”ቅንድቡ ያማረው” (መክብብ ማሞ)

መክብብ ማሞ [email protected]

ሳፓርሙራት ኒያዞቭ ይባላሉ። ቱርክሜኒስታንን ለሁለት ዓስርተ ዓመታት ያህል አስተዳድረዋል – ገዝተዋል ቢባል የሚቀል ይመስለኛል። አነሳሳቸው ከዝቅተኛ ቤተሰብ ነው። አባታቸው ናዚ ጀርመንን ሲዋጉ እንደሞቱ ይነገራል። ሌሎቹ ቤተሰቦቻቸው ደግሞ በመሬት መንቀጥቀጥ ስለሞቱ ወላጅ አልባ ነው ሆነው ያደጉት። ብዙም ሳይቆይ ግን አገራቸው የሶቪዬት አንድኛዋ ክልል በነበረችበት ወቅት የኮሙኒስት ፓርቲው አባል በመሆን የቱርክሜን ኮሙኒስት ፓርቲ ዋና ጸሃፊ ሆነው ለዓመታት ሠርተዋል። በሶቪዬት ኅብረት ኮሙኒስታዊ አገዛዝ መለኪያ እንኳን ፓርቲያቸው ፈጽሞ ተሃድሶን የማያውቅ አምባገነናዊ እንደነበር ይነገራል።