ሚኒስትሩ ዛሬም በኔትወርካቸው ጉዳይ እንደተወዛገቡ ነው:: 1 ለ 7 የጥርነፋ ስትራቴጂ
ሚኒስትሩ ዛሬም በኔትወርካቸው ጉዳይ እንደተወዛገቡ ነው:: 1 ለ 7 የጥርነፋ ስትራቴጂ
[ክቡር ሚኒስትሩ ከቤት ሊወጡ ሲል ልጃቸው አኩርፎ አገኙት]
– ምን ሆነሃል?
– ምን እዚህ ዳዲ …
– ፊትህን እኮ ዘፍዝፈኸዋል፡፡
– ኢሜሉ ነዋ ዳዲ፡፡
– ኔትወርኩ አስቸገረህ?
– የትኛው ኔትወርክ?
– ስንት ዓይነት ኔትወርክ አለ?
– ያው የሙስናው ኔትወርክ…
– እ…
– የደላላው ኔትወርክ …
– ምን አልክ?
– ይኼ ቃል እኮ ስለሚያደናግረኝ ነው፡፡
– እኔ ያልኩህ የቴሌውን ነው?
– ዛሬ እንኳን ደህና ነው፡፡
– ታዲያ ምን ሆነህ ነው ያኮረፍከው?
– ለስኮላርሽፕ አፕላይ አድርጌ አልነበር?
– ምን አሉህ?
– አልተቀበሉኝም፡፡
– ለምን ሲባል?
– እኔንጃ ዳዲ፡፡
– እኔ ሪኮመንዴሽን ጽፌልህ?
– ምን ታደርገዋለህ ዳዲ?
– በጣም ተናንቀናል ማለት ነው፡፡
– ከማን ጋር?
– ከኒዮሊብራሎቹ ጋር!
[ክቡር ሚኒስትሩ የኒዮሊብራሎቹ ኤምባሲ ደወሉ]
– ጤና ይስጥልኝ፡፡
– አለቃሽን አገናኚኝ፡፡
– ማን ልበል ጌታዬ?
– ክቡር ሚኒስትር ነኝ፡፡
– ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
– አለቃሽን አገናኚኝ አልኩሽ እኮ?
– ስብሰባ ላይ ናቸው፡፡
– እናንተም ትገማገማላችሁ እንዴ?
– ግምገማ ላይ ሳይሆን ስብሰባ ላይ ናቸው ነው ያልኩዎት፡፡
– ስብሰባማ ካልተገማገምሽበት የምን ስብሰባ ነው?
– ምን ልርዳዎት ክቡር ሚኒስትር?
– ልጄ ለስኮላርሽፕ አፕላይ አድርጐ ነበር፡፡
– እሺ፡፡
– ግን አልተቀበሉትም፡፡
– ክቡር ሚኒስትር ዩኒቨርሲቲዎቹ እኮ ነፃ ተቋማት ናቸው፡፡
– እኔ ተወረዋል አልኩኝ እንዴ?
– ያው ልጁን ስላልተቀበሉት ኤምባሲው ምንም ማድረግ አይችልም ልልዎት ነው፡፡
– የመንግሥት ዩኒቨርሲቲ እኮ ነው?
– ቢሆንም ኤምባሲው ምንም ማድረግ አይችልም፡፡
– ለማንኛውም አለቃሽ ግምገማውን ሲጨርስ ይደውልልኝ፡፡
– እሺ፡፡
[አምባሳደሩ ለክቡር ሚኒስትሩ ደወሉላቸው]
– ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
– እናንተም ትገማገማላችሁ እንዴ?
– ኧረ ስብሰባ ላይ ነበርኩ፡፡
– እኛም ተገማግመን ስብሰባ ብለን ነው የምንሸውደው፡፡
– ለማንኛውም ምን ልርዳዎት?
– እናንተም ጋ የመልካም አስተዳደር ችግር አለ ማለት ነው?
– የምን የመልካም አስተዳደር ችግር?
– ልጄ እናንተ አገር ያለ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት አመልክቶ ነበር፡፡
– እሺ፡፡
– ዩኒቨርሲቲው ግን አልተቀበለውም፡፡
– ክቡር ሚኒስትር እኛ አገር ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች ለመግባት ዓለም ላይ ያሉ ተማሪዎች እኮ ነው የሚያመለክቱት፡፡
– እና እነሱ አመለከቱ ተብለው የእኔ ልጅ መውደቅ አለበት?
– ማለቴ ውድድሩ ከባድ ነው ልልዎት ነው፡፡
– ይኸው የእናንተ ኢንቨስተሮች አገራችን ላይ እንደፈለጉ እየተንቀሳቀሱ አይደል እንዴ?
– እሱ ከዚህ ጋር ምን ያገናኘዋል?
– በደንብ ነው እንጂ የሚያገናኘው፡፡
– እኮ እንዴት ሆኖ?
– የእኔን ልጅ ነካችሁ ማለት አገሪቷን ነካችሁ ማለት ነው፡፡
– አገሪቷ የእርስዎ ናት ማለት ነው?
– እና የእናንተ ናት፡፡
– ይቅርታ አላወቅኩም ነበር፡፡
– ለማንኛውም ጠብቁ፡፡
– ምን እንጠብቅ?
– ተመጣጣኝ ዕርምጃ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ሲገቡ ጸሐፊያቸውን አስጠሯት]
– ተቃጠልኩ እኮ፡፡
– ምነው ክቡር ሚኒስትር?
– እንዴት እንደሚሞቅ አታይም?
– የሙቀቱን ነገርማ ተውት፡፡
– ተንገበገብን እኮ ባክሽ፡፡
– በዚህ ላይ ደግሞ ኑሮ ውድነቱ ሲጨመር ያስቡት፡፡
– እ…
– ለነገሩ እርስዎ እሱ ብዙም አይገባዎትም፡፡
– ስሚ አሁን ኖት ያዥልኝ፡፡
– የምን ኖት ክቡር ሚኒስትር?
– የአየር ንብረታችን እየተለወጠ ነው፡፡
– ይኼማ ግልጽ ነው፡፡
– ለዚህ ደግሞ ተጠያቂው ማን ነው? ተፈጥሮ ናት?
– የለም የለም፣ ኒዮ ሊብራሎቹ ናቸው፡፡
– እንዴት ሆኖ?
– ተፈጥሮን በቁጥጥር ሥር አውለው ይኸው በሙቀት እያነደዱን ነው፡፡
– እና ምን ይደረግ?
– አሁን በአስቸኳይ ይገዛ፡፡
– ምን ክቡር ሚኒስትር?
– ኤሲ ለሁሉም ሠራተኛ ይገዛ፡፡
– እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
– አየሽ ሙቀቱን መቋቋም የምንችለው ቢሯችን ውስጥ ኤሲ በመክፈት ነው፡፡
– የኑሮ ውድነቱንስ በምን እንቋቋመው?
– ለእሱም መክፈት ነዋ፡፡
– ምን?
– ኤልሲ!
[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ ሚኒስትር ጋ ደወሉ]
– ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
– ምን እየተደረገ ነው?
– ለምኑ ክቡር ሚኒስትር?
– ነጋዴው እኮ እየተንጫጫ ነው፡፡
– ምን ቢንጫጫ አሉ?
– ከፍተኛ ምሬት ነው እኮ ያለው፡፡
– እኮ በምኑ?
– ዕቃው ሁሉ ወደብ ደርሶ መምጣት አልቻለም፡፡
– ምን ይደረግ ክቡር ሚኒስትር?
– ይኼ የመልካም አስተዳደር ችግር ነው እኮ፡፡
– ወደቡ እኮ የእኛ አይደለም፡፡
– የማን ነው ወደቡ?
– የጂቡቲ ነዋ፡፡
– የራሳችንን ገንብተናል አይደል እንዴ?
– እሱማ ደረቅ ወደብ ነው፡፡
– እንዲረጥብ ማጠጣት ነዋ፡፡
– አልገባዎትም ክቡር ሚኒስትር፡፡
– ቢገባኝ ባይገባኝ ኪሴ ካልገባልኝ ምን ያደርግልኛል?
– አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
– መንግሥት እንኳን ይችለዋል እኔ ግን በምን አቅሜ?
– ምኑን ክቡር ሚኒስትር?
– ዲሜሬጁን!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከሾፌራቸው ጋር ወደ ቤት እየሄዱ ነው]
– ጨዋታውን ተመለከቱት እንዴ?
– የምን ጨዋታ?
– እግር ኳሱን ማለቴ ነው፡፡
– ዌኬንድ ላይ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ነበረ እንዴ?
– ኧረ የአገርዎትን ነው ያልኩዎት?
– እንግሊዝም ብትሆን አገራችን ናት፡፡
– ለነገሩ ፓስፖርት እንዳለዎት አውቃለሁ፡፡
– የምን ፓስፖርት?
– ያው በዜግነት ኢትዮጵያዊ ቢሆኑም…
– እ…
– በኢንቨስትመንትዎ እንግሊዛዊ ነዎት፡፡
– እንዴት ማለት?
– እዚህ ካለዎት ሀብት እዚያ ያለው ይበልጣል ብዬ ነዋ፡፡
– ይኼን ነው ስታወራ የምትውለው አይደል?
– ብቻ ሕዝቡ አፍሯል ክቡር ሚኒስትር፡፡
– ምን ሆኖ?
– በቡድናችን ውጤት፡፡
– ተሸነፍን እንዴ?
– ሽንፈት ቢሉ ሽንፈት ነው፡፡
– በማን ነው የተሸነፍነው?
– በአልጄሪያ፡፡
– ስንት ለስንት?
– 7ለ1
– ቀኑን ሙሉ ነው እንዴ የተጫወቱት?
– እነሱማ የሚሉት ሌላ ነው፡፡
– ምን እያሉ ነው?
– ውጤቱን አጥብበነው ነው የመጣነው፡፡
– ጭራሽ?
– እህሳ ክቡር ሚኒስትር፡፡
– ከዚህ ሽንፈት ግን እኔም የተማርኩት ነገር አለ፡፡
– ምን ተማሩ?
– የጥርነፋ ስትራቴጂያችንን መቀየር እንዳለብን፡፡
– አንድ ለአምስቱን?
– አዎና፡፡
– በምን?
– በአንድ ለሰባት!