የጎንደር ሰልፍን በተመለከተ ሕዝብ ሕገ መንግስታዊ መብቱን ማስደፈር የለበትም (ግርማ ካሳ)
ሕዝብን በወክሉ ሽማግሌዎች እና በብአዴን ባለስልጣናት መካከል በሰሜን ጎንደር ዞን ፅ/ቤት ሲካሄድ የነበረው ስብሰባ ያለ መግባባት መበተኑን የሚገልጹ ዜናዎችን እያነበብን ነው። በሰሜን ጎንደር ዞን በተነሳው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ምክንያት፣ ብአዴን ከፍተኛ አጣቢቅኝ ዉስጥ እየገባ ነው። ሆኖም ግን ድርጅቱ አሁንም የሕወሃት ተጽኖ የለቀቀው አይመስልም። ቢያንስ ለሕወሃት ታማኝ የሆኑ ግለሰቦች አሁንም ብአዴን የሕዝብን ጥያቄ እንዳያከበር ወደ ኋላ እየጎተቱት ያለበት ሁኔታ ነው ያለው።
ሕዝብን ወክለው የመጡ ሽማግሌዎች ያቀረቧቸው ጥያቄዎች መሰረታዊና ቀላል የሆኑ ጥያቄዎች ናቸው። ከነዚህ መካከል አንዱ ሰልፍ የማድረግ ጥያቄ ነው። በሕግ መንግስቱ ላይ ዜጎች ሰላማዊ በሆነ መንገድ ድምጻቸዉን የማሰማት መብት አላቸው። ያንን መብት ነው የጠየቁት። ስላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት።
ሕወሃት በወልቃይት ጠገዴ፣ ብዙ ሰዎችን በአዉቶብስ ከተከዜ በስተምስራቅ በማመላለስ ፣ ያሉትን ደግሞ በማስፈራራት፣ እናቶችንም ጠመንጃ አስይዞ በማሰለፍ ሰልፎችን ማድረጉ ይታወሳል። ሕወሃት ያቀናበራቸዉን ሰልፎች፣ የነ ጌታቸው ረዳ ኢቢሲ(ኢቲቪ) ሰፊ ሽፋን ሰጥቶትም እንደዘገበው አይተናል።
ታዲያ የአማራው ክልል ሕዝብ ድምጹን እንዳይሰማና ሰልፍ እንዳያደርግ መሰናክሎች ከፊቱ የሚወረወሩበት ምክንያቱ ምንድን ነው ? እንዴት ነው ሕገ መንግስቱ ላይ ያለ መብት የሚሰራው ለአንድ ክልል ነዋሪዎች ብቻ ነው እንዴ ? ብአዴንስ ሕወህቶችን ለማስደሰት እስከመቼ ነው በሕዝቡ ጥያቄ ላይ ቀዝቃዛ ዉሃ የሚከለብሰው ?
ሐምሌ 14 ቀን 2008 ዓ.ም፣ ሽማግሌዎች ከብአዴን ባለስልጣናት ጋር ባደረጉት ዉይይት ለሐምሌ 17 ሰልፍ እንደሚያደርጉ ሲያሳወቁ ባለስልጣናቱ ከአሥር ቀናት በኋላ እንዲደረግ በመጠየቃቸው ሰልፉ፣ ከ10 ቀናት በኋላ፣ ለእሁድ ሐመሌ 25 እንደሚደረግ እየተነገረ ነው።
ሆኖም ግን አሁንም ብአዴን ምን ያህል ለሰልፉ እውቅና ሰጥቶ፣ ጥበቃዎችን አሰማርቶ ፣ ሰልፉ እንደሚደረግም በአማራው ክልል ራዲዮና ቴሌቭዥን እንዲነገር አስደርጎ የህዝብ ጥያቄን እንደሚያከብር ገና በይፋ የታወቀ ነገር የለም። አሁንም ብአዴን ዉስጥ ያሉ የሕወሃት ታማኞች ሰልፉን በድጋሚ ለማጨናገፍ ሙከራ ማድረጋቸውን ያቆሙ አይመስልም። ያ ብቻ አይደለም ለሰልፉ ቅስቀሳም እንዳይደረግ፣ ሰልፉ ሊደረግ ትንሽ ቀናት ሲቀሩት ብቻ እውቅና ሊሰጡም ይችላሉ። ከጎንደር ዙሪያ ህዝብ ወደ ከተማዋ እንዳይመጣና የትራንስፖርትና አገለግሎት እንዲቋረጥ፣ መንገዶችን እንዲዘጉም ሊያደርጉም ይችላሉ።
ሕገ መንግስቱ ሰልፍን ይፈቅዳል። የብአዴን ባለስልጣናት ሕዝብን ለማዳመጥ በመጠኑም ቢሆን ፍቃደኘነት ስላሳዩና ሰልፉ ከ10 ቀናት በኋሏ ይደረግ ብለው ስለጠየቁ፣ የሰላምና የዉይይት መንፈስ እንዲዳብር ከሕዝቡ ዘንድም ፍላጎት ከመኖሩም የተነሳ፣ በ10 ቀናት በኋላ ለማድረግ ሰልፉ አንድ ጊዜ ተራዝሟል። ከዚህ ዉጭ ሰልፉን ማራዘም ማለት ሕዝብን እንደመናቅ ነው። በመሆኑም ሕዝቡ ብአዴኖች እውቅና ሰጡም አልሰጡም ወሳኝ እርሱ መሆኑን ከማረጋገጥ ዉጭ ሌላ አማራጭ ሊኖረው አይገባም። ብአዴኖች ስራቸው ህዝብን መታዘና ህዝብ ማገልገል ነበር። ሕዝብን ከማገልገል ሕውሃትን ማገለገል ከመረጡ ህዝብ እነርሱም የሚታገስበት ትከሻ የሚኖረው አይመስለኝም።
አንድ ነገር መረሳት የለበትም። ህወሃቶች አንድ በጣም የተካኑበት ነገር አለ። አንድ ነገር አፍጥጦ ሲመጣባቸው መልካቸዉን ቀይረው ለማዘናጋት ሰላም ፈላጊ ወይንም ተደራዳሪ ሆነው ይቀርባሉ። በምርጫ ዘጠና ስባት ለመስከረም 22 ቀን 1998 ሰልፍ ተጠርቶ በነበረበት ጊዜ አቶ መለስ ዜናዊ የአሜሪካን አምባሳደር አማላጅነት ልኮ በሁሉም ጉዳዮች ላይ ለመደራደር ዝግጁ ነኝ ካለ በኋላ፣ የቅንጅት መሪዎች ድርድር ይኖራል ብለው ሰልፉን ካራዘሙ በኋላ አቶ መለስ ዜናዊ ቃሉን አጠፈ። ጭራሹኑ የቅንጅት መሪዎችን ወደ ቃሊቲ ወሰደ። ድርድር፣ ዉይይት መልካም ነው። ግን ድርድር፣ ዉይይት አለ ተብሎ በምንም መልኩ መዝናጋት አያስፈልግም። ብረት ሞቆ እያለ ካልቀጠቀጡት በኋላ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው።
በጎንደር የሚደረገዉን ሰልፍ በተመለከተ ሕጉ እንደሚፈቅደው ለከትተም አስተዳዳሪዎች የማሳወቅ ሥራ ተሰርቷል። በባህር ዳር፣ በደሴና በደብረ ብርሃንም ሰልፎች ለማድረግ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ እየሰማን ነው። በዚህ ረገድ ጥረቱ በተጠናከረ መንገድ መፋጠን ያለበት መሰለኝ። እስክ አሁን ላለፉት አንድ ሳምንታት ማለት ይቻላል እንቅስቃሴዎች እየታዩ ያሉት በሰሜን ጎንደር ብቻ ነው። በደቡብ ጎንደር (ደብረ ታቦር) በምእራብ (ባህር ዳር) እና ምስራቅ (ደብረ ማርቆስ) ጎጃም ዞኖች፣ በሰሜን (ወልዲያ) እና ደቡብ (ደሴ) ወሎ ዞኖን በሰሜን ሸዋ (ደብረ ብርሃን) ዞኖች ህዝቡ ድምጹን ማሰማት መጀመር አለበት።