በግብፅ 5 ኢትዮጵያውያን ታሰሩ

የግብፅ ፖሊስ በሲና በረሀ በኩል ድንበር አቋርጠው እስራኤል ለመግባት የሞከሩ አምስት ኢትዮጵያውያንን መያዙን አስታወቀ ። ፖሊስ እንዳለው እነዚህኑ ሶሶት ወንዶችና ሁለት ሴቶች ትናንት ኤል አሪሽ ውስጥ በማስጠንቀቂያ ተኩስ አስቁሞ ከያዛቸው በኃላ አስሯቸዋል ። የተያዙት ኢትዮጵያውያን እስራኤል እንደሚያስገቡዋቸው ቃል ለገቡላቸው ድንበር አሻጋሪዎች እያንዳንዳቸው አንድ ሺህ ዶላር መክፈላቸውን ተናግረዋል ። አምስቱ ኢትዮጵያውያን በአሁኑ ሰዓት ኤል-አሪሽ እስር ቤት የታያዙ ሲሆን ፣ ጉዳያቸውንም በግብፅ የኢትዮጵያ ኤምባሲ እንዲያውቀው መደረጉን የጀርመን ዜና አገልግሎት DPA ዘገባ ያስረዳል ። በተለያዩ ጊዜያት በተመሳሳይ ሁኔታ በግብፅ ድንበር በኩል ወደ እስራኤል ለመሻገር ከሞክሩ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን አብዛኛዎቹ ፖሊስ እየተኮሰባቸው ተገድለዋል ። በቅርቡ ደግሞ ከአሸጋሪዎቻቸው ጋር በክፍያ የተጋጩ የስምንት ስደተኞች ህይወት ማለፉ ይታወሳል ።