የቢዝነስ ስልኮች ፦ክቡር ሚኒስትሩ አንድ ትልቅ ሆቴል ውስጥ የቀጠሩት ደላላ አረፈደባቸው::
[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ ትልቅ ሆቴል ውስጥ የቀጠሩት ደላላ ስላረፈደባቸው ደወሉለት]
– ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
– የት ደርሰሃል?
– ኧረ ክቡር ሚኒስትር ታስሬያለሁ፡፡
– ማን አሰረህ?
– ማለቴ መንገዱ ተዘጋግቶ አንድ ቦታ ታስሬያለሁ፡፡
– ለምንድን ነው መንገድ የተዘጋው?
– ስብሰባ አለ ነው የሚሉት፡፡
– የምን ስብሰባ?
– የአፍሪካ ኅብረት ነው ምናምን አሉ፡፡
– ታዲያ ሌላ አማራጭ መንገድ አትጠቀምም?
– ወይ አማራጭ መንገድ?
– ምነው?
– ሁሉም መንገድ ተዘጋግቷል ስልዎት፡፡
– ኪራይ ሰብሳቢ ነህ ልበል?
– ምነው ክቡር ሚኒስትር?
– እንዴት ምንም መንገድ የለም ትላለህ?
– የለማ ታዲያ ምን ላድርግ?
– ለዚህ እኮ ነው ኪራይ ሰብሳቢ ነህ ያልኩት፡፡
– እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
– ሰፈር ውስጥ ሳይቀረን አይደል እንዴ መንገድ የሠራነው?
– ምን አሉኝ?
– እንደ ሠንሠለት የተያያዘ መንገድ አይደል እንዴ የሠራነው፡፡
– አይ ክቡር ሚኒስትር፡፡
– እና አልደርስም እያልከኝ ነው?
– ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር፡፡
– ምን ዓይነት ጣጣ ነው?
– ለምንድን ነበር የፈለጉኝ?
– ለጥብቅ ጉዳይ ነዋ፡፡
– በስልክ አይነግሩኝም?
– በስልክ የሚነገር አይደለም፡፡
– ለዛሬ ቢነግሩኝም ግን ችግር የለውም፡፡
– ለምንድን ነው ችግር የሌለው?
– ያው ቢግ ብራዘሮች በከተማዋ ትልቅ ስብሰባ ስላለ በዛ ስለሚጠመዱ እኛ ትዝ አንላቸውም ብዬ ነው፡፡
– ፈልጌ ነበር፡፡
– ምንድን ነው የፈለጉት?
– ዶላር ነዋ፡፡
– ይጠይቁዋ ታዲያ?
– የት ነው የምጠይቀው?
– ባንክ ነዋ፡፡
– ቀልዱን ለምን አትተውም?
– ክቡር ሚኒስትር ሰሞኑን እኮ ቅጥል ነው ያደረጋችