ይህ ሁሉ ወንጀል እየተሠራ ያለው በሁለቱም መሪዎቻችን ግፊት ነው
ምሕረቱ ዘገዬ

በተለይ ካለፉት 25 ዓመታት ወዲህ ዓለምን የሚያስደምም ወንጀል በሀገራችን ውስጥ እየተሠራ ይገኛል። በዓለማችን የእስካሁንም ይሁን የወደፊት ታሪክ በፍጹም ያልታየና ሊታይም የማይችል ወንጀል ወያኔዎች እንደልባቸው እየሠሩ ናቸው። እነዚህ በጣት የሚቆጠሩና የዋናው ዓለም አቀፍ የወንጀለኞች ቡድን አባላት የሆኑ ጥቂት ወያኔዎች እየሠሩት ያለውን የከፋና የከረፋ ወንጀል ሁለቱም መሪዎቻችን በሚገባ ያውቃሉ። ነገር ግን ሁለቱም መሪዎቻችን እልህ የተጋቡና አንዳቸው በአንዳቸው ጣልቃ ላለመግባት የወሰኑ ይመስላል፤ በድርድርም ይሁን በመሸናነፍ ቅራኔያቸውን አስወግደው እኛን ሠላም ሊሰጡን አልቻሉም ወይም ምናባልት ጊዜው ገና ነው። የዝኆኖች መራገጥ ለሣር እንደማይበጅ ሁሉ እኛም በነሱ ሰበብ እየተደቆስን አለን።