የኢትዮጵያ ዘውጋዊ ክፍፍሎችና የመፍትሔ ሃሳብ
ፕ/ር መሳይ ከበደ

ይህ ጽሁፍ በቅርቡ ቪዥን ኢትዮጵያ ከኢሳት ቴሌቪዥን ጋር በመተባበር ባዘጋጀው ጉባዔ ላይ ያቀረብኩት ነው።
የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አሁን በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት በሠላም ወይም በኃይል ከሥልጣን ለማውረድ ቢችሉም እንኳን፤ ባለፉት 24 ዓመታት የተዘረጋውን ዘውጋዊ ክፍፍል ለማብረድና ብሔራዊ አንድነትን መልሶ ለመገንባት የሚያስችል ራዕይና ፖለቲካዊ መፍትሔ ያስፈልጋቸዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት ከሚስተዋሉት ችግሮች ሁሉ ተቀዳሚና እጅግ አስቸጋሪ የሆነው ዘውጋዊ ፖለቲካ በመሆኑ ያለውን መንግሥት ለመጣልና አዲስ ሥርዓት ለመመስርት ስለ ዘውግና ዘውጋዊ ፖለቲካ ትክክለኛ ግንዛቤ ማግኘትን ይጠይቃል። ወያኔ ከተሸነፈ የዘውግ ፖለቲካ በራሱ ይጠፋል ብሎ ማሰብ ከንቱ ምኞት ነው። ይህ ጽሁፍም “የዘውግ ፖለቲካ ዋና ዓላማ ምንድን ነው? ከብሔራዊ አንድነት ጋር በምን ሁኔታ ሊጣጣም ይችላል?” የሚሉትን ጥያቄዎች በአጭሩ ይዳስሳል።