ ግዴታ ልጆቻችንን ቤት ለማሳደግ ተገደድን። በወቅቱ ባለቤቴ ታክሲ ይነዳ ነበር። እኔ ቤት ከልጆች ጋር ተቀምጬ ስውል ባለቤቴን ለምን አላግዘውም በሚል ልጆች እየጠበኩኝ ሥራ ፈጠርኩኝ። በወቅቱ ያለነው ሃበሾች ትንሽ ብንሆንም የበርበሬና የእንጀራ ፍላጎት እንዳለ በመረዳት ስፖንሰሬ ነጭ ስለነበር እሱን በማነጋገር እሱም ረድቶኝ በርበሬውን እቤት አዘጋጅቼ እሱ እያስፈጨልኝ በየአፓርትመንቱ ቤት ለቤት የተዘጋጀ በርበሬ መሸጥ ጀመርን። ቢዝነሱን እየለመድኩ ስመጣም ለቤት እንጀራ መጋገር ጀምሬ እሱን ለመብላት እቤቴ ብዙ ሰዎች እንጀራ ለመብላት ይመጡ ነበር። እንጀራ ሰው እንደሚሰስብ የተረዳሁትም ያኔ ነው። ሰዎች እንጀራዬን እንደዚህ የሚወዱት ከሆነ ለምን ገበያ ላይ አላወጣውም አልኩና ጀመርኩት።

ዘ-ሐበሻ፦ ይህን የእንጀራ ቢዝነስ ስትጀምሪ የሕዝቡ ምላሽ ምን ነበር?

እንዬ፦ አብዛኛው ሰው ደስተኛ ነበር። ግን አንዳንድ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎች ነበሩ። አንዳንዶች ስሜን እንኳ አይጠሩትም “ያቺ እንጀራ ሻጯ” ነበር የሚሉኝ። አንዳንዶቹ “እንዴት አሜሪካንን የሚያህል ሃገር መጥተሽ እንዴት እንጀራ ትሸጫለሽ” እያሉ ይወቅሱኝ ነበር። እንደውም ለቤተሰቦቼ ኢትዮጵያ ደውለው “እሷ እኮ አሜሪካ ውስጥ እንጀራ ነው የምትሸጠው እያሉ” ሊያቃልሉኝ ሞክረው ነበር።

ሌላው እንጀራውን እና በርበሬውን በሱቅ ለምን አልጀምረውም ብዬ በመነሳት ሎኬሽን ሳላውቅ ወደ ኖርዝ ኢስት (በጣም ዘረኛ ሕዝብ በነበረበት) አካባቢ ነበር የከፈትኩት። የሱቁ ቢዝነስ አልሆን አለ፤ ምንም አጣሁኝ። ከዛ ሲደር አካባቢ መርካቶ የሚባል ሱቅ ከፍቼ ውጤታማ ልሆን ቻልኩ። ሱቁ ውጤታማ ሲሆን ባለቤቴም ታክሲ ዎቹን በመሸጥ ሥራውን ትቶ አብረን መሥራት ጀመርን።

ዘ-ሐበሻ፦ በሚኒሶታ የመጀመሪያዋ ነጋዴ ነሽ ማለት ይቻላል?

እንዬ፦ አዎ!

ዘ-ሐበሻ፦በምን ያህል ካፒታል ነበር ሥራ የጀመርሽው?

እንዬ፦ ያን ጊዜ ቢዝነስ የጀመርነው 1 ታክሲ ተሸጦ ነው። የአንድ ታክሲ ዋጋ ወደ 22 ሺህ ዶላር ነበር። በዛ ብር ላይ ከጓደኞቼ ብር ጨምሬ ቤቱን ተከራይተን ነው ስራውን የጀመርነው።

በሚኒሶታ የመጀመሪያውን “መርካቶ” የሃበሻ ሱቅ እና “መርካቶ” እንጀራን የጀመረችው እንዬ “ከድሮው እና ከአሁኑ የአሜሪካንን ኑሮ ስታነጻጽሪው የትኛው የተሻለ ነው ትያለሽ?” ብለናት ነበር። እንዬ የአሁኑ ጊዜ ጥሩ እንደሆነ ትናገራለች። “አሁን እንጀራ የሚጋግር ሰው እንደ አሸን የፈላው ቢዝነሱ ስላለ ነው። የዛን ጊዜ እንጀራ የሚጋግር ለማግኘት ከባድ ነበር። ሕዝቡን ስለበዛ ቢዝነስ ለመከፈትም ያሁኑ ጊዜ ቆንጆ ነው። የልጅ ጠባቂ ችግርም ብዙ የለም” ትላለች። ወደ ቃለ ምልልሳችን እንመለስ፦

