ሕዝብን የሚያዳምጥ መንግሥት፤ መንግሥትን የሚያዳምጥ ሕዝብ!! ዲ/ን ዳንኤል ክብረት

ሀገር ሰላም እንድትሆን፤ ሰላም ሆናም በብልጽና ጎዳና እንድትራመድ ከተፈለገ ሁለት ነገሮች ያስፈልጓታል፡፡ ሕዝብን የሚያዳምጥ መንግሥትና መንግሥትን የሚያዳምጥ ሕዝብ፡፡ ማዳመጥ ከመስማት ይለያል፡፡ መስማት ጆሮ ለተፈጠረለት ሁሉ የሚቻል ነው፡፡ ይህን ጽሑፍ ስናነብ እንኳን ስንትና ስንት ድምጾችን ፈልገንም ሳንፈልግም እንሰማለን፡፡ ማዳመጥ ግን ሦስት ነገሮችን ይፈልጋል፡፡ ይሁነኝ ብሎ መስማት፣ ሰምቶ ማስተዋል፣ አስተውሎም መመለስ፡፡
ሕዝብን የሚያዳምጥ መንግሥት ስንልም ይሁነኝ ብሎ ሕዝቡን የሚሰማ፣ ሰምቶ ሕዝቡ ምን እንዳለው የሚያስተውልና ከዚያም አስተውሎ መልስ የሚሰጥ መንግሥት ማለት ነው፡፡ ለሕዝብ የመናገር ነጻነት ብቻውን ምንም አያደርግለትም፡፡ የመደመጥ መብት ከሌለው በቀር፡፡ ሰሚ ከሌለ እንኳን ሕዝብ ፈጣሪ አይናገርም፡፡ ቢናገርም ጥቅም የለውም፡፡ ለዚህም ነው ሊቃውንቱ እንደሚነግሩን፤መላእክት እስኪፈጠሩ ድረስ ፈጣሪ ፍጥረታትን በአርምሞ ብቻ የፈጠረው፡፡ ለምን? ቢሉ ሰሚ ሳይኖር መናገር ምን ያደርጋል ብሎ። መላእክት ከተፈጠሩ በኋላ ግን ‹ብርሃን ይሁን› ብሎ ሲናገር እንሰማዋለን፡፡ አሁን ሰሚ ተገኝቷልና መናገር ዋጋ አለው፡፡
ሕዝብም መናገሩ ብቻ ጥቅም የለውም፡፡ የተናገረውን የሚያዳምጠው መንግሥት ያስፈልገዋል፡፡ ሕዝብ የሚያዳምጠው ሲያጣ፣ ጩኸቱን የሚያዳምጠው አጥቶ ቤቱ እንደተዘረፈበት ውሻ ‹ነባይነ ነባይነ ከመዘኢ ነባይነ ኮነ – ጩኸን ጩኸን እንዳልጮኽን ሆን› ብሎ አይቀመጥም፡፡ ራሱን በራሱ ማዳመጥ ይጀምራል፡፡
የልቤን መከፋት ሆዴ እያዳመጠ
ሊመረው ነው መሰል ነገር አላመጠ
— የሚል የቆለኛ ፉከራ አለ፡፡ ሰውዬው በልቡ መከፋቱን ለሰው ቢናገር ቢናገር የሚሰማው አጣ፡፡ እርሱ ሰሚ ሲያጣ ሆዱ ግን የልቡን መከፋት እየሰማ ይቃጠል ጀመር፡፡ በኋላም ሆዱ እየቆረጠ ሲሄድ ጊዜ ነው ይህንን የፎከረው፡፡ ሕዝብ ራሱን ማዳመጥ ሲጀምር፤ ‹ሊመረው ነው መሰል› የሚለው ፉከራ ላይ እየደረሰ ነው ማለት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ የሚሆነውን ለመገመት አስቸጋሪ ነው፡፡ ሕዝብን በርእዮተ ዓለም፣ በሐሳብና በአመለካከት አንድ ለማድረግ እጅግ ጽኑ ትግል፣ እጅግ ብርቱ ጥረት፣ እጅግ ብዙ ልፋት ይጠይቃል፡፡ ሕዝብን በቀላሉ የሚያስተባብረው አንድ ነገር ነው፡፡ መጠቃት ወይም መገፋት፡፡ ያን ጊዜ ወዲያ ማዶ ሆኖ አንዱ የተጣራውን፣ ወዲህ ማዶ ሆኖ ሌላው ይሰማዋል፡፡
እዚያ ማዶ ሆኖ አንድ ሰው ተጣራ
እዚህ ማዶ ሆኖ ሌላ ሰው ወይ አለው
ጎበዝ ተነቃቃ ይህ ነገር ለኛ ነው
—- ማለት የሚችለው የሚያዳምጥ መንግሥት ካለ ብቻ ነው፡፡
መንግሥት ሕዝብን ይሁነኝ ብሎ ማዳመጥ አለበት። አንዳንድ ጊዜ ሕዝብ የተናገረው ላይደርሰው ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሕዝብ ያልተናገረውን ሊሰማ ይችላል፡፡ ሕዝብ የተናገረው ለመንግሥት ካልደረሰው ወይም ሕዝብ ያልተናገረውን መንግሥት ከሰማ፣ እወደድ ባዮች ለመንግሥት የሚያስፈልገውን ትተው መንግሥት የሚፈልገውን ብቻ ይነግሩታል ማለት ነው፡፡ ሕዝብ ብዛት ብቻ አይደለም ያለው። ውጥንቅጥም ነው፡፡ በእምነት፣ በርእዮተ ዓለም፣ በመፍትሔ አቅጣጫ፣ በባህልና ቋንቋ፣ በዕውቀትና ሥልጣኔ፣ በዕድሜና ጾታ የተወነቀጠ ነው – ሕዝብ፡፡ ሕዝብን ማዳመጥ ማለት እነዚህን ሁሉ በየመልካቸው ማዳመጥ ማለት ነው፡፡ ሕዝብ ውስጥ መንግሥትን የሚወዱና የሚደግፉ፣ መንግሥትን የሚጠሉና የሚቃወሙም አሉ፡፡ ሕዝብን ማዳመጥ ማለት እነዚህን በየመልካቸው ማዳመጥ ማለት ነው፡፡
