በኦሮምያክልል ውስጥ ያለው ህዝባዊ እምቢተኘት እንደተፋፋመ ነው
ቢቢኤን ሐምሌ 23/2008
የአዲስ አበባን ህገ ወጥ ማስተር ፕላን ተከትሎ ከወራት በፊት የተነሳዉ የኦሮምያ ህዝባዊ እምቢተኝነት ተፋፍሞ እንደቀጠለ ነዉ። ከ400 ሰዎች በላይ የሞቱበት የኦሮምያ ህዝባዊ እምቢተኝነት ህወሃት መራሹ የጫነዉ የጭቆና ቀምበር በቀጣዩ ትዉልድ ሳይሆን፤ አሁን ባለዉ ትዉልድ የእድሜ ዘመን ከኦሮሞ ህዝብ ላይ ሊወርድ ይገባል በሚል መርህ ተፋፍሞ ቀጥሏል። የኦሮም ህዝብ ተቃዉሞ ስርዓቱን ሊያንገዳግድ የበቃ ሐይል ነዉ የሚል አስተያየት እየተሰጠበት ነዉ።
ይዘቱንና ቦታዉን እያቀያየረ በእየለቱ የሚከሰተዉ የኦሮሞ ህዝባዊ እምቢተኝነት የህወሃትን አከፋፍሎ የመግዛት ሴራ ያከሸፈ ብቻ ሳይሆን የህወሃት የሽብር ጦርን አጋዚን ግራ ያጋባ ህዝባዊ ሐይል መሆኑ እየታየ ነዉ።ከኦሮምያ ህዝባዊ እምቢተኝነት አንቀሳቃሽ ግብረ ሐይል ለማወቅ እንደተቻለዉ ከትላትና ወዲያ ምሽት በምእራብ ሐረርጌ ዉስጥ ተቃዉሞ ያሰሙ የነበሩ ወጣቶች የአጋዚ መጠለያ የነበረን ቦታ በእሳት በማቃጠላቸዉ በኦሮምያ የሰፈረዉ አጋዚ ቦታዉን ለቆ እንዲሔድ መደረጉ ታዉቋል።
በምእራብ አርሲ በአዳባ ወረዳ በላጆ አካባቢ የትግል ባንዲራዉን እያዉለበለበ እደባባይ የወጣዉ ህዝብ ነጻነቱን ከህወሃት እንደሚቀዳጅ ቁርጠኝነቱን እንዳሳየ ታዉቋል። በተመሳሳይ መልኩ በላጆ አካባቢ በነበረዉ ተቃዉሞ ህዝቡ የትግል ባንዲራዉን አንግቦ መንገድ ላይ ወጥቶ ድምጹን አሰምቷል።ህዝቡ የኦሮሞ ወገኑ እየደረሰበት ያለዉን ስቃይና መከራ ያወገዘ ሲሆን በሚያደርገዉ ትግልም ገፍቶ እንደሚቀጥል ቁርጠኝነትን ያሳየ መሆኑን የኦሮሞ ህዝባዊ እምቢተኝነት አንቀሳቃሾች አሳዉቀዋል።
በምስራቅ ወለጋ በቤጂ ዉስጥ ህዝባዊ ተቃዉሞ ሊቀሰቀስ ይችላል ብሎ የሰጋዉ ህወሃት መራሹ መንግስት የአጋዚ ስምሪትን አጠናክሮ መቀጠሉን ከስፍራዉ የተገኘ መረጃ ያመላክታል። የአጋዚ ስምሪት ምንም በምስራቅ ወለጋ መጠመሩ ቢታይም ህዝቡ መብቱን ለማስከበርና ነጻነቱን ለመቀዳጀት ያለዉ ፍላጎትና ተነሳሽነት የላቀ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
በዛሬዉ እለትም ታላቅ የተቃዉሞ ትእይንት በምእራብ አርሲ በሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች እንደነበር ታዉቋል።ጢዮ፣ዋቀንቴራና ጢጆ በዛሬዉ እለት የህዝባዊ እምቢተኝነቱ አካል የነበሩ ሲሆን ባካባቢዎቹ የነበሩት የመከላከያ ሰራዊቶች ማፈግፈጋቸዉ የህዝቡ ብሶት የደረሰበትን ደረጃ እንደሚያመላክት ተገልጿል። ያፈገፈጉት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ራቅ ካሉ ስፍራዎች እንደገና መሰባሰብ መጀመራቸዉ የታወቀ ሲሆን ይህም ለመብቱ፣ለነጻነቱ ቁርጠኝነቱን እያሳየ ላለዉ የምእራብ አርሲ ህዝብ የሚያስፈራ አይደለም ሲሉ የአካባቢዉ ነዋሪዎች ያስረዳሉ።
በምእራብ ሐረጌ በቱሉ ወረዳ በሁንዴ-ሙሴማ አካባቢ በንጹኋን ነዋሪዎች ላይ ተኩስ የከፈቱት አጋዚዎች ብዙ ሰዎችን ማቁሰላቸዉ የታወቀ ሲሆን በዚሁ ድንገተኛ ጥቃት ሰለባ የሆኑትን ሶስት ሰዎች ስምን የኦሮሞ ህዝባዊ እምቢተኘት አንቀሳቃሾች አሳዉቀዋል። ኪሚያ ጀማል፣አሲያ አብዱሏሒና ኢብሳ አህመድ የጥቃቱ ሰለባዎች መሆናቸዉ ተገልጿል። ሶስቱም በጥይት የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸዉ ንጹኋን ዜጎች የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸዉ መሆኑ ታዉቋል።
የኦሮሚያ ህዝባዊ እምቢተኝነት ወደ ምስራቅ ሸዋ ገስግሶ በአዳሚ ቱሉ ጂዶ-ኮምቦልቻ ያለዉ ወጣት አደባባይ በመዉጣት በመላዉ ኦሮሚያ ከሚደረገዉ ተቃዉሞ ጋር በመንፈስ የተሳሰረ መሆኑን አስመስክሯል። ወጣቱ ምንም ሐረርጌ፣ቦረናና ወለጋ ካለዉ ወገኑ ጋር በርቀት ቢገኝም የሚብከነከነዉ ተመሳሳይ በሆነ የመብትና የነጻነት ጥያቄ መሆኑን አሳይቷል።
ህዝብን የሚያረጋጉ የአገር ሽማግሌዎችን፣ወጣቱን ቀናዉን ጎዳና የሚያሳዩ የተከበሩና የእድሜ ባለሰጋ የሆኑን የኦሮሞ ተምሳሊታዊ አባቶችን ህወሃት ያስራል፣ያሰቃያል የሚል ክስ ይቀርብበታል። የኦሮሞ ህዝባዊ እምቢተኝነት ከወራት በፊት ሲጀመር ህዝብን ሰብስበዉ ያረጋጉ ያገር ሽማግሌዎች እሲስ እበባ ማእከላዊ እስር ቤት መግባታቸዉን የሚገልጹት የኦሮሞ ህዝባዊ እምቢተኝነት አንቀሳቃሾች በሻሸመኔ ነዋሪ የሆኑት የተከበሩት የኦሮሞ ሽማግሌ ዴኬባ ዋሪዮ መታሰራቸዉን ይፋ አድርገዋል። በቤተሰብና በቤተዘመድ ላይ ጫናን ለመፍጠርና ለማሸበር ዴኬባ ዋሪዮ ወጣት ልጃቸዉ ቦንቱ መተሳሯ ታዉቋል። መስል የሽብር ተግባራት የኦሮሞን ህዝብ ጥንካሬ የሚሰጡ ቢሆኑ እንጂ ወደ ኋላ የሚያስቀሩት አይሆኑም በማለት በማለት ስለ ሁናቴዉ የሚያስረዱ አሉ።
በምስራቅ ሐረጌ በዶጉ ጉራዋ በሰርግ ላይ በአጋዚ የተገደለዉ ኢብሳ አደም ሲቀበር ህዝቡ የቀብር ስነስራቱን ለተቃዉሞ አዉሎት እንደነበር ታዉቋል። የኦሮሞን ህዝብ የትግል ባንዲራና መፈክሮችን ይዞ የወጣዉ ህዝብ የኢብሳ አደም ሞት አንገቱን እንደማያስደፋዉ፥በህወሃት የሚመራዉን መንግስት ተጠያቂ አድርጎ በትግሉ እንደሚቀጥልና መስዋእትነትን እንደሚከፍል አሳዉቋል።
በኦሮሚያ ዉስጥ ያለዉ ተቃዉሞ ቀጥሏል። መንገዶች በየቦታዉ ይዘጋሉ።የህወሃትን ጥቅም አስከባሪ የሆኑ አዉቶብሶች ይቃጠላሉ።ወታደራዊ መጠለያዎችን ወጣቱ በእሳት እየለኮሰ የመከላከያ ሰራዊትን ቦታ ሲያስቀይር ይታያል። የኦሮሞ ህዝብ የትግል ባንዲራዉን እያዉለበለበ አደባባይ መዉጣቱን ቀጥሏል። ፍርሃት አከርካሪዉ የተሰበረ ይመስላል። በሰፊዉ የኦሮሚያ መሬት ዛሬ ተቃዉሞ ያልተነሳበት ቦታ ነገ የተቃዉሞ መናኸሪያ ይሆናል። መሬቱ መሳሪያን ካነገተዉ የህወሃት የሽብር ጦር እጅ እያፈተለከ በህዝብ ቁጥጥር ስር የመሆኑ እዉነታ እየታየ ነዉ። ህዝቡ አምርሯል መዳረሻዬ የድል ደጃፌ ብሏል።
ህዝቡ መወዳጀትን መርጧል፣ህዝቡ መጫረስን እምቢኝ ብሏል። ህዝብን እየጨረሰ ያለዉ፣ህዝብን ያከፋፈለዉ አምባገነናዊዉ መንግስት በቅቶታልና በህዝብ የበላይነት ዳኝነትን ያግኝ-ችሎት ይቅረቡ የሚል የጋራ ዉስኔ በሰሜን፣በደቡብ፣በምስራቅና በምእራብ ባለዉ ህዝብ የተወሰነ ይመስላል። ህወሃት በሐያ አምስት አመታት ዉስጥ በጥላቻ ሊበታትናት የፈለጋትን አገር በፍቅር እንስፋት የሚል ጣምራ ድምጽ ይሰማል።