ዘ-ሐበሻ፦ በሚኒሶታ የመጀመሪያው እንጀራ ያንቺ “መርካቶ” እንደሆነ ነው ያጫወትሽኝ። እንጀራውን እንዴት ነበር የምትጋግሩት?

እንዬ፦ ጤፍ እንደልብ ስለማናገኝ የምንጋግረው ሚለት ፍላወር ነው። ሚለት ገብስ እና ስልፍራይዚንግ አንድ ላይ ቀላቅለን ነበር የምንጋግረው። ከዛ በኋላ ግን እየቆየን ስናውቀው ጤፍ ከኢዳሆና ከሚቺጋን በስፖንሰሬ አማካኝነት ሳገኝ ጤፍ እየቀላቀልን መጋገር ጀመርን። በዚህ ስቴትም ከ1992 እስከ 2005 ድረስ እንጀራ በስፋት እናቀርብ ነበር።

ዘ-ሐበሻ፦ በአሁኑ ሰዓት ሲደር ላይ ያለውን መርካቶ ስቶር ለሶማሌዎች ሸጠሽዋል፤ በምን ዓይነት ንግድ ላይ ተሰማርተሻል?

እንዬ፦ እንግዲህ በፊት ሲደር አካባቢ ብዙ ሃበሾች ስለነበሩ፤ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሚኒሶታም ቅርብ ስለነበር የመርካቶ ሱቅ ገበያም ጥሩ ነበር። ሀበሻም አዲስ ሲመጣ ሃበሻ ያለበትን ፈልጎ ስለሚኖር ድሮ ሲደር መሰባሰቢያችን ነበር። አሁን ግን ሶማሌዎች ቦታውን በብዛት እየገቡበት ሃበሻውም እየለቀቀ ሲመጣ የሱቄ ገበያ ቀዘቀዘ። በዛ ላይ የሶማሌ ሱቆች የኢትዮጵያን

እቃዎች ስለሚይዙም ለገበያው መቀዝቀዝ ምክንያት ሲሆን መርካቶን ለሱማሌዎች ሸጥኩላቸው። ስሙን መጠቀም ፈልገው ነበር እኔ ግን አይሆንም ብዬ ስሙን ለወንድሜ ሰጥቼው ዩኒቨርሲቲ አቬንዩ ላይ ሱቅ ከፈተበት። እነርሱ አፍሪክ ግሮሰሪ ብለው እየሰሩበት ነው። ሊከር ስቶራ ችን ግን እግዚአብሄር ይመስገን ጥሩ እየተንቀሳቀሰ ነው።

ዘ-ሐበሻ፦ በፊት የኢለመንተሪ ት/ቤት አስተማሪ እንደነበርሽ ሰምቻለሁ። አስተማሪነትሽ አሁን ላለሽበት የቢዝነስ እንቅስቃሴ የረዳሽ ነገር አለ?

እንዬ፦ አይመስለኝም። አስተማሪና ቢዝነስ እጅግ የተለያዩ ነገሮች ናቸው። እንደው እግዚአብሄር እዚህ ስመጣ ብልሃቱን ሰጠኝ እንጂ አንዳንድ ጊዜ እንደውም ድሮ ያለ ፊልዴ ነው አስተማሪ የሆንኩት ማለት ጀምሬያለሁ። በልጆች ማሳደግ የተነሳ የቢዝነስ እውቀቴን ለማሳደግ ባልችልም የበለጠ ባጠና ስኬታማ እሆን ነበር ብዬ አስባለሁ።

