ትውስታዬ በውጭ ጉዳይ ሚንስቴር – ክፍል 3

በክፍል ሁለት የቢሮየ ተጋሪ ሲያሻው ስዩምን ደደብ እያለ እንደሚሳደብ መለስን ደግሞ ጀግና እያለ እንደሚያሞካሽ ገልጬ አቁሜ ነበር።እነሆ ተከታዩ ክፍል፤

እንደዚያ ዝም አንዳልኩ አራት ዓመቱ ደረሰና ወደ ውጭ አገር የመመደብ ምኞቴ እውነት ወደ መሆን ተቃረበ።የት አገር ይመድቡኝ ይሆን እያልኩ ማሰብን ተያያዝኩት።ኤምባሲዎቻችን ውስጥ ያሉ ክፍት ቦታዎችን አጠናሁ አንዳንድ አገሮችንም መርጥኩና ምዳባየን ብቻ መጠባበቅ ያዝኩ።ነገሮች ሁሉ መልካም መሰሉኝ።በነገራችን ላይ አንድ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሠራተኛ ወደ ውጭ አገር ያሉ ኤምባሲዎች ከተመደበ ከሲኦል ወደ ገነት እንደተዛወረ ይቆጠራል።በዘመድ አዝማድ መካከልም ፍጹም ደስታና እፎይታ ይሆናል።ድሮ ድሮ ወደ ውጭ አገር መላክ እንደ ግዞት ይቆጠር ነበር ሲባል ሰምቼ ነበር።የህወሃት እድገት ያመጣው አንዱ ፈተና አንድ ሰው ከቀየው ከመንደሩ ተነቅሎ ሲሄድ ፍጹም ደስታንና እፎይታን የማግኘቱ ሚስጢር ነው።ህወሃትና ጉጅሌዎቻቸው ለዚህ ምስጢር መፍቻ የሚሆን ቁልፍ ካላቸው  ሚስጢሩን ቢፈቱልን መልካም ነበር።

ይሄው እኔም ወደ ውጭ መሄጃየን ግዜ እያሰብኩ ለቤተሰቦቼ አይዟችሁ ያዘመመ መኖሪያችን የሚታደሰብት ግዜው ደርሷል እያልኩ አጽናናቸው ጀመር።

ወላጆቼም በተስፋ ተሞልተውና  ደስ እያላቸው ይመርቁኝ ጀመር።ሊወድቅ ያዘመመን ቤት ስጠግንላቸው እየታየኝ እኔም ውስጤን ደስ ሲለው ተሰማኝና መስሪያ ቤቴን ወደደኩት።ይሄን እድል ለሰጠችኝ አገር ታምኜ ማገልገል እንዳለብኝም ራሴ ለራሴ ቃል ገባሁ።

ሙዝ በዳቦ ከመብላት ልላቀቅ መሆኔንም እያሰብኩ ዘና አልኩ።ከምደባየ ስመለስም እንደ ቢሮየ ተጋሪ በወር 42 ሺህ ብር ማከራየት የምችለው ዓይነት ቤት ባይኖረኝም ከግለሰብ ኪራይ ቤት ወጥቼ የራሴ ማደሪያ ሊኖረኝ እንደሚችል አለምኩና ደስ አለኝ።በዚያች አገር ከዚህ በላይ ምን እንዳስብ ይጠበቅብኝ ይሆን ?  ሌላ ነገር ማሰብ  ወንጀል የሆነበት አገር ውስጥ ምን ላስብ እችላለሁ ?

እንዲህ ምድባየን እዚያ በሩቅ አለች እንደምትባለው መንግስተ ሰማያት በተስፋ እየጠበኩ ባለበት ወቅት የ1997 ዓ.ም ምርጫ ተቃረበ ቀስ በቀስም ቅንጅት የተባለ ድርጅት አዲስ ነገር ይዞ መጣ።ሁሉም በያለበት ሁኖ የወቅቱን ክርክር ተከታትሏል።እኛም ዴሞክራሲ የወለደውን ነፃነት ደህና አድርገን አጣጣምነው።በዚያን ወቅት ነጻነት እንደ ንጋት ፀሃይ ሰውነታችንን ሲያሞቅው ተሰማን።ያን የንጋት ፀሃይ የሞቀ ሁሉ ልቡና ሰውነቱ ተፍታቶ መንፈሱ  ሲቀየር አየሁ።የኢሕአዴግ ቱባ ቱባ ባለስልጣኖች በቴሌቭዥን መስኮት ብቅ እያሉ ክርክር ሳይሆን ስድብ መሰል ነገር በመያዛቸው ጉድ ጉድ ተባለ።የቅንጅት ተከራካሪዎች በትምህርት ደረጃቸው የላቁ በመሆናቸው ለክርክሩ አንብበው ተዘጋጅተውበትና የሚናገሩትን አውቀው ሲመጡ ስዩምን ጨምሮ የኢሕአዴግ ዋና ዋና የተባሉ ሰዎች ትእቢታቸውንንና ባዶነታቸውን ብቻ ይዘው መጡና በዓይኔ አይቼ በጆሮየም ሰምቼ በትካዜ ተዋጥኩ።ከዚያም “ኢንተርሃሞይ” የተባለ ባእድ ቃል በመጨመር የክርክሩን ድባብ አደበዘዙት።የውጭ ጉዳይ ሠራተኛ መሆኔን የሚያውቁ “ለመሆኑ እነዚህ ናቸው እንዴ አገር የሚመሩ” እያሉ ሲጠይቁኝ መልስ መስጠት ተሳነኝና የሚጠይቁኝን ሁሉ በመሸሸ ለማምለጥ ሞከርኩ።እውነትን መሸሸ በደንብ የተማርኩት ከህወሃት ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ነው።

ህወሃቶችና አጃቢዎቻቸው ለሚነሳው ጥያቄ ሁሉ መልሳቸው የደርግና የትምክህተኛ ጥያቄ እያሉ በመሳደብ ጥሩ ደጋፊዎቻቸውን ሁሉ አሳፈሩ።እኔም አፈረኩባቸው።እነርሱ ግን እፈረት አያወቁም።እንዲያውም በነውራቸው እርስ በርሳቸው ሲሞጋገሱ ሰምቼ በጣም ተገረምኩ።ነውራቸው ክብራቸው የሆኑ ዜጎች በገዛ አገሬ ላይ መሰልጠናቸውን ሳይ አዘንኩ።

የቢሮየ ተካፋይም “አይ በረከት ወንድ ነው።ልክ ልካቸውን ነገራቸው እኮ።ይሄ ትምክህተኛ ሁሉ ስልጣን እንዲሁ ሊወስድ ይፈልጋል እኮ እያለ ይፎክራል።ደግሞ አያፍሩም መሬት ይሸጥ ይላሉ እነዚህ የኤምፔሪያልዝም ርዝራዦች” እያለ ቅንጅቶችን ይሳደባል።እርሱ ግን  ሁለተኛ ቤት ሊሰራበት መሬት ለመግዛት ላይ ታች ይላል።ህወሃቶች እንዲህ ናቸው።ሌላውን ይከለክላሉ እነርሱ ግን በዚያ ሥፍራ ዋነኛ ተዋኒያን ይሆናሉ።ብዙዎቹ ይሄ ነውር መሆኑን የሚረዳ ሂሊና የላቸውም።አገርንም የሚያፈርስ ተግባር መሆኑን አይረዱትም።ወይም ለመረዳት አይፈልጉም።

በተቻለኝ ሁሉ ከዚህ ሠው ጋር ምንም ዓይነት አገራዊ ጉዳይ ላለማውራት እጠነቀቃለሁ።እፈራለሁ ልበላችሁ እንዴ ?።ህወሃት የባእዳን ስብስብ ነው።ጠብ መንጂያ በእጁ ነው ህግም አይገዛውም ታዲያ ብፈራ ለምን ፈራህ እባል ይሆን ? እነርሱ እኮ የጠላት አገር የሚገዙ ነው የሚመስላቸው። የእነርሱ አገር እና የእኔ አገር የተለያየች ሁናለች።እኔ ስለእነርሱ አገር ማውራት ፍላጎት የለኝም።ስለዚህ ዝም ማለት የተሻለ አማራጭ ነው ብየ አምን ነበር።ሁል ግዜ ዝም ማለት አይቻልም።አልፎ አልፎ ዝምታን የሚሰብር ሃሳብ ይመጣል።ዝምታየ በጥቂቱ በሚከተለው ሁኔታ ዘመም አለ።

አንድ ቀን ስለ ባድሜ ጉዳይ ተነሳና  አፌን ከፊቼ አስተያየት ሰጠው።ወደ ጦርነቱ መገባቱ ትክክል ነው ብየ አላምንም አልኩ።ከተዋጋንና ያ ሁሉ መስዋእትነት ከተከፈለ በኋላ ደግሞ አልጀርስ ድረስ ሂዶ ይግባኝ የማይባልበት  ስምምነት መፈራራም ትክክል ነው ብየ አላምንም ስል ጨመርኩ።

እንዴት ? አመራሩ አምኖ ትክክል ነው ብሎ ያደረገውን አለመቀበል እኮ ችግር አለው።ይህ ማለት ደግሞ በአመራሩ ችሎታና ብቃት ላይ ጥራጣሬ አለህ ማለት ነው ሲል ደመደመው።የእንስሳት አብዮት በተባለው መጽሃፍ ውስጥ “ሁለት እግሮች ሁሉ መጥፎ፤አራት እግሮች ሁሉ ጥሩ” ብለው የሚዘምሩ በጎች አሉ።የእነዚያ በጎች አምሳያ ይሄው ከዚህ ቢሮ አለ።ለዚህ ሰው መለስ ዜናዊ ፍጹም ንጹህና  ሁሉንም አዋቂ የማይሳሳት ነው።

