ግቡን ያልመታው ትግል

ከአገሬ አዲስ

ሰሞኑን በሰሜን አፍሪካ የአረብ አገሮች የተካሄደውን ሕዝባዊ ትግልና ያስገኘውን መለስተኛ ድል በሚመለከት “እኛስ መቼ” የሚለው ጥያቄና የትግል ጥሪ ሲንሸራሸር ከርሟል፣ አሁንም እየተንሸራሸረ በመሄድ ላይ ነው። በብዙ ግለሰቦችና ቡድኖች ለአንድነት ትግል የሚደረገው ጥሪ እየጎላ መጥቷል። ሆኖም ግን የየራሳቸውን ጎጆ ሰብረው በመውጣት ጥሪ ለሚያደርጉለት የአንድነት የጋራ ግንባር ምስረታ ፈቃደኞችና ግንባር ቀደሞች ሆነው አልታዩም፤ እንደውም ከማን አንሼ በሚለው ውድድር የተሰለፉ ይመስላሉ። ይህ በዓላማ ለመገናኘትና ለመሰባሰብ ፈቃደኛ ያለመሆን አቋምና አዝማሚያ እስከዛሬ ድረስ አንድ ሳንሆን ለደረሰብን የመከራ ኑሮና ውድቀት አስቀጣይ ጥረት ከመሆን በስተቀር የሚያመጣው ለውጥና የሚሰጠው ጥቅም የለም። አሁንም በተናጠል ጥሪ የሚያደርጉት ግለሰቦችና ቡድኖች እውነት በአገራችን ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ የሚሹ ከሆነ ለለውጥ መምጣት እንቅፋት ሆኖ የቆየውን የተበታተነና የተነጣጠለ የትግል ባህል ሰብረው ትግላቸውን አንድ የጋራ አካል በመፍጠር ሊያቀናጁት ይችላሉ፣ ማቀናጀትም አለባቸው። የትናንቱ የግብጽ ሕዝብ የትግል ውጤት የሚያሳየንም ያንን ነው። የግብጽ ሕዝብ በተለይም ወጣቱ ትውልድ ላለፉት ሶስት ሳምንታት በቆራጥነት፣ በአንድነት ተባብሮ በከፈለው የደም ዋጋ ለትናንቱ ድል አብቅቶታል፤ ለዘላቂውም ዴሞክራሲያዊ ለውጥና ስርዓት የበለጠ እንዲታገል ማበረታቻ ሞተር ሆኖታል። ይህን የተጀመረ የድል ውጤት ሊያስመዘግብ የቻለው ውስጣዊ ልዩነቱን አቻችሎ፣ የፖለቲካ መስመርና የሃይማኖት ልዩነቱን ወደ ጎን አስቀምጦ፣ ለሁሉም የጋራ በሆነው ነጻነቱና ጸረ አምባ ገነን በሆነው የትግል መድረክ በመሰለፉ ነው።

በአንዳንድ ወገኖቸ እንደሚጻፈውና እንደሚነገረው በኢትዮጵያ ምድርም የዚህ አይነቱ ሕዝባዊ ትግል እንዲካሄድ የሚያሳስብና ጥሪ የሚያደርግ ነው።የኢትዮጵያ ሕዝብ ባይልለት ነው እንጂ ከትናንቱ የግብጽ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ በፊት የዛሬ ሰላሳ ሰባት ዓመት ተመሳሳይ ትግል አካሂዶ የነበረውን ዘውዳዊ ስርዓት የገረሰሰ ነበር። ሆኖም ግን በተደራጀ የፖለቲካ ፓርቲ አለመኖር፣ በመሪ እጦትና የአንድነት ግንባር አለመኖር የትግሉ ውጤት በጣት ለሚቆጠሩ አረመኔ የወታደር አምባገነኖች የስልጣን መሰላል ሆኖ ለአስራ ሰባት ዓመት የመከራ ዘመን ዳርጎን አለፈ።ለአለፉትም ሃያ ዓመት በቦታው የተተካው ዘረኛ መንግስት ስልጣን ይዞ አገሪቱን የሚያምሰው በዛው በቀጣይነት ተሸክመን በኖርነው አንድ ላይ ቆመን ላለመስራት፣በአንድ የጋራ ግንባር ስር ላለመሰለፍ በምናደርገው የተናጠልና ከማን አንሼ ውድድር የተነሳ ነው።

የዛሬ ስድስት ዓመት ዘረኛውን ቡድን ብርክ ውስጥ ያስገባና ሕዝቡን ያስተባበረው ትግል ውጤቱ ከስሞ የቀረውና የተጨናገፈው በአንድነት አብሮ ከመቆም አለመቆምን፣ ከጋራ ትግል ይልቅ የተናጠል ትግልን፣ ሕዝቡን ለስልጣን ከሚያበቃው ዴሞክራሲያዊ አሰራር ይልቅ የግለሰቦች ስልጣን ፍላጎትና ውድድር በመቅደሙና በዚያው ሽኩቻ ተፈረካክሶ በመቅረቱ ነው።

