ህገመንግስቱን አታርክሱታ!
ከህልሜ
በቱኒዚያ ሆነ፡፡ በግብጸም ሊሆን ነው፡፡ እኛስ ጋ? በሚል የስጋትና የስሜት ቧጣጭ ጥያቄ ሁላችንም ተወጥረን ባለንበት ሰአት፤በቅርጽ ብቻ ያለው ባዶ ቀፎው ፓርላማ ውስጥ አንድ ጥንብ አንሳ ጮኸ፡፡ ጩኸቱ ደሞ በአካካቢው ላሉ ትናንሽ ጥንብ አንሳዎች ነበር፡፡ጥንብ አንሳዎቹም፤ አፍ አላቸው አይናገሩ፤ ጆሮ አላቸው አያዳምጡ፤ አይን አላቸው አያዩ ናቸው፡፡ እርግጥ እጅ አላቸው ይወጣል፡፡ ሳይዘፈንለት ያጨበጭባል፡፡
ዋናው ቁንጮ አለቃቸው ያልተጠየቀውንና ሊጠየቅም ያልታሰበውን ‹‹አልፈቅድም!›› እያለ ጮኸ! ታየዋ! ያ ቀን አፍጥጦ ሲመጣበት፡፡ ታየው ያ በ97 እለተ ሚያዝያ 30 መስቀል አደባባይን ምጥ ያስያዘው ሰላማዊ ሰልፍና ሕዝባዊ ስብስብ ድጋሚ መጣሁብህ ሲለው እና፤ ሂትለርን ጠራ የደርግንም ቀይ ሽብር አነሳ፡፡ እዚህ ላይ የራሱን ግዳይ እነዚያን የዋህ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶችን፤እነዚያን የዴሞክራሲና የፍትህ የሰብአዊ መብት ተሟጋች የነገ መሪ ሊሆኑ የሚችሉ ዜጎችን የጨፈጨፈበትን ቀን ግን ሳያነሳው አለፈው፡፡
በጎረቤት ስላለው ሁኔታ ልንደሰት አይገባም! በማለት ዓለም ከዳር እስከዳር ያደነቀውን የሰላማዊ ለውጥ ጥያቄና ሂደት በማጣጣል ‹‹በሃገራችን ያሉት ሰላማዊ ነን የሚሉት እስኪመቻቸው ብቻ ነው እንጂ ሲመቻቸው ወደ ሌላ መዞራቸው፤ ሕገመንግስቱን እንጣስ ማለታቸው አይቀሬ ነው›› በማለት ድንጋጤና ፍርሃት የተመላበት ማስፈራሪያ ሰነዘረ፡፡
ሰውዬውና አጋር ተባባሪዎቹ ያልተገነዘቡት ጉዳይ ቢኖር፤ሕዝብ ሲበቃውና መኖር ወደማይችልበት የእለት ተእለት መከራ ውስጥ ሲገባ፤አምባገነኖች የሚያወሩትን ተረት ለመስማት ጊዜ እንደሌለው ማሰብን ነው፡፡ አምባገነን ገዢን መቃወም እንዴት ብሎ ከሂትለር ጋር ሊመሳሰል እንደሚችል ማሰብም የሚቻል ቅዠት አይደለም፡፡
ሂትለር ጋር የሚመሳሰለውማ የህዝብን ነጻነት፤ዴሞክራሲ፤ፍትህ፤ ሰብአዊ መብት በመጣስ እንደባርያ አስሮና በጦር መሳርያና በስለላ ድርጅቱ አንቆ የሚይዝ ነው፡፡
ሂትለር ጋር የሚመሳሰለውማ መብቱን ሊጠይቅ የሚነሳን ሕዝብ አፍኖ ለመያዝ የቅድሚያ እገድልሃለሁ፤አርድሃለሁ፤በማለት ጩኸት የሚያሰማ ነው፡፡
ከቀይሽብር ጋር የሚመሳሰልማ አስተዳደራዊ ፍትህን ሲጠየቅ፤ ሀገራዊ ጉዳይ ሲነሳበት፤ በዘር የመከፋፈል አስከፊነት ሲነገረው የስለላ ድርጅቱንና ጦሩን ለማንሳትና አመልካች ጣቱን እያሳከከው ተኩስ ተኩስ የሚለውን አግአዚን ለማሰማራት የሚነሳ ነው፡፡
ትላንት ሙባረክን አቅፈው ደግፈው ባንተ መጀን ሲሉት የነበሩት፤የአረቡ ዓለም ተጠሪያችን፤ የሰሜኑ ተሟጋች አጋራችን ሲሉት የነበሩት ሁሉ፤አሁን ጥንብ እርኩሱን ሲያወጡት እያየ አሁንም አካኪ ዘራፍ፤
እኔ አለኝ የነሱ ድጋፍ!
የሚለው ድንፋታ የትም እንደማያደርሰው ማወቁ ነው ቁም ነገሩ፡፡
ቁንጮው አምባገነን ‹‹ማንም አይኑን ያልተሸፈነ የሚያውቀው ነው›› በማት ሰላማዊ ትግል የሚያራምዱትን ሰላማዊ አይደሉም በማለት፤ የቅድሚያ የግድያ ኢላማው፤ የአስር ዛቢያው ሊያደርጋቸው እንዳቆበቆበ በአገልጋዮቹ ፊት አረጋገጠ፡፡
በመላው ዓለም ነጻ የዜና ማሰራጫ ጣቢያዎች ላይ የሚተላለፈውን እውነታ ላለማየት አይኑ የተሸፈነውና፤የአጋሮቹም አይን እንዲሸፈን የሚፈልገው አምባገነኑ መለስ፤‹‹የኢትዮጵያ›› እያለ በሚጠቀምበት የግሉ በሆነው ቴሌቪዥንና ሬዲዮማ የቱኒዚያው ሳይሰማ ሳይታይ አለፈ፤ የግብጹም በቀረበበት ጊዜ አስከፊ የሆነው ምስል ብቻ እየተመረጠ ለማስፈራሪያነት ቀረበ፡፡
ወጣቱ፤ በእድሜ የገፋው፤ሴቱ፤ወንዱ፤ ጤነኛው በሽተኛው፤ሁሉም፤በየቀበሌው በተወጠረው ድንኳን ስብሰባ እየተጠራ ስለወያኔ ጥሩነት፤የልማት ተነሳሽነት፤ለሃገር አሳቢነት፤ለሕዝብ ተቆርቋሪነት ምኑ ቅጡ? ሁሉም ሃሰት ተተረከለተ፡፡ተወራ፡፡ሊጠቀሙባችሁ የሚፈልጉ አሉና ተጠንቀቁ፤ ልጆቻችሁንም ምከሩ ወደ ቤት ሰብስቡ ተባሉ፡፡
ከዚህ መሰል ስብሰባ የወጡ አንዲት እናት ‹‹ ምን ቤት አለንና ነው? ቤቱንማ ለኢንቤስተር ብሎ አፍርሶት የለም እንዴ! የት ነው የምንሰበስባቸው?›› ብለው ተሳለቁበት እንጂ ውትወታውን ከቁጥርም አላስገቡለት፡፡
እጅጉን የሚያስገርመው ጉዳይ ግን አምባገነኖች የየትም ሃገር ይሁኑ የየትም ስራቸው፤ተንኮላቸው፤ንቀታቸው፤ውሸታቸው፤ፖለቲካቸው ሁሉ አንድ አይነትና ተመሳሳይ መሆኑ ነው፡፡ ሙባረክ ያን ሁሉ ሕዝባዊ እምቢታ እያዩና አገልጋዮቻቸውን እየላኩ በአደባባይ ያለውን እውነታ ዘገባ ካዳመጡም በኋላ ‹‹ይሄን ድርጊት የሚመሩት ጸረ ሕዝቦችና የግብጽ ጠላቶች ናቸው፡፡ የዚህ እንቅስቃሴ አቀንቃኞች በግል ፍላጎታቸው የተነሳሱ ሃይሎች ናቸው›› ማለታቸው ነው፡፡አቶ መለስም ሁልጊዜ ችግር ሲመጣባቸውና ሕዝባዊ ጥያቄ ሲያፈጥባቸው የሚሉት ልክ ይህንኑ ነው፡፡ ልዩነቱ ሙባረክ በአረብኛ መለስ ደሞ በአማርኛ መናገራቸው ብቻ ነው፡፡ሁለቱም ግን የለየላቸው አምባገነኖች ናቸው፡፡
አንድ ለጥቅም ፍለጋ ፎርም የሞላ አባል ‹‹እንዴ ሙባረክማ ስልጣን መልቀቅ አይችሉም፡፡ እሳቸው፤ማለት አቶ መለስ ሳይፈቅዱላቸውና ሂሳባቸውን ሳያወራርዱ ስልጣን መልቀቅ ብሎ ነገርማ አይታሰብም፡፡ ምንም ቢሆን የአባይን ጉዳይ በማስመሰል ተቃውሞ ለቀንላቸው እንዴት አሁን ስልጣን ይለቃሉ?›› ብሎ ቀለደ፡፡
እውነቱን ነው ነገሩ ሁሉ ለነሱ ቀልድ ነው፡፡ ለኢትዮጵያዊያን ግን የመረረ ብሶት፤መከራ፤ችግር ስለሆነ ለውጥ የግድ ነው፡፡ለውጥን በሰላማዊ መንገድ ለመጠየቅ የሚነሳን ሕዝብ ደሞ በጦር ለመውጋት፤ በሰላዮች ለማፈን ማሰቡ ከጥቅሙ ጉዳት የሚብስ ስለሆነ ቁንጮው አምባገነን አቶ መለስና አጋፋሪዎቻቸው አስቀድመው ሊገነዘቡት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡
የአቶ መለስ ያሁኑ የፓርላማው አካሄዳቸው አሜሪካው ኦባማ፤የጀርመኗ አንጌላ ሜርክል፤የፈርን ሳዩ ሳርኮዚ፤ሁሉም የአውሮፓ ዩኒየን አባል ሀገራት መሪዎች የሂትለር ተመሳሳዮች ናቸው ነው የሚሉን፡፡ ይህን በምን ሂሳብ እንዳሰሉት ከሳቸውና ከመሰል ፈላጭ ቆራጭ አምባገነን አቀንቃኞቻቸው ውጪ የሚያውቀው የለም፡፡
እኛ ኢትዮጵያዊያን አንድ ሆነን ኖረን፤አሁንም አንደነታችንን እትንኩብን በማለታችንና መብታችንን ተነጥቀናል በማለት፤የመልሱልን ጥያቄ ስናነሳ በአግባቡ መልስ ማግኘትን ካጣን ከርመናል፡፡አሁን ግን ያን ለማስመለስ አንድ ሆነን በአንድነት መነሳት ይኖርብናል፡፡
የመከላከያ አባላትም፤ስማቸው የሚያምረው የሀገር መከላከያ ሃይሎች ሲባልና በተግባርም ለሃገር ሲቆሙ ነው እንጂ፤ለማታለያ ተብሎ ‹‹ሕገመንግስቱን ሊጥሱ ነው›› በሚል የግለሰብ ጠባቂ ሲደረጉና የተከበረ ስማቸው ሲጠፋ፤እምቢ በማለት ለሃገር፤ለወገናቸውና ለክብራቸው ሊቆሙ ይገባቸዋል፡፡ በስማቸው ሲነገድ፤ በስማቸው ሃገር ስትጠፋ፤ በስማቸው ወገን ለስቃይ ሲዳረግ እያወቁ እንዳላወቁ ሆነው ማለፍ በታሪክም በትውልድም ተጠያቂ ያደርጋቸዋል፡፡
ለነጻነት መቆም፤ ለመብት መታገል፤ ሕገ መንግስቱ በግልጽ የሚፈቅደው የዜግነት መብት ነውና በአተረጓጎም እያሳሳቱ የሚያቀርቡትን በአንድነት ቆመን ሕገመንግስቱን አታርክሱት ልንላቸው የግድ ነው፡፡
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን በነጻነት ለዘልዓለም እንዲኖሩ ማሰብ እንጀምርና እንነሳ!!