ሕዝቡ ይህንን ሲል ምን ማለቱ ነው? ለምን እንዲህ አለ? ምን ስለሠራሁ ወይም ምን ስላልሠራሁ ነው? የትኛውን ችግሬን ስፈታው የሕዝቡ ጥያቄ ይመለሳል? ብሎ ማስተዋል ነው ሕዝብን ማዳመጥ ማለት፡፡ ሕዝቡ ስላልገባው ነው? ስላልተረዳ ነው? ስላልተማረ ነው? ስላልሠለጠነ ነው? እያሉ ጠያቂውን የችግሩ መነሻ ማድረግ፣ ሕዝብን ያለመስማት ዋናው መገለጫው ነው፡፡ ‹ደንበኛ ንጉሥ ነው› እያልን ‹ሕዝብ ንጉሥ ነው› የሚለውን እንዴት መቀበል ያቅተናል? ‹ደንበኛ አይሳሳትም› እያልን ‹ሕዝብ አይሳሳትም› የሚለውን እንዴት ማመን ይሳነናል?
በደርግ ጊዜ አንድ የገጠር ሕዝብ ያምጻል፡፡ መሬት ሲከፋፈል የመሬት ኮሚቴዎች በጉቦ አስቸገሩት፡-
ከዛፍ ወደ ዛፍ ላይ ትዘላለች ጦጣ
መሬትን ያገኘ ኮሚቴን ያጠጣ
ብሎ ዘፈነ፡፡ የሰማው ግን አልነበረም፡፡ ትንሽ ቆይቶ የመንደር ምሥረታ ተባለና የኖረበትን ቀዬ ልቀቅ ተባለ፡፡
ቤቱን አፍርሱ አሉን የበላንበትን
ማፍረስስ አልጋውን ትኋን ያለበትን
ብሎ ዘፈነ፡፡ የሰማው ግን አልነበረም፡፡ ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ልጆችህ ይዝመቱ ተብሎ ወታደር ተመራበት፡፡
ልጅህን አምጣ ይላል የኛ ዘመናይ
እኔ ልጄን ስወልድ አዋልዶኛል ወይ
ብሎ ገጠመ፡፡ የሰማው ግን አልነበረም። በመጨረሻም ከእንግዲህ ደርግ ጠላታችን ነው፡፡ ለጠላታችን ለደርግ አንገዛም ብሎ ተማማለ፡፡ ነገሩ እየከረረ መሄዱን የሰሙ ካድሬዎች ወረዱና ሕዝቡን ሰበሰቡት፡፡ ሲነግሩት ዋሉ፡፡ ሲሰማቸው ግን አልዋለም። ስብሰባው ሲያልቅ፤ ‹ጠላቶቻችን ይውደሙ› ብሎ ካድሬው መፈከር አሰማ፡፡ ሕዝቡም በአንድ ድምጽ እጁን አውጥቶ ‹ይውደሙ› አለ፡፡ ካድሬዎቹም ደስ ብሏቸው ስብሰባውን በመፈክር አሳርገው ሄዱ። ለአለቆቻቸው ሕዝቡን አሳምነው እንዳስፎከሩት ተናገሩ፡፡ ሕዝቡ ያለው ሌላ እነርሱ ያዳመጡት ሌላ፡፡
ሕዝብን ማዳመጥ ማለት ሕዝብ የሚለውን ለማዳመጥ መቻል ነው፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቅኔ ሕዝብ ነውና ሕዝቡን ለማዳመጥ ባለቅኔ መንግሥት ያስፈልገዋል፡፡
ሕዝብን የሚያዳምጥ መንግሥት ማዳመጡን በሚሰጠው ምላሽ ነው የሚገልጠው፡፡ ምላሹ የሚወሰነው ለማዳመጥ በሰጠው ማስተዋል ነው። የመጣው ከዚህና ከዚያ፣ ከነእንቶኔና ከነእንትና ነው ማለቱን ትቶ፣ ሕዝብ ተናግሯል ብሎ የሚያምን ከሆነ፣ያንንም ይዞ ከየዓይነቱ ሕዝብ ጋር የሚመክር ከሆነ፣ መክሮም መንግሥት የሚፈልገውን ሳይሆን ሕዝቡ የጠየቀውን የሚመልስ ከሆነ፣ ያ መንግሥት ‹ሕዝብን የሚሰማ መንግሥት› ይባላል፡፡
ሕዝብን የሚሰማ መንግሥት፣ መንግሥትን የሚሰማ ሕዝብ መፍጠር ይችላል፡፡ ሕዝብ የሚያከብረውን፣ የሚወደውንና ይሰማኛል ብሎ የሚያምነውን መንግሥት ይሰማል፡፡ መደማመጥ የጋራ ነው፡፡ ሕዝብ ፈጣሪው የሚለውን የሚሰማውኮ ፈጣሪዬ የምለውን ይሰማኛል ብሎ ስለሚያምን ነው፡፡ ፈጣሪ አይሰማኝም ካለማ ፈጣሪውን መስማት ያቆማል። ማንም የማያዳምጠውን አያዳምጥም፡፡ ፈጣሪም ‹ኑ እንዋቀስ› ያለው የሚወቀስ ነገር ኖሮት ሳይሆን ሕዝቡን እንደሚያዳምጥ ሲናገር ነው፡፡
ሕዝብ መንግሥት አያዳምጠኝም ብሎ ተስፋ ሲቆርጥ ቀስ በቀስ መንግሥትን ማዳመጥ ያቆማል፡፡ መንግሥት የመናገሪያ መሣሪያ ስላለው ብቻ ይናገራል፡፤ ሕዝብም ጆሮ ስላለው ብቻ ይሰማል፤ ግን አያዳምጥም። ነገሩን እውነት ነው ብሎ አይቀበለውም፡፡ ለእኔ ነው ብሎ ልብ አይለውም፡፡ አዳምጦም የሚፈለገውን ምላሽ አይሰጠውም፡፡
አንተ ስትናገር ያልፋል በእኔ ላይ
እኔም ስናገርህ ያልፋል ባንተ ላይ
ከንግዲህ ሆነናል ወንዝና ድንጋይ
የተባለው’ኮ ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ወንዝ በድንጋይ ላይ ሲያልፍ ይጮኻል ግን ድንጋዩ አይሰማውም፡፡ ድንጋዩም ውኃው በላዩ ላይ ሲያርፍ ይጮኻል፤ ግን ወንዙ አይሰማውም፡፡
ሕዝብን የማያዳምጥ መንግሥትና እርሱ የሚፈጥረው መንግሥትን የማያዳምጥ ሕዝብ እንዲህ ናቸው፡፡

10 Comments on “ሕዝብን የሚያዳምጥ መንግሥት፤ መንግሥትን የሚያዳምጥ ሕዝብ!! ዲ/ን ዳንኤል ክብረት”

  1. የልቤን መከፋት ሆዴ እያዳመጠ
    ሊመረው ነው መሰል ነገር አላመጠ::

    እዚያ ማዶ ሆኖ አንድ ሰው ተጣራ
    እዚህ ማዶ ሆኖ ሌላ ሰው ወይ አለው
    ጎበዝ ተነቃቃ ይህ ነገር ለኛ ነው::

    ከዛፍ ወደ ዛፍ ላይ ትዘላለች ጦጣ
    መሬትን ያገኘ ኮሚቴን ያጠጣ::

    ቤቱን አፍርሱ አሉን የበላንበትን
    ማፍረስስ አልጋውን ትኋን ያለበትን::

    ልጅህን አምጣ ይላል የኛ ዘመናይ
    እኔ ልጄን ስወልድ አዋልዶኛል ወይ::

    አንተ ስትናገር ያልፋል በእኔ ላይ
    እኔም ስናገርህ ያልፋል ባንተ ላይ
    ከንግዲህ ሆነናል ወንዝና ድንጋይ::

  2. Debtera Daniel wedet tega;tega ?????

    25 AMET WEYANEN SITAGELEGIL NOREH .e

    eskezare yet neberk ?

    AHUN MIN SEMTEH NEW ???
    YE eTHIOPIAN Hizb Meshengel atichlim !!!

    QOY:HAGERU YERGA BILEN ENJI SELANTE ALE NEGER !!!

  3. Dear Daniel; this is high time to speak on my behalf, just after reading this piece. I have read so many of your articles before. Indeed, many of them are so cautious and remarkable that they deserve attention and respect. I appericiate your concern to your country.

    In this (your) piece, you seem to reavel that the link between the speaker and the listner is missing right now. Or, otherwise, do you think that there is still a room to reverse that? You also seem to advise the supposed listners that they have to just start listening.

    Leaving aside the above and envissioning about the future, what kind of system do you think is appropriate for realizing the situation underwhich those who speakes and supposed to listen is entertained; provided that you are imagining a kind of society endowed with speakers and listners aswell. I strongly recommend you to engage yourself in that endravor.
    Million Thanks!

  4. ወደድን ጠላንም የቆሸሸን ቤት ማደስ ተገቢ ነው ስርአቱ ግልሙት ሆኗል አድፏል ።

  5. ዲ/ን ዳንዔል፤
    ድፍረት ባይሆንብኝ፤ እስኪ አንተ ራስህ በዚህ አገዛዝ ከተማረርክባቸው ነገሮች ጥቂት ላስታውስህ ፤
    – የአገዛዙን የጎሳ ዘር ተክትሎ ጵጵስናን የሚያህል ነገር ፣ሲደፈር፤
    ሲኖዶስን ያህል ነገር ሲከፋፈል፤ በየአህጉራቱ ያሉት የእናት ቤተክርስቲያን አውደ ምህረቶች የፖለቲካ መነታሪኪያ ፣ የፖለቲካ መደስኮሪያ ከሆኑ ድፍን 25 ዓመት አልሞላንም? ለመሆኑ በአንተ አስተያየት ፣ ሩብ ክፍለ ዘመን ሙሉ የማይሰማ ..ይቅርታ ማያዳምጥ አገዛዝ ነው ያለው ብለህ ነው የምታስበው?
    ለማንኛውም የሰጠኽው ምክር ፤ ከሃገር እና ህዝብ ስቃይ ጋር ሳነጻጽረው፣ ካንሰር ለያዘው በሽተኛ አስፕሪን የመስጠት ያህል ተሰምቶኛል። ለነገሩ እንተም ብለኽዋል ህዝብ ያውቃል ፣ ሁላችንንም !

  6. አንተ ስትናገር ያልፋል በእኔ ላይ
    እኔም ስናገርህ ያልፋል ባንተ ላይ
    ከንግዲህ ሆነናል ወንዝና ድንጋይ
    ይህ በትክክል ያለንበትን ወቅት ይገልፃል ፡፡ ወያኔ ህዝብን ለማዳመጥ ፈቃደኛ አይደለም ስለዚህም ወያኔን የሚያዳምጥ ህዝብ የለም ፡፡ ወያኔ ድንጋይ ነዉ የማይሰማ ይልቁንም በጥይት ህዝብን በመግደል ስልጣኑን ለማራዘም የሚሞክር ያልገባዉ ነገር ገዳይም ተገዳይም ህዝቦች መሆናቸዉን ነዉ ስለዚህም እነዚህ ህዝቦች ለመገዳደል ያስገደዳቸዉን አስገዳይ መንግሥት መግደላቸዉና ማስወገዳቸዉ አይቀርም

  7. Dn Daniel
    We really appreciate your writing as always. He is always outspoken and wrote this for his own audience, not for Ethiopian review. He has been writing for the government since the new patriarch took office. It’s nothing new. He has been serving the church all his life. Never left Ethiopian orthodox people for his comfort to come and hide in America. He will be there for them as he always has.

  8. Robel
    Rama I really admire what you have wrote here. Dn Daniel didn’t even have a house for his family. I saw him trying to find a house to rent not long ago in Ethiopia and felt so bad that a teacher like him can’t even afford to buy his own house. He is an example of a real servant of God.

  9. ዲን ዳንኤል አንድ ያልገባህ ነገር ያለ ይመስለኛል ምንድነው መሰለህ ኢትዮጵያ የውስጥ እኮ ህዝብ እንጂ መንግስት የለም። አሁንስ ገባህ?

  10. በጣም ውስጥ የሚገባ እንደ አንድ ሃላፊነት እንደአለበት የሃይማኖት ሰው የተነገረ ነው።በእውነቱ ትክክለኛ አስተሳሰብ ነው። ቃለ ሕይወት ያሰማል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*