የምንከተለው አሰራርና የትግል ዘዴ ሳይለወጥ እኛም ባስተሳሰብ ሳንለወጥ እድሜአችን ብቻ እየተለወጠ የሌሎች አገር ሕዝብ ለድል የበቃበትን ትግል እያየንና እየተመኘን ቁጭ ብለናል።ለስሙ የለውጥ ያለህ ብለን ብንጮህም የትግል ሂደታችን ያው የበፊቱ አይነት “እኔ”ከሚለው ፍላጎት የራቀ አይደለም።”ወደ እኔ ኑ” እንጂ ወደ እሱ ልሂድና ልምከር የሚለው ቀና አስተሳሰብ የደበዘዘ ነው።”ለስሟ ቁና ሰፋች” እንደሚባለው ትግሉም ለዝናና ለጥቅም የሚወዳደሩበት ንግድ እየመሰለ መጥቷል።

ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላማዊ ኑሮ፣እድገትና ነጻነት የሚመኝ ማንኛውም ዜጋ ፣የግብጽን ሕዝብ የትግል ውጤት ከመመኘት ይልቅ ከሰላሳ ሰባት ዓመት በፊት የተጀመረው ተጨናግፎ ግቡን ያልመታው ትግል የየካቲቱ ንቅናቄ ተገቢውን መልስ እንዲያገኝ እስከዛሬ ድረስ እንቅፋት የሆነበትን የመከፋፈል ባሕልና አሰራር ለዘለቄታው አውግዞ በየቦታው ለአንድነት ጥሪ የሚያደርጉት ቡድኖችና ግለሰቦች ከጎጆአቸው ወጥተው በአንድ ጠረጴዛ ዙርያ ተሰባስበው እንዲመክሩ ማሳሰብና ማስገደድ ነው።

በዚሁ የተለያዩ ቡድኖችና ግለሰቦች ለአንድነት ግንባር መፈጠር ጥሪ ማድረጋቸው የሚታወቅ ነው።ከነዚህም ውስጥ ” አስተባባሪ ኮሚቴ” በሚል ስም ከስድስት ወራት በፊት ጥሪ ያደረገ አካል አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ሲቪክ ተቋማትና ታዋቂ ግለሰቦችን በማሰባሰብ የጋራ ግንባር ምስረታ ሂደት ውስጥ እንዳለ ገልጿል። በመደጋገምም ሌሎቹ እንዲሰበሰቡ ጥሪ አስተላልፏል።በአቶ ኦባንግ ሜቶም የሚመራው እንዲሁ ለአንድነት ግንባሩ ምስረታ በግሉ ጥሪ አስተላልፏል፣ በ”እስከመቼ” በሚለውም ቡድን ዙሪያ ለዚሁ ለአንድነቱ ጥሪ ተደጋጋሚ ጽሁፍ ቀርቧል።በጣም የሚያሳዝነው ነገር እነዚህ የተለያዩ የአንድነት ግንባር ጠሪዎች እርስበርሳቸው ለመቀራረብ ፍላጎት አለማሳየታቸውና እርምጃም አለመውሰዳቸው ነው። ሌላውን ለመሰብሰብ ጥሪ ሲያደርጉ፣የአንድነት ግንባር መፈጠር አስፈላጊነቱን ሲያወሱ እርስ በርሳቸው ላለመገናኘት የግል ካምፕና ግምብ ከመገንባት አለማለፋቸው የሚያሳዝን ነው። አንዳንዶቹም በግለሰብ ደረጃ ሳይቀር ለተደረገላቸው ጥያቄና ጥሪ መልስ ሳይሰጡ ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው እንዳልሰማ በመሆን የግል ጥረታቸውን ቀጥለውበታል።ተቀራረቡ የሚለውን ልመናና ማሳሰቢያ የስልጣን መንበራቸውን እንደሚያናጋና እንደሚያጠፋ ፈንጂ በመቁጠር ጥሪውን አልተቀበሉትም፤የጨዋ መልስም አልሰጡበትም።በነሱ ጥሪ ስር ያልመጣና ያልተመራ አንድነት ግንባር ከሚፈጠር ይልቅ ግንባረ ቢስ የተበታተነ ትግል እየተካሄደ በስልጣን ላይ ያለው ዘረኛ መንግስት ዘላለም ቢኖር የሚመርጡ ይመስላል።

