የአዞ ዕንባ
የአዞ ዕንባ
ከሃበተጊዮርጊስ ለገሰ
ስነ ልቦናዊ ማግባቢያ ወይም ማባበያ /Psychological Manipulation/ አንድን ተጎጂ የሆነ የህብረተሰብ ክፍልን ወይም ግለሰብን በተንኮል፣በማጭበርበር ወይም ጎጂ /Abusive/ የሆኑ ስነልቦናዊ ቴክኒኮችን በመጠቀም የግል ፍላጎትን ወይም ዓላማን ለማሳካት ጥቅም ላይ የሚዉል ዘዴ መሆኑን የስነልቦና ጠበብት ይናገራሉ፣፣
በነዚህ ዘዴዎች የሚፈጠሩ ማህበራዊ ተፅዕኖዎች ሁሉም አሉታዊ ዉጤት ብቻ አላቸዉ ተብሎ ባይገመትም እነዚህ ዘዴዎች ጨቋኝ፣ጎጂ፣ቅንነት የጎደለዉ ሀሳብ የሚቀርብበት ማጭበርበሪያ ቴክኒኮች በመሆናቸዉ አብዛኛዉን ጊዜ የማህበራዊ ተጽእኖዉ ዉጤቶች አሉታዊ እንደሆኑ ጠበብት ይስማሙበታል፣፣
ጆርጅ ኬ. ሲሞን /George K. Simon/ ተጎጂ የሆነ የህብረተሰብ ክፍልን በማጭበርበር፣በተንኮል ወይም በማባበል ለማግባባት ግለሰቦች የሚጠቀሙባቸዉን ቴክኒኮች ካብራሩት ዉስጥ አንዱ የስነልቦና ጠበብት ናቸዉ፣:
ከመሳቅ፣ ከማጨብጨብና የድጋፍ እጅ ከማዉጣት በስተቀር ለእዉነት ተከራክሮ የወከለዉን የህብረተሰብ ጥቅም ለማስጠበቅ ያልታደለዉን የፓርላማ አባል ወደ ፈለጉት አቅጣጫ የሚሾፈሩት አቶ መለስ የሲሞንን የማጭበርበሪያ የስነልቦና ቴክኒኮችን በአግባቡ እየተጠቀሙበት እንደሆነ በፓርላማ ዉሎዎች ወቅት እየታየ ነዉ፣፣
ሲሞን /George K. Simon/ በመጽሐፋቸዉ ዉስጥ ከጠቀሷቸዉ አንዱ ቴክኒክ ማሳፈር /Shaming/ ነዉ፣፣ በኚህ የስነልቦና ጠበብት አገላለፅ መሰረት ግለሰቦች በሌላዉ ላይ ተፅዕኖ ማሳደር ሲፈልጉ ተጎጂዉን ግለሰብ ወይም የህብረተሰብ አካል በማሸማቀቅ በፍርሀት ድባብ ስር እንዲወድቅና የእራሱን ችሎታና ማንነት እስከ መጠራጠር ድረስ እንዲደርስ የማድረጊያ የስነልቦና ቴክኒክ ይጠቀማሉ ይሉናል፣፣
ቀደም ካሉት የፓርላማ ዉሉዎች የቀድሞ የፓርላማ አባል የአቶ ተመስገንን የእንግሊዘኛ ቃል አነባነብ /Fiscal Monetary/ ለማረምና ለማስተማር ሲደረግ የነበረዉን የፓርላማ ድራማ ብናስተዉል አቶ መለስ የራሳቸዉን የበላይነትና አዋቂነት ለደጋፊዎቻቸዉ ለማጉላት የማሳፈር ቴክኒክ ሲጠቀሙ በእንግሊዞችና በአሜሪካኖች ዓይን ሲታዩ እሳቸዉም በትክክል እንደማያነቡ አጥተዉት አይመስለኝም፣፣
