የወያኔ ወሮበላ ቡድንና ተላላኪዎቹ
የወያኔ ወሮበላ ቡድንና ተላላኪዎቹ
ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየው በማን እንደሚዘወርና ማንን እንደሚያገለግል ለአማራ ሕዝብ መንገር ለቀባሪው ማርዳት ነው፤ በዚህ ገልቱ ግለሰብ አስተያየት ላይ መወያየትም እርባና የለውም፡፡ የእኛ አጀንዳ ግፈኛው የሕወሓት ወሮበላ ቡድን የአማራን ሕዝብ ጥያቄ ለማኮላሸት ምን ያህል ሊሠራ እንደሚችል፣ ለዚህ ደግሞ ክልሉን አስተዳድራለሁ የሚለው ብአዴን በተባለው የሕወሓት ቅምጥ ድርጅት ውስጥ በከፍተኛ አመራርነትና በዘዋሪነት የተቀመጡት እንደበረከት ስምኦንና ካሳ ተክለ ብርሃን ያሉ የአማራ ሕዝብ ደመኞች ምን ያህል በተለመደው የጥፋት ተግባራቸው ሊገፉበት ቆርጠው እንደተነሱ ከሕዝባችን ጋር መወያየት፣ መተንተንና አቅጣጫ ማስቀመጥ ነው፡፡
በሕወሓት ሠራዊትና የደኅንነት አካላት እየተዋከቡም ቢሆን ሕዝባቸውን ለማገልገል የቆረጡ በርካታ የብአዴን አባላት እንዳሉ ጥርጥር የለውም፡፡ እነዚህን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እናከብራቸዋለን፤ እንደግፋቸዋለን፡፡ ይሁን እንጂ ከወሮበላው ሕወሓት ጋር አንድና ያው ሆነው ብአዴንን የሚያሽከረክሩት እንደ በረከት ስምኦን፣ ካሳ ተክለብርሃንና ታደሰ ካሳ ያሉት ምንደኞች በመሆናቸው፣ ብአዴን ራሱን ከሕወሓትና ከእነዚህ የሕወሓት መሣሪያዎች ነጻ አውጥቶ ለአማራ ሕዝብ ይቆማል ማለት አይቻልም፤ ተግባሩ የሚያሳየውም ይህንኑ ነው፡፡
ለዚህ ነው ትግሉ መራራና እልህ አስጨራሽ መሆኑን ማወቅ የሚገባን፡፡ ትግሉ መራራ ቢሆንም የገባንበትን አስከፊ ሁኔታ ተረድተን እንደ ሕዝብ ከተንቀሳቀስን ግን የማንወጣው አይደለም፡፡ ለዚህ ደግሞ የትግል ስትራቴጂያችን ወዳጅና ጠላትን በሚገባ የለየና ጥራት ያለው እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡ ስኬታችንም ውድቀታችንም በዚህ ስትራቴጂያችን ድክመት ወይም ጥንካሬ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