ክቡር ሚኒስትሩ እና የአክስታቸው ልጅ ስለ ግንቦት 20
[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን አስጠሩት]
- አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አንድ አስቸኳይ ሪፖርት አዘጋጅ፡፡
- የምን ሪፖርት ክቡር ሚኒስትር?
- እንደ ዶሮ ክሽን ያለች ሪፖርት ነው የምፈልገው፡፡
- ኪራይ ሰብሳቢነት ላይ ነው?
- ኧረ አይደለም፡፡
- ታዲያ ሙስና ላይ ነው?
- ምን ይላል ይኼ?
- ይቅርታ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ላይ ነው?
- የለም የለም፣ የግንቦት 20 ፍሬዎች ላይ፡፡
- እነዚህ ታዲያ የምን ፍሬዎች ናቸው?
- እ…
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- ስማ እንደ አፕል ግመጡኝ ግመጡኝ የሚል ሪፖርት ነው የምፈልገው፡፡
- Iphone ላይ እንዳለው አፕል ማለት ነው?
- በትክክል፡፡
- ግን ክቡር ሚኒስትር ሪፖርቱ ለማን ነው የሚቀርብው?
- ለሕዝቡ ነዋ፡፡
- ሕዝቡ እኮ ታዲያ አፕል ሲገመጥ በሥዕል ብቻ ነው የሚያየው፡፡
- እና ምንድን ነው የሚገምጠው?
- ኧረ በአሁኑ ጊዜ ኮሽምም ካገኘ መልካም ነው፡፡
- በል አሁን አትንኮሻኮሽብኝ፡፡
- ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ሚስታቸው ጋ ደወሉ]
- እንኳን አደረሰሽ፡፡
- ለምኑ?
- ለብር ኢዮቤልዩ በዓላችን፡፡
- ከተጋባን 25 ዓመት ሞላን እንዴ?
- የትግላችን ውጤት 25 ዓመት ሞላው አይደል?
- ግንቦት ሃያን ማለትህ ነው?
- ስሚ ግንቦት 20 ለእኔ ትልቅ ትርጉም ነው ያለው፡፡
- እንዴት?
- አስቢ እንጂ ሴትዮ?
- ምን ማለትህ ነው?
- እስቲ ተመልከቺ፡፡
- ምኑን ልመልከት?
- አምስቱ የተንጣለሉት ቪላዎች የምን ፍሬዎች ናቸው?
- የግንቦት 20፡፡
- ሦስቱ ሕንፃዎች የምን ፍሬዎች ናቸው?
- የግንቦት 20፡፡
- በውጭ ባንክ የተቀመጠው ገንዘብ የምን ፍሬ ነው?
- የግንቦት 20፡፡
- ስለዚህ ይኼ በዓል ለእኔ ልዩ ቦታ አለው፡፡
- እውነት ብለሃል፡፡
- ስለዚህ ድል ያለ ድግስ መደገስ አለብን፡፡
- እኮ ምን ይደረግ?
- አምስት በሬ ታርዶ ድብልቅልቅ ያለ ድግስ ይደገስ፡፡
- እና የት ነው የሚደገሰው?
- በቅርቡ የተረከብነው አዲስ መሬት ላይ የቻለውን ያህል ድንኳን ተጥሎ እዛ ይደገስ፡፡
- ድግሱስ ላይ ማን ነው የሚጠራው?
- እንደ እኔ ያሉ የግንቦት 20 ፍሬዎች ናቸዋ፡፡
- ስለዚህ ተጋባዦቹ እንትኖች ናቸዋ፡፡
- ምኖች?
- የግንቦት 20 ፍራፍሬዎች!
[የክቡር ሚኒስትሩ የአጎት ልጅ ስልክ ደወለላቸው]
- ሄሎ ጋሼ!
- አቤት ጐረምሳው፡፡
- የሩቅ ሰው አደረከኝ በቃ ጋሼ?
- ምን እያልክ ነው?
- ልጅ ስትድር እንዴት ለእኔ አትነግረኝም?
- ኧረ ማንንም አልድርም፡፡
- ይኸው በሰፈራችሁ ሳልፍ ልጠይቃችሁ ጐራ ስል ቤት አምስት ሠንጋዎች ቆመው አይቼ ነው፡፡
- እሱማ ለሠርግ አይደለም፡፡
- ታዲያ ለምንድን ነው?
- ለግንቦት 20 ነው፡፡
- ጋሼ እኔና አንተ ከእሱ የበለጠ ሠርግ አለን እንዴ?
- እንዴት ማለት?
- ከግንቦት 20 በፊት እኮ እኔ በረንዳ አዳሪ ነበርኩ፡፡
- እሱማ ልክ ነው፡፡
- አሁን ይኸው በግንቦት 20 ሳቢያ ለመጡ በዓላት ሁሉ ኮርድኔት ማን ነው የሚያደርገው?
- አንተ ነህ፡፡
- ኮፍያ ማን ነው የሚሠራው?
- አንተው ነህ፡፡
- ቲሸርት ማን ነው የሚሠራው?
- አንተው ነህ፡፡
- የኅትመት ሥራዎችን ማን ነው የሚሠራው?
- አንተው ነህ፡፡
- ስለዚህ ጋሼ ግንቦት 20 እኔን ከመሬት ሰማይ የተኮሰኝ በዓል ነው፡፡
- እሱስ ልክ ብለሃል፡፡
- እኔ እንደውም በዚህ ወር ለሚወለደው ልጄ ስም አውጥቼለታለሁ፡፡
- ማን ልትለው?
- የግንቦት 20 ፍሬ፡፡
- ድንቅ ስም ነው ባክህ፡፡
- ለማንኛውም ለእኔ ግንቦት 20….
- ምን?
- ውስጤ ነው!
[የክቡር ሚኒስትሩ የአክስት ልጅ ደወለችላቸው]
- ምነው ድምፅሽ ተዘግቷል?
- ትንሽ አልቅሼ ነው፡፡
- ምን ሆነሽ?
- ስለግንቦት 20 ቲቪ ላይ እያየሁ፡፡
- ታዲያ ምን አስለቀሰሽ?
- እንዴት አላለቅስ ጋሼ?
- እኮ ምን ሆንሽ?
- ግንቦት 20 ባይኖር ኖሮ ምን ልሆን እንደምችል አስቤው በጣም አለቀስኩ፡፡
- ምን ትሆኚ ነበር?
- ምን ነካህ ጋሼ?
- ምነው?
- ከግንቦት 20 በኋላ እኮ ነው ሕንፃ መገንባት የቻልኩት፡፡
- እሱስ ልክ ነሽ፡፡
- ከግንቦት 20 በኋላ አይደል እንዴ አሥር ተሳቢ መኪና ሊኖረኝ የቻለው?
- ልክ ብለሻል፡፡
- ከግንቦት 20 በኋላ አይደል እንዴ ዓለምን እንደፈለኩ እየዞርኩኝ ያለሁት?
- ወይ ግንቦት 20?
- እሱ ባይኖር እኮ ከዛች ደሳሳ መንደር ባልወጣሁ ነበር፡፡
- አንቺም ሌላኛዋ የግንቦት 20 ፍሬ ነሻ?
- ስማ ጋሼ እንደውም አንድ ሐሳብ አለኝ፡፡
- የምን ሐሳብ?
- ከመስከረም እስከ ጳጉሜ ያሉት ወራት ቢቀየሩ ደስ ይለኛል፡፡
- ምን ይባሉ?
- ግንቦት!
[አንድ የክቡር ሚኒስትሩ ወዳጅ ባለሀብት ስልክ ደወለላቸው]
- እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
- ጠፍተሃል ወዳጄ?
- ይኸው ሆቴሉን ለማጠናቀቅ ሌት ተቀን እየተጣደፍኩ ነው፡፡
- ምነው? ምን ተገኘ?
- እንደው ለዛች ቅዱስ ቀን እንድትደርስ ብዬ ነዋ፡፡
- ለየቷ ቅዱስ ቀን?
- ለግንቦት 20 ነዋ፡፡
- ዋናው እኮ ሆቴሉን መሥራትህ ነው፡፡
- የለም የለም ክቡር ሚኒስትር፣ ለእኔ ያቺ ቀን የሕይወቴ ቃና የተለወጠባት ቀን ናት፡፡
- እንዴት ማለት?
- ክቡር ሚኒስትር ከዛ በፊት እኮ የመንግሥት ክበብ ውስጥ ሻይ አፊይ ነበርኩ፡፡
- ወይ ለውጥ?
- ይኸው በግንቦት 20 ምክንያት 20 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ቤት ውስጥ እኖራለሁ፡፡
- እና ግንቦት 20 ለአንተ ልዩ ናት ማለት ነው?
- ልደቴን ራሱ የማከብረው በዚህች ቀን ነው፡፡
- መቼ ነው ግን የተወለድከው?
- ግንቦት 7፡፡
- እሱማ የአሸባሪ ቀን ነው፡፡
- እኔም ለዛ እኮ ነው ግንቦት 20 የማከብረው፡፡
- ለመሆኑ የሆቴልህን ስም ምን አልከው?
- ግንቦት 20 ሆቴል!
[የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ቢሯቸው ገባ]
- ሪፖርቱን አጠናቀርክልኝ፡፡
- ኧረ ስለእሱ ላማክርዎት ነው፡፡
- ምንድን ነው የምታማክረኝ?
- Google ላይ ‹‹የግንቦት 20 ፍሬዎች›› ብዬ ጻፍኩና google አደረግኩት፡፡
- እና ምን አለህ?
- ‹‹Do you mean የግንቦት 20 እሳቶች?›› ብሎ መለሰልኝ፡፡
- ከኒዮሊብራል ኩባንያ ምን ትጠብቃለህ?
- ግን ክቡር ሚኒስትር ግንቦት 20 ፍሬ አለው እንዴ?
- ፍሬ ብቻ ሳይሆን ፍራፍሬዎች ነው ያሉት፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ሰዎች ግን እንደዚህ አያስቡም፡፡
- ምንድን ነው የሚያስቡት?
- ግንቦት 20 ፍሬ ሳይሆን ያለው ወሬ ነው አሉኝ፡፡
- ይኼ የፀረ ልማት ኃይሎች ወሬ ነው፡፡
- ለመሆኑ የግንቦት 20 ፍሬ ምንድን ነው?
- እ…
- ሰዎች የሚታይ ግን የማይበላ ፍሬ ነው ብለውኛል፡፡
- ወይ ጣጣ፡፡
- የሚገኝበት ቦታ የት እንደሆነስ ያውቃሉ?
- የት ነው የሚገኘው?
- ሙሰኛ ሹማምንት ጋ!
[ክቡር ሚኒስትሩ የግንቦት 20 በዓልን አስመልክቶ የተዘጋጀውን ስብሰባ እየመሩ ነው፡፡ ተሰብሳቢዎች ስለበዓሉ ምን ዓይነት አመለካከት እንዳላቸው ሲጠየቁ፣ አንድ የቀድሞ ታጋይ አስተያየት መስጠት ጀመረ]
- እሺ ምንድን ነው አስተያየትህ?
- ክቡር ሚኒስትር ከትግል ጀምሮ እንተዋወቃለን፡፡
- አስተያየትህን ብቻ ስጥ፡፡
- ባለፉት 25 ዓመታት ውስጥ ሙስና ከቁጥጥር ውጪ ሆኗል፡፡
- እ …
- የመልካም አስተዳደር ችግር ሕዝቡን ደም እንባ እያስለቀሰው ነው፡፡
- ሰውዬ?
- የሀብት ክፍፍሉ በእጅጉ ኢፍትሐዊ ነው፡፡
- ምን ማስረጃ አለህ?
- ቅድም እንዳልኩት እኔና እርስዎ አንድ ላይ ታግለናል፡፡
- እና ምን ይጠበስ?
- እርስዎ ከአንድም ሦስት ሕንፃ እንዳለዎት ይታወቃል፡፡
- ምን?
- አምስት ቪላዎች እንደሠሩም የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡
- ኧረ ይኼን ሰውዬ አስቁሙት፡፡
- በውጭ አገር የባንክ አካውንት እንዳለዎትም ይወራል፡፡
- እኔ እኮ የሚገርመኝ ከምታወሩ ለምን አትሠሩም?
- ክቡር ሚኒስትር እዚህ አገር ሠርቶ ከማደግ ሰርቆ መለወጥ ይቀላል፡፡
- ሰውዬ የስብሰባውን ሐሳብ እየሳትከው ነው፡፡
- ምንድን ነው ሐሳቡ?
- እዚህ ማውራት ያለብህ ስለግንቦት 20 ትሩፋት ነው፡፡
- እንኳን ትሩፋቱ ትርፍራፊውም አልደረሰኝማ፡፡
- በቃ ስለግንቦት 20 ፍሬዎች ተናገራ፡፡
- እኔ ማውራት የምፈልገው ስለሌላ ነገር ነው፡፡
- ስለምንድን ነው ማውራት የምትፈልገው?
- ስለግንቦት 20 ምሬቶች!