እብሪት በሃይማኖት

ከኮስትር ጎንደሬው

እኔ መላው ቢጠፋኝ እስቲ እናንተ መላ ምቱ ለማለት ነው ይህቺን ትንሽ ቋጠሮ ብጤ ከዚህ ድረ ገጽ ላይ ለማውጣት ማሰቤ:: እንዲያው እንደ ጤነኛ ከላያችን ጣል ካደረግነው ጨርቅ ሌላ የቱ ድርጊታችን ጤነኛ እንደሚያሰኘን አልታይህ ቢለኝ ካዋቂም አዋቂ አለውና ዘመድ ወዳጅ ቢያመላክተኝ ብዬ ነው::

አገራችን ኢትዮጵያ እኛም ኢትዮጵያውያን ነን:: ያንን ያህል መቼም እንስማማለን ብዬ አምናለሁ:: መስማሚያ ነጥባችን ግን እዚህ ላይ ይቆማል ብል ላመል ያህል ትንሽ ታንገራግሩ እንደሁ እንጂ አክርራችሁ የምትጣሉኝ አይመስለኝም:: ስምምነትማ እናቱ ሞተች! ሰነበተች!

የ 1997ቱ ምርጫ ላይ ተባላን: ተጋደልን። ጥቂት የማይባሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ደም ፈሰሰ። ዘረኞች፡ ጎጠኞች፡ አምባገነኖች ምርጫችንን ሰረቁን ብለን አንጎራጎርን። ከዚያኔው ልምዳችን ላይ የመሪዎቻችን ክህደትና የስልጣን ጥም ታክሎበት የማያዳግም ትምህርት አገኝን መሰለኝ ለ2002ቱ ምርጫ ቀጥ ሰጠ ብለን እጅ ሰጥተን ገባን።

ታዲያ ከዚህ ለዳግም ሽንፈት ከተዳረግንበት ምርጫ በርግጥ አንዳንድ ወግኖች ትምህርት አግኝተውበተል: ምንም ትምህርቱ ለበጎ ባይውልም:: ዘመዶቼ: ሌላ አይደለም:: የተገኘው ትምህርት “ሥልጣን ወይም ሞት” በሚል በዚህ ባሜሪካን አገር በሚገኙ የኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያናት የቦርድ አባላትና በተለይም ሊቀመናብርት የስልጣን አንለቅም ግብግብ ነው:: ያው ከማን አንሼ ነውና: ልክ ከጌቶቻቸው እንደ ቀሰሙት ትምህርት ግሱን ግሳንግሱን ሰብስበው በማስጮህና በማስጨብጨብ የብዙሐኑን ድምፅ ማፈንና መንጠቅ ነው::

“ሌባ ላመሉ ዳቦ ይልሳል” እንዳልል ሥልጣኑ የተፈለገው ላመል ለመከበሪያነት ብቻ አልመስልህ አለኝ። ታዲያ አምላኬን: ሃይማኖቴን አገለግላለሁ ላለ ክርስቲያን ከሥልጣን አልወርድምን ምን አመጣው? ሥልጣኑን ሲያጣ አብሮ የሚያጣው ነገር ከሌለ በቀር? ስኳር ለመድኩ አሉ ታምራት ላይኔ!! እሳቸውስ ነፍሳቸውን ሊያድኑ ጴንጤ ሆኑ አሉ:: የኛዎቹስ ምን ሊሆኑ ይሆን?

