ተቃዋሚ ፓርቲዎች በማሟያ ምርጫ አንካፍልም አሉ

በተለያዩ ምክር ቤቶች የተጓደሉ አባላትን ለሟሟላት የካቲት 20 2003 ዓ.ም. ሊካሄድ በታሰበው ምርጫ ላይ ፓርቲዎች አንሳተፍም ከማለታቸው በተጨማሪ አብዛኛው ህዝብም በመራጭነት ከመመዝገብ ተቆጥቧል፡፡ በሟሟያ ምርጫ ላይ እንዲሳተፉ ምርጫ ቦርድ በደብዳቤ ለሁሉም ፓርቲዎች ጥሪ ቢያደርግም ለመመዝገብ የቻሉት ግን ኢህአዴግን ጨምሮ ሶስት ብቻ ናቸው፡፡

የስድስት ፓርቲዎች ስብስብ የሆነው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት መድረክ፣ በቅርቡ ስምንት ፓርቲዎች የመሰረቱት የጋራ ፎረም እና መኢአድ በምርጫው ለመሳተፍ የሚያስችል ፖለቲካዊ ምህዳር ባለመኖሩ እጩዎቻቸውን ለማስመዝገብና ለመወዳደር ፍላጎት እንደሌላቸው በይፋ የገለጹ ሲሆን ሌሎቹ ፓርቲዎችም ሳይመዘገቡ ቀርተዋል፡፡

ፓርቲዎቹ ራሳቸውን ከውድድሩ ማቀባቸውን ተከትሎ ህዝቡ የምርጫ ካርድ ሊወስድ ባለመቻሉ የምርጫ ቦርድ ትላንት እንዲጠናቀቅ አቅዶት የነበረው የመራጮች ምዝገባም በአንድ ሳምንት ተራዝሟል፡፡ በጉዳዩ ላይ ያናገርናቸው አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ኢህአዴግ ብቻውን ተወዳድሮ በሚያሸንፍበት ምርጫ ላይ ተሳትፎ ለማድረግ ፍላጎት እንደሌላቸው አስታውቀዋል፡፡