ማንነት መሬት ላይ አይዘራም
ጌታቸው ኃይሌ

ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ማንነት ዋና የመወያያ ርዕስ ሆኖ ቈይቷል። የሥነ ልቡና ምሁራን identity crisis የሚሉት ነው እንዳልል ያተኰረው “እኔ ማነኝ” ከሚለው ላይ አይደለም። ያተኮረው “ማንነት ከመሬት ጋር ይያያዛል ወይስ አይያያዝም?” ከሚለው ጥያቄ ላይ ነው። ውይይቱን እንዳዳመጥኩትና እንደሰማሁት፣ እኔም አስተያየቴን እንድሰጥ ተጠይቄ እንደተቸሁት፣ ማንነትን ከመሬት ጋር የሚያያይዙ እምነታቸውን ከኃይማኖት እምነት ደረጃ አድርሰውታል። ስለዚህ እነሱን በማስረጃ ማሳመን ሃይማኖታችሁን ለውጡ እንደማለት ሆኗል። “እምነቱ ሀገር አጥፊ ነው፤ ተውት” ቢባሉም፣ ማንነታቸው ከያዙት መሬት ጋር ከተቆራኘ፣ ይህ አደገኛ አቋማቸው ለሚያስከትለው ሀገራዊ ችግር አንዳች ሥጋት አይታይባቸውም። ክልል ይዞ ኢትዮጵያዊ መሆን ይቻላል የሚሉም አይጠፉም። መሳሳታቸውን መስማት አይፈልጉም፤ ግን ማንነት የሚዘራበት መሬት የሚያስፈልገው ዳጉሳ አይደለም።