ይህን ሁሉ ያነሳሁት ያለ ምክንያት አይደለም። ይሄ ተዚያ ሳይባል በዋሽንግተን ዲሲና በሌላውም አካባቢ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ተመራጮች በሙሉ ሥልጣንን የሙጢኝ ብለው ቀርተዋል። በዋሽንግተን ዲሲ ከብላደንስበርግ መንገድ ኖርዝ ኢስት ወጣ ብሎ የሚገኘውን ቅዱስ ገብርእል ካቴድራል በምሳሌነት እንየው።

የዚህ ቤተክርስቲያን የሥራ አመራር (ቦርድ) አባላት የሆኑ ወገኖቼ: በኔም ጠንካራ ድጋፍ ጭምር ለቦርድ አባልነት ከተመረጡ ይሄውና ከአስርት አመታት በላይ ተቆጠሩ:: በዚህ ሂደት ውስጥ ከተነሱበት የአገልጋይ ተመራጭ ባለስልጣንነት በተለይ ሊቀመንበሩ ወደ አምባገነናዊ ሥልጣን ሰጪነት እርከን ዘለል ዕድገት አድርገዋል:: ሁሉም ናቸው ባይባልም አብዛኛዎቹ የቦርድ አባላት ከሀገራቸው የተሰደዱበት ምከንያት ፖለቲካዊ ነው ቢባል ብዙም ከእውነት የራቀ አይሆንም። ታዲያ የዲሞክራሲን ድንቅ መዐዛ አነፍንፎ ካገሩ የተሰደደ ሕዝብ በተሰደደበት አገር በተራው አምባገነንነት አመራርን ማስፈኑ ፍቺ የማይገኝለት ቅዠት ሆኖ ታየኝ። ዲሞክራሲ መጀመር ያለበት ከራስ ነውና።

እዚህ ቤትማ ሁኔታው ከሌላው በጣም ሳይለይ አይቀርም። የቦርድ አባላቱ በሙሉ በቦታው የተሰየሙት ያለሕዝብ እውቅና በቦርድ ሊቀመንበሩ በራሳቸው ምርጫ ብቻ መሆኑ በአይነቱ የመጀመሪያው ይሆናል ብዬ አስባለሁ። እንደ አጼ ሃይለሥላሴ ስዩመ እግዚአብሔርነትን አግኝተው ይሆን? ይህ እንዴት ሆነ ልትሉኝም አይደል? እንዲህ ነው። የተማረሩ ተመራጭ የቦርድ አባላት እየጣሉ በሄዱ ቁጥር በቦታቸው ያገር ልጆችና ሌሎች አቧራ የማያስነሱ ለዘብተኞች በወረንጦ ተለቅመው ተሰገሰጉበት:: ማን አለብኝነትን ለማያውቀው ይሄ ትክክለኛ መገለጫ ባሕሪው ነው ቢባል ጭራሽ የሚያከራክር አይሆንም::

ከመነሻው ምርጫውን ስናካሂድ ሊቀመንበር የሆኑት ግለሰብ በጊዜው የራሳቸው የተለየ ስውር አጀንዳ ይኖራቸው እንደሁ አላውቅም:: በእርግጠኝነት ግን ተመራጮቹ ጥሩ የሕዝብ አገልጋይ ክርስቲያኖች እንጂ ወደ መጥፎ የቱርክ ገዢነት ሊለወጡ ይችላሉ ተብለው ያልታሰቡና ብሔራዊ ስብጥርም ያላቸው ነበሩ::

ነገር ከጅምሩ ነውና ትንሽ ከመንገድ ወጣ ላድርጋችሁ:: ነገሩ እያደር እየከረፋኝ ሲመጣ፡ እኔም እንደ ቀደሙት የቦርድ አባላት የሽሽት ጎራውን ከተቀላቀልኩ ያለፈው ታህሳስ ገብርኤል ሁለት ዐመት አስቆጠርኩ። ታዲያ አሁን ተስፋ የቆረጥኩበት ምዕመን መብቱን ለማስከበር ጥያቄ እየጠየቀ እንደሆነ ስሰማ ወትሮም የሽሽቴ ጉዳይ የእግር ውስጥ እሳት ሆኖብኝ ነበርና፡ አምባገነንነትን ለማጥፋት ተመልሼ መጣሁ። ማንም ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን የሆነ ሁሉ የዚህ ቤተ ክርስቲያን አባልም ባይሆን ይህንን የሥልጣን በሽታ ባለበት ቦታ ሁሉ በሕብረት ሊዋጋው ይገባል።

