የጃዋር መሐመድ ቅኝቶች
ክንፉ አሰፋ

መገናኛ ብዙኀንን መቼ እና እንዴት መጠቀም እንዳለበት ጠንቅቆ ያውቃል። የሚፈልገውን ነገር ሁሉ ከፈጸመ በኋላ ግን እንደ በረሃ ተኩላ እያደፈጠ ይናከሳል። ሲናከስ ደግሞ ማንንም አይምርም። ውለታ የሚባል ነገር አያውቅም። ይሉኝታ አይነካካውም። እፍረትም በእርሱ ዘንድ የለችም። ከቶውን መቀበል እንጂ መስጠትን አያውቅም። አስር ተቀብሎ በዜሮ የሚሸኝ ጀግና ነው። በዚህ ተግባሩ አድናቂው ነኝ። “እኔ-ነኝ” ያለ የዲሲ ፖለቲከኛን ሳይቀር ከአንዴም ሁለቴ እንደማስቲካ እያኘከ መትፋቱን እንመሰክራለን። የጡት አባቱ የሆነው ኦነግንም ቢሆን ‘A Critical Assessment of the Oromo Liberation Front” በሚለው መጣጥፉ እንዳይሆን እንዳይሆን አድርጎ የጠረበ ፍጡር ነው። ይህ ሰው እንደገና ተመልሶ የ”ነፍጠኛውን ሜድያ” ለመጠቀም የማይሞክርበት ምክንያትም የለም።