ዘ-ሐበሻ፦ ውጤታማ ሆነሽማ የተለያዩ ሽልማቶችን እንደገኘሽ ሰምቻለሁ።

እንዬ፦ (ሳቅ) ያገኘሁት ሽልማት እንደምታየው ይህን አካባቢ አሳምረነዋል። ሕንጻም ስለሰራንበት በዚህ የተነሳ አካባቢው ስላደገ በጥረታቸው የዚህን አካባቢ ኮምዩኒቲ ጥሩ እርዳታ የሚያደርጉ ናቸው በሚል ነው የኮምዪኒቲ ዴቨሎፕመንት ከአንድም ሁለት ጊዜ ሽልማት ያገኘነው።

ዘ-ሐበሻ፦ “እንዬ ያሰበችውን ካላሳካች እንቅልፍ አይወስዳትም” ይላሉ ብዙ ሰዎች። እንግዲህ ጠንካራነት ሽን እየገለጹ ነው። የወደፊት እቅድሽ ምንድን ነው?

እንዬ፦ አሁን የመሥሪያዬ ጊዜ ነው ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ልጆቼም ኮሌጅ ገብተዋል፤ የጨረሱትም ጨርሰዋል። አሁን ከባለቤቴ ጋር በመሆን ሰፊ እንቅስቃሴ ለማድረግ ተነሳስተናል። እንደምታየው ባሁኑ ወቅት ብዙ የቢዝነስ ውድድር አለና በዚያ ውስጥ ገብተን የውድድሩ አካል መሆን እንፈልጋለን። ከኢትዮጵያ የሚመጡ ምርቶች ላይ በሰፊው ማተኮር እንፈልጋለን። ለምሳሌ ቡና ለማከፋፈል በጅማሮ ላይ ነኝ። በአሁኑ ወቅት የሃገር ቤት ቢራዎችንና ወይኖችን እያከፋፈልኩኝ ነው። ይህንንም በስፋት ማብዛት እፈልጋለሁ። እንደውም የሃገራችንን መጠጦች ለማስተዋወቅ የዓለም አቀፍ ቢራዎችን ወደ ሚሸጡ ስቶሮች ሁሉ ለማስገባት እየተነጋገርን ነው። ሌላው አሁን ባለው ሕንጻችን ጀርባ የዳቦና ኬክ መጋገሪያ ለመክፈት ቅድመ ሁኔታዎች ተጠናቀዋል። እስካሁንም የቆየሁት እኛ ሕንጻ ላይ ብዙ ቢዝነሶች ስላሉ የሾፒንግ ሞል ፍቃድ አውጪ ብሎ መንግስት ስላስቸገረኝ ለ3 ወር ያህል እየተንገላታሁኝ ነው። እሱ ካለቀ ዳቦና ኬክ ቤት ለመክፈት ሁሉ ነገር ዝግጁ ነው።

ዘ-ሐበሻ፦ በዚህ አጋጣሚ ይህንን ያንቺን ቃለ-ምልልስ ለሚያነቡ የሚኒሶታ ነጋዴዎች የምታስተላልፊው መልዕክት ምንድን ነው?

እንዬ፦ ጥሩ ጥያቄ ነው። በዚህ አጋጣሚ የምለው ነገር ቢዝነሶች መብዛታቸው ጥሩ ነው። ሁላችንም ስንወዳደርና ሁሉም ሲሰራና ሲያድግ ለእድገታችን መሠረት ነው። ተሰደን እስከመጣን ድረስ ሁላችንም ስኬታማ ብንሆን በጣም ደስ ይላልና በርትታችሁ ሥሩ ነው የምለው። ቢዝነስ ቀዘቀዘ ከሰርኩ ብሎ ከማማረር ቀድሞውኑ ሁለት ወይም 3 ዓይነት ቢዝነሶችን መጀመር፤ በአንዱ ስትከስር በሌላኛው ታገኘዋለህ። ሃበሻ ሁሉም ጠንካራ ሠራተኛ በመሆኑ ይህ ይጠፋዋል ብዬ ባላስብም ብልሃተና እንሁን እላለሁ።

እንዬ ጎንደር ትወለድ እንጂ ያደገችው ደብረብርሃን አካባቢ ነው። ከዛም አባቷ በሥራ ምክንያት አዲስ አበባ ሲመጣ አዲስ አበባም ረዥም ጊዜ ተቀምጣለች። ከርሷ ጋር የነበረን ቆይታ እዚሁ ላይ አበቃ።µ

Source: ZeHabesha Newspaper