የመልእክታቸው አንባቢ የሚጽፉትን አንብቦ ከመቀመጥ ይልቅ የሚሉትን በተግባር ለመግለጽ ሙከራ እንዲያደርጉ፤ተመሳሳይ ፍላጎትና ዓላማ ያላቸው በቅድሚያ ተገናኝተው በጋራ ለመስራት የሚችሉበት ውይይት እንዲያደርጉ ማስገደድና መጠየቅ ይኖርበታል።የሚያነሱት ጥያቄ የነሱ ብቻ ሳይሆን ሁላችንንም የሚመለከት ነው፤ ስለዚህ አሳልፈን የምንሰጠውና በዝምታ የምናልፈው ጉዳይ አይደለም።

ጌዜውና ያለንበት ሁኔታ በተናጠል የምንባክንበት ሳይሆን የተናጠል ጥረታችንን የምናሰባስብበትና የምናዋቅርበት ነው።የጊዜው አንገብጋቢ ጥያቄ በትግል አይነቱ(የትጥቅና ሰላማዊ በሚለው) መጨቃጨቅ ሳይሆን ትግሉን ሊመራና ሊያቀናጅ የሚችል ጠንካራ የጋራ ግንባር መመስረቱ ነው።በጠንካራ የአንድነት ግንባር ስር ያልተመራ ትግል ፣ለተወሰነ ቡድን ስልጣን መውጣት በር ይከፍታል ወይም ያለው ዘረኛ መንግስት ዕድሜ እንዲራዘም ይረዳል። የትግሉን አቅጣጫና መልክ ሊቀይስና ለድልም ሊያበቃ የሚችለው ትልቁ መሳሪያ ጠንካራ የጋራ ግንባር መኖር ነው።ግንባር ተፈጥሮ ፣በግንባሩ ታምኖበት የሚቀየሰው የትግል አይነትና ጉዞ አስተማማኝ ነው፤ብዙሃኑን ስለሚያሳትፍም ለድል ዋስትና ይሆናል።

ከአለፈው የትግል ልምዳችን እንደተረዳነው ለውድቀታችን ዋና ምክንያት የሆነው ተነጣጥለን በየፊናው ያካሄድነው የትግል ጉዞና ፣እርስ በርሳችን እየተባላን በመወጋገዝ ሃይላችንን በማድከም የተነሳና የጋራ ጠላታችን ባገኘው እድል ለመጠቀም መቻሉን መሆኑን መካድ የለብንም።አሁንም በዛው በለመድነው አካሄድ ከቀጠልን የትግል ዕድሜ እየቆጠርን ከመሄድ በስተቀር ትግላችን በአመርቃኝ ውጤት ሊጠናቀቅ አይችልም።

በግለሰብ ደረጃ በአደረኩት ጥረት የተገነዘብኩት ነገር ቢኖር የአስተባባሪው ኮሚቴው ቡድን በተሻለ ደረጃና አቅም መገኘቱን ነው።እነማን ናቸው ወደሚለው ኳላቀርና እንቅፋት ፈጣሪ ጥያቄ አላመራም።ከማንነታቸው በላይ የተነሱበት ዓላማ ለአሁኑ ጊዜ አስፈላጊና ወሳኝ ነው ብዬ ስለማምን ሌሎቹ በተናጠል ለማዘጋጀት የሚያባክኑትን ጊዜና ጉልበት ወደዚህኛው ቢያውሉትና በግንባሩ አመሰራረት ላይ እኩል ተሳትፎና ድርሻ እንዲኖራቸው፤ በየበኩላቸው ለተመሳሳይ ዓላማ ድርጅት ለመፍጠር ከመድከም የተፈጠረውን ለማጠናከር ጥረት ያደርጉ ዘንድ በአንድነት ስም እጠይቃቸዋለሁ።ያለፈ ነገር እያነሱ ፣ከመቻቻልና አብሮ ከመስራት ይልቅ የሚለያዩበትን ነጥብ እያወሱ ከመራራቅ ሕዝብ ለሚሻውና ለሚሰለፍበት የጋራ ዓላማ መነሳቱና መጣሩ ትልቅ ዋጋና ብልጫ አለው። ተበታትኖ ከመበታተን ተሰባስቦ መሰብሰቡ ቅድሚያና ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

በተጨማሪም የተለያዩት የአንድነት ግንባር ጠሪ ቡድኖችና ግለሰቦች እስከዛሬ ድረስ አብሮ ለመስራት ያደረጉትን ጥረትና ውጤቱን እንዲሁም የገጠማቸው ችግር ካለ እንዲገልጹ በተቀረው የአንድነት ግንባር ፈላጊ ስም እጠይቃለሁ።

የአንድነት ግንባሩ ጥሪ በተግባር ይገለጽ!!

ግቡን ያልመታው እረጅሙ የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል በድል ይጠናቀቅ!!