እንዲህ ዓይነት እምነት ካለው ግለሰብ ጋር እንዴት መነጋገር ይቻላል ? ለማንኛውም ጉዳዩ ከሮ ሌላ ነገር እንዳያስከትል ስለሰጋሁ እንዲህ አልኩት ይሄ የመጠርጠር ያለመጠርጠር ጉዳይ ሳይሆን  በነገሩ አጀማመርና አፈጻጸም ላይ ግልጽነት ስለሚጎለው እውቀት የለኝም ለማለት ነው ።

ይገርማል አለ።

እዚህ ውስጥ ምን የሚገርም ነገር አለው ስል ጠየኩት።

ብዙ የሚገርም ነገር ብሎ ዝም አለ።ከዚህ በኋላ አልተነጋገርንም።

ይህች እለትና ይህች ንግግር ተስፋየንና ምኞቴን ያመከነች መሆኗን የተገነዘብኩት ብዙም ሳልቆይ ነው።

የአዲስ አበባ ህዝብ በሙሉ ቅንጅትን በመምረጡ በህወሃት ፤የውጭ ጉዳይ ሰራተኛ ደግሞ በስዩም መስፍን ጥርስ ውስጥ ገባ።ስዩምም ከሠራተኛ አስተዳደር የሠራተኞችን ስም ዝርዝር አስመጥቶ ከእነዚህ ውስጥ ባስቸኳይ 10% ይባረር ሲል መመሪያ ሰጠ።10%ቱን ረሽኑ ቢልስ ማን ይከለክለው ነበር ?

በቃ አስር ፐርሰንቱን አባርሩ ብሎ ቀጭን ትእዛዝ አስተላለፈ።ከአራት መቶ ሃያ ሰራተኞች መካከል 42 ሰው መባረር አለበት።በተለይ አማራ፤ኦሮሞና ጉራጌ ትኩረት ተደረገበት።ከተባረሩት 42 ሠራተኞች መካከል አንድም ትግሬ አለመኖሩ ነገሩ በሌሎች በተለይም በአማራ በኦሮሞና በጉራጌ ብሄር አባላት ላይ ያነጣጠረ መሆኑ ታወቀ።ይህ ድርጊት የሌሎች ብሄር አባላትን በትግሬዎች ላይ ቂም እንዲይዙ አላደረገም ማለት አይቻልም።የህወሃትም ምኞትና ፍላጎት ይሄው ነው።ትግሬዎችን ከሌላው ህዝብ ለይቶ የሥርዓቱ ተጠቃሚ አድርጎ ማሳየትና በሌላው ህዝብ እንዲጠሉ ማድረግ።በዚህ ረገድ ይሳካላቸው አይሳካላቸው እስከ አሁን ግልጽ የሆነ ነገር የለም።ጥላቻው ሥጋ ለብሶ ቁሞ እንዲሄድ ግን ህወሃቶች ቀንና ማታ እየሰሩ ነው።ሥጋው ነፍስ የዘራ እለት ግን አገራችን ብዙ ሳታለቅስ አትቀርም።እግዜር እዚያ ደረጃ  አያድርሰን ብሎ መጸለይ ብቻ ሳይሆን ህወሃት ሊዘራ የሞከረውን የጥላቻ ዘር ፍሬ እንዳያፈራ ሁሉም በያለበት የሚችለውን ማድረግ አለበት።ትግሬዎች ደግሞ ዝም አትበሉ።በእናንተና በሌሎች መካከል መለስ ዜናዊ የሚገነባውን የጠብ ግድግዳ ለማፍረስ አሁንም የረፈደ አይመስለኝም።”አማራና ኤምፔሪያልዝም የትግራይ ህዝብ ቀንደኛ ጠላቶች ናቸው” ብለው የሚያስቡትን ኃይሎች ተሳስታችኋል ብትሏችው ለሌላውም ለእናንተም  መልካም ነበር . . .