በሌላዉ የፓርላማ ዉሎ ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳን የሞኝ ለቅሶ መልሶ መላልሶ ብለዉ ሲተርቱባቸዉ ሞኝ አለመሆናቸዉ ሳይገባቸዉ ቀርቶ ሳይሆን ዶር ነጋሶ ላይ ስነልቦናዊ ጉዳት በማድረስ ችሎታቸዉን እንዲጠራጠሩና የአጥቂነትና የመጋፈጥ ሚናቸዉን በመቀነስ እሳቸዉ ግን ያሻቸዉን እነዲፈፅሙና እነዲናገሩ መንገዱን ለመጥረግ እንደሆነ መረዳት ይቻላል፣፣ ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳም ወደ ኢትዮጵያዊነት ጎራ በመቀላቀልና የአገር ቤት ትግልን በመምራት ሞኝ አለመሆናቸዉን እያስመሰከሩ ናቸዉ፣፣
በቅርቡ የካቲት ዉስጥ በተደረገዉ የፓርላማ ጥያቄና መልስም የስነልቦና የማታለያ ቴክኒክ ዉጤታማ እንደሚያደርጋቸዉ በማመን ሲጠቀሙበት ተሰምተዋል፣፣ በፓርላማ ብቸኛዉ ተቃዋሚ አቶ ግርማ ሴይፉ ላቀረቡት
ሁለት ዐቢይ ጥያቄዎች በአቶ መለስ የተሰጠዉን መልስ ብንመለከት ምን ያህል ህዝብን የማጭበርበር ስራ እየተሰራ እንደሆነ በቀላሉ ማወቅ ይቻላል፣፣
አቶ ግርማ የፖለቲካ ምህዳሩ መጥበቡን ለማሳየት ከህዝብ ጋር ለመወያየት አዳራሽ መከራየት እንዳልቻሉ፣ፍቃድ መጠየቅ በማያስፈልገዉ ፍቃድ እንደሚጠየቁ፣ፍቃድ ሲያቀርቡ በስልክ እንደሚታግድ፣ቢሮ ለመከራየት እንዳልቻሉና ለዚህም እንደ አንድ ፓርቲ ተወካይ ሳይሆን እንደ አንድ ሀገር መሪ አስተያየት እንዲሰጡ አቶ መለስ ሲጠየቁ በሰጡት መልስ የቤት ኪራይ ዉድ ከሆነና መንግስት ማቃልለ የሚችል ከሆነ እንወያይበታለን፣እንዲሁም ግለሰቦች አላከራይም ካሉ ድጋፍ ይደረግልን ማለት አንድ ነገር ነዉ በማለት ጥያቄዉን ወደ ሌላ ሀሳብ በመቀየር ማዛባታቸዉ /Diversion manipulative technique/ የፖለቲካ ምህዳሩን በማጥበብ በኩል የእሳቸዉ ሚና ከፍተኛ መሆኑን በግልፅ የሚያሳይ ነዉ፣፣
የአፄ ሀይለስላሴ ሀዉልት በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ለምን እንደልተተከለ ለቀረበላቸዉ ጥያቄ የክዋሜ ንክሩማህ/Kuwame Nekrumah/ ሀዉልት ስለተሰራ ተቃዉሞ እንደቀረበ አድርጎ ሀሳቡን ማዛባት ማምለጫ ለማያገኙለት ቀጥተኛ ጥያቄ ቀጥተኛ መልስ ከመስጠት ይልቅ በስነልቦና ማባበያ ቴክኒክ ሽወዳ /Psychological manipulative technique/ ኢትዮጽያንና እትዮጽያዊነትን የማሳነስ ዓላማቸዉን ማሳካት አመራጭ አድርገዉታል፣፣
የአዞ እንባ የዉሸት ሀዘንን፣ የይምሰል ርህራሄን፣ የዉሸት ለቅሶን በአጠቃላይ አስመሳይነትን የሚያመለክት ቃል ነዉ፣ ፣በሳይንስ እንደተረጋገጠዉ አዞ እንደሰዉ እንባ ፈሳሽ ነገር የሚያመነጭ ዕጢ እንዳለዉና ከዉሀ ዳርቻ ሲሆን ለረጂም ጊዜ ፈሳሹ ከአይኑ እንደሚወርድ ይነገራል፣፣ ነገር ግን አዞ እንባ ቢዎርደዉም አለማልቀሱ ግን /crying/ ሂደቱን የተሟላ ስለማያደርገዉ የአዞ ዕንባ የዉሸት ሀዘኔታና የአስመሳይ ሰዎች ባህሪ አመላካች ሆኖ ይገለፃል፣፣
ብራይከር/Harriet B.Braiker/ የተባሉት ሌላዉ የስነልቦና ጠበብት ግለሰቦች ተጎጂ የሆነ የህብረተሰብ አካልን ወደ አሰቡት ዓላማ እንዲመጣላቸዉ ከሚያግባቡበትና ከሚያታልሉበት ስነልቦናዊ ቴክኒኮች አንዱ የአዞ እንባን ማንባት /superficial sympathy or crocodile tears/ እንደሆነ ይገልፃሉ፣፣
የየካቲቱን ፓርላማ ዉሎ ሳዳምጥ በብራይከር /Harriet B.Braiker/ የተገለጸዉን የስነልቦና የማባበያ ቴክኒክ አቶ መለስ ሲጠቀሙ ስሰማ ምነዉ በዙሪያቸዉ የከበቡት አማካሪዎች አዎንታዊ ተጽዕኖ ለማሳደር እንዲጠቀሙበት ቢመክሯቸዉ አሰኝቶኛል፣፣
የሊዝ አዋጁን አስፈላጊነት ሲያስረዱ የመንግስት ሌባንና ከመንግስታቸው ዉጭ የሆነውን ሌባ ለመከላከልና ሀብታምም ደሀም ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ፣ የመንግሰትና የግል ሌቦችን ድራሻቸዉን ለማጥፋት ነዉ በማለት ህብረተሰቡ የማያዉቅ ስለመሰላቸዉ በሌቦች እንደተከበቡ በተደጋጋሚ አብስረዉናል ፣፣
ክቡር ጠ/ሚኒስትር የህዝብን ጥቅም በአጠቃላይ የነካ አዋጅ ፣ ጥቃቅን መሬትና ቤት ያላቸዉን ድሀዉን የህብረተሰብ ክፍል የሚጎዳ አዋጅ በማዉጣት ለድሀዉና ላገሪቱ ዕድገት ያሰቡ ከማሰመሰል ይለቅ ሲወጡና ሲገቡ የሚያዩትን ሰማይ ጠቀስ ሕንፃ በስድስት ሺ ብር ደመወዝ አርባ አመስት ሚሊዮንና ከዚያ በላይ ወጭ በማድረግ ያስገነቡትን ጄነራሎችና በህዝብ ሀበት ምዝበራ ተሰማርተዉ ቢሊየነር የሆኑ ባለቤትዎንና ጓደኞችዎን ለህግ በማቅረብ የዘረፉትን ለህዝብ ጥቅም ቢያዉሉ የሚሻል አይመሰልዎትም-ብላቸዉ ይቀበሉኝ ይሆን?
ከዚህ በላይ የተጠቀሰዉ የእኔ የግሌ ምክር ነዉ፣፣ ምክሩን ግን አቶ መለስ የሚቀበሉት አይመስለኝም ሌላ አማራጭ አላቸዉና፣፣ ምንም ያልነበራቸዉን በአጭር ጊዜ ዉሰጥ ባለፎቅና ቢሊየነር ያደረገ መንግስታቸዉ በህዝብ ተማምኖ በህዝብ ላይ እምነት ጥሎ ለሕዝብ ከመስራት ይልቅ ጥቂት ጄነራሎች፣ሃላፊዎችና ደጋፊዎችን ከበርቴ በማድረግ ሕዝብን መቆጣጠርና ማንበርከክ ይቻላል በሚለዉ ትክክለኛ ያልሆነ ስሌት የሚመራ አማራጭ ያላቸዉ ይመስለኛል፣፣ ይህ አማራጭ ግን ትልቅ አደጋ የሚያስከትል ስለሆነ የመንግስታቸዉ አወዳደቅ የሰሜን አፍሪካ መሪዎች አወዳደቅ ዓይነት ከመሆኑ በፊት የዉሸት ዕንባን በማቆም የህዝብን ጥያቄ በአግባቡ ቢመልሱ ይበጃል እላለሁ፡፡
ኢትዮጽያ ለዘላለም ትኑር!!!
ኢትዮጽያዊነት ያብባል!!!