ውሃ በፈረቃ ፥ የሙታንን መነሳት ተስፋ እናደርጋለን ( ሄኖክ የሺጥላ )
ውሃ በፈረቃ ፥ የሙታንን መነሳት ተስፋ እናደርጋለን ( ሄኖክ የሺጥላ )
ኣንድ ወዳጄ አዲሱን የአዲስ ኣበባ “ውሃ በፈረቃ” ዜና እንደሰማ ፥ « ድሮ በምን ነበር ?» ብሎ የጠየቃት ጥያቂ ፈገግ ኣድርጋኛለች።
የኣዲስ ኣበባ የመሬት ትሎች ዛሬ ዛሬ ከኣፈሩ ይልቅ ለመኖሪያነት ቧንቧውን ይመርጣሉ። ለምን ቢሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ውሃ ከሚመጣበት ቀን ይልቅ « መሬቱ ለ ኢንቨስትመንት ይፈለጋል እና ተነሱ» የሚለው የመንግስት ማስታወቂያ የሚሰማበት ይልቃልና።
ኣንደውም ኣንድ ዘመዴ « ጉዳዩ የውሃ ጉዳይ ሆኖብኝ እንጂ ይሄንንም ቧንቧ እንደ ኢቲቪ ጥርቅም ኣድርጌ ዘግቼው ባረፍኩ ነበር !» ያለችኝን ባነሳስ!
ለነገሩ ኣባይ ተገድቦ እንዳለቀ ፈረቃው ይቀራል ልል ብዬ ፥ ለካስ ኣባይ ለመጠጥ የሚሆን ውሃ የለውም ለግድብ እንጂ! ብዬ ያባይን ነገር ለግብፆች ትቼ ወደ ኣዋሽ ገሰገስኩ ። ኣዋሽ ስደርስ ኣዋሽ ከነ ኣባ ሳሙኤል እና ገፈርሳ ጋ ኣምስት ለኣንድ ኣልጠፈነግም ብሎ ፥ ህገ መንግስቱም ኣይመለከተኝም ብሎ እንደ ዋቢ ሸበሌ ኣሸዋ ውስጥ መኖር እንደጀመረ ሰማሁ ።
በነገራችን ላይ በወንዞች የተከበበችው ሸገር ውሃ ሲጠማት ትግራይ እንዴት ኣድራ ይሆን ?
ማን ነበር
« ኣይጫንም እንጂ ውሃ በመኪና
መቀሌ ነበሩ ኣባይና ጣና » ያለው ።
እነሱ ምናቸው ሞኝ ነው በመኪና የሚጭኑልህ ሃይላንድ እያለ!
ኣዲስ ኣበቤዎች የክርስቶስን ፥ የውሃን እና የመብራትን መምጫ እስከ ዛሬ ኣያውቁትም ነበር ፥ ዋን ኢዝ ዳወን ናው ። መብራትም በፈረቃ ሆነ የሚለውን ዜና ስንሰማ ምናልባት ያኔ « የሙታንንም መነሳት ተስፋ እናደርጋለን !» ብለን ካንጀታችን እንፀልያለን ። ሲሆን ስላየን!