እኔ አማራም ኦሮሞም ነኝ።ኢሕዴግንም አምርሬ የምጠላ አልነበርኩም።እንዲህም በመሆኔ የመባረሩ ነገር እኔን ይመለከታል ብየ አላሰብኩም።እኔ ለመንግስት ታማኝ አገልጋይ መሆኔን ስለማውቅ መባረሩን እንደ እኔ ዝም ማለትን ልማድ ላላደረጉ ትቼ ጥቅሜን ብቻ ማሰብ ያዝኩ።ጥቅሜን ብቻ ማሰቤን የሚለው አስምሩልኝ።ኢትዮጵያችንን እየገደለ ያለው ይሄው “እኔ ብቻ” የሚለው ሃሳብ በየልቦናችን ውስጥ ነፍስ መዝራቱ ነው።ይሄ አሳፋሪ ነው።አለቃየ በሥራ አፈጻጸም የሰጠኝ ውጤት ከፍተኛ ነው።ምንም የሚያሳስበኝ ነገር አልነበረም።በራሴና በተሰጠኝ ውጤት ተማምኜ ምደባየን እንጂ ሌላ ለማሰብ ምክንያት አልነበረኝም።አንድም ቀን የቅንጅትን ሃስብ ደግፌ የቢሮየ ተጋሪን ከሚመስሉ ሰዎች ጋር አውርቼ አላውቅም።ስለዚህ የሚደርስብኝ ዱላ ይኖራል ብየ አልተጨነኩም።ቢሆንም ተባረርኩ።

አስር ፐርሰንቱን  መርጠው የሚያባርሩ ግለሰቦች በሚስጥር ተመርጠው በስዩም መስፍን ተሰየሙ።ኋላ እንደታወቀው በመስሪያ ቤቱ ውስጥ የነበሩት ህወሃቶች በቅንጅት ነውጥ ተደናግጠው ስለነበረ ለውጥ ፈላጊ ሃይሉን በሙሉ የ“ትግሬ” ጠላት ነው ብለው ፈርጀው ለማባረር ቆርጠው ተነሱ።በወቅቱ ለውጥ ፈላጊውን መርጠው ለማባረር በትጋት የሰሩና “ህወትን መቃወም ትግሬን መቃወም” ነው ብለው የሚያምኑ ናቸው የተባሉ ግለሰቦች  የሚከተሉት ናቸው።

1ኛ.ወንድሙ አሳምነው

2ኛ ሙሉጌታ ዘውዴ

3ኛ.ዋህደ በላይ

4ኛ.ካሳ ገ/ዮሃንስ

5ኛ.ኑረዲን  ዓሊ

6ኛ.ቢነጋ ተወልደ ሲሆኑ ፤ከቢነጋ ተወልደ በቀር ሌሎቹ በሙሉ የህወሃት አባላቶች መሆናቸው ይታወቃል። ቢነጋ ተወለደ አባል ስለመሆኑ ጥርጣሬ አለ።የዚህ ታሪክ ባለቤት ቢነጋ ተወለደ እንዲህ ዓይነት ድርጅት ውስጥ ገብቶ በተራ ሰብቅ ውስጥ ይሳተፋል ብሎ ለማመን ይቸገራል።በዚህ ጽሁፍ ውስጥም የቢነጋ ስም መነሳቱ ያሳዝነዋል።ብዙዎች የተባረሩት ግን  ቢነጋን ከሌሎች ለይተው አያዩትም።እውነቱን ቢነጋ ራሱ ካለበት ሁኖ ሊነገረን ይችላል።ኑረዲን ዓሊ ከፖለቲካል ሳይንስ ትምህርት ክፍል በብዙ መከራ ተንጠልጥሎ የጨረሰ ነው።በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ለመቀጠር ሲመረቅ ቢያንስ 3 ነጥብ ማግኝት ይጠበቅ ነበር።ህወሃቱ ኑረዲን ግን እንደምን ሆኖ እንደተቀጠረ ፈጣሪ ይወቀው።አብረውት የተማሩት የእርሱን ትምህርት የመቀበል አቅም ደካማነትን ሲናገሩ ስሰማ ህወሃትን በተጨማሪ ከመታዘብ በቀር ሌላ የምለው ነገር የለም።ከ1ኛ እስከ 4ኛ የተዘረዘሩት አዛውንት የድርጅቱ አባላት ናቸው።

እነዚህ በሚስጥር የተደራጁ ቡድኖች ሰራተኛው ሳያውቃቸው ውስጥ ለውስጥ የሌሎች ብሄር ተወካዮችን መርጠው ሴሎችን መሥርተው ጥናታቸውን ጀመሩ።ከዚያም ከሰራተኛው መካከልም ጓደኛሞችን እየከፈሉ ጓደኛህ ከመንግስት ፖሊስ በተቃራኒው ሁኖ መንግስትን የሚጎዳ ተግባር ፈጽሟል።አንተ ካሁን በኋላ እርሱን የምታድንበት መንገድ የለም።ስለአንተም የምናውቀው ነገር አለ ቢሆንም አንተ ብዙ ጉዳት አታደርስም ተሳስተህ ሊሆን ይችላል  የሚል እምነት አለን።አሁን ስለ ጓደኛህ የምታውቀውን ንገረን እያሉ ያፋጥጡ ገቡ።

ይቀጥላል፤