ተኝተዋል ተብለው የተናቁት ምእመናን በሙሉ ነቁና ስለነሱ ዘላለማዊ የስልጣን ዘመንና ለመረጣቸው ሕዝብ ያላቸውን ተጠያቂነት (አካውንተቢሊቲ) መጠየቅ ጀመሩ።

አምባገነን ምን ጀግና ቢሆን መደንገጡ አየቀርምና፤ ነገሩ ከከረረ መመለሻ እንደሌለው ስለሚያውቁ: ለወዳጅ ዘመድ የተለመደ የድረሱልኝ ጥሪ ቀለጠ:: ጥሪው እኔን ዘሎኛል:: ምንም ካንድ ክፍለሀገር ብንመጣም የኔ መነሻዬ እነሱ ከመጡበት ፈንጠር ሰለሚል ተዐማኒነት ያገኘሁ አልመሰለኝም:: ከያ አካባቢ ያለው ድጋፍ እንዳይከፋፈልባቸው በማስብም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጠባብ ብሄረተኝነታቸውን ወደ ጎጠኝነት ደረጃ ዝቅ አድርገውታል:: ላይና ታች ብለው አንዱን አገር ከመሃል ከፈሉት፡ ሸነሸኑት:: ወንድማማቾቹን ሆድና ጀርባ አደረጉን!! ያልተቀደሰ ጥሪያቸው እንኳንም ቀረብኝ፡ እሰየው!

መንግሥት በሥልጠኑ ነውና ክተት ሠራዊት ታወጀ በየወገን ቤቱ ማታማታ የስልክ ጥሪ ተጧጧፈ: ባንዳንድ ተጠርጣሪ አንቀሳቃሾች ላይ መጠነ ሰፊ የስም ማጥፋት ዘመቻ ያለገደብ ተለቀቀ:: መክት! ውጋ! ንቀል! ወድር! ያፄ ፋሲል አገር የቴዎድሮስ አገር ተባለ:: ለአንድ ኢትዮጵያ እራሱን የሰዋው ቴዎድሮስ ይሄኔ ስንተዬ ዐፅሙ በመቃበሩ ውስጥ ተገላብጦ ይሆን?

ለድንገቱ ሌላም ስልት ተቀይሷል:: ምናልበት ምዕመኑ አንዴ ዐይኑን ከፍቷልና እነዚህን አምባገነኖች ዐይናችሁን ላፈር ያለ እንደሁ ተብሎም ሌሎች ያካባቢው ተወላጅ ተወዳዳሪዎችም ተዘጋጅተዋል። አላወቀውም እንጂ ግብረሃይሉ መሸ ነጋ እያለ በየአበሻው ሬስቶራንት ከትፎውን እየሰለቀጠ ሲዶልት አጠገቡ ቁጭ ብለን የፈሪሳውያን እንውገረው ምክሩን ተቋድሰንበታል:: እኛም አውቀናል ጉድጓድ ምሰናል ነውና ነገሩ።

ይህን ማውጋቴ ለአስር ዐመታት ሙሉ ከፈፀምኩት የዝምታ ተባባሪነት ወንጀል እራሴን ነፃ ለማውጣት ሳይሆን በጥቂት ጥቅም አጋባሾች በተቀደደው አደገኛ የጎጠኝነት ቁልቁለት እንዳንወርድ ለማስጠንቀቅ ነው። ለመብታችን እንታገል!! ክርስቲናዊ ሕይወት የዕብሪት መንገድ ሊሆን አይገባውም። ያእግዚአብሔር መንገድ የፍቅር ጎዳና እንጂ የግለሰብ የሥልጣን መገለጫ አይሆንም።
(ጸሀፊውን በዚህ ኢሜይል አድራሻ ማግኘት ይቻላል፤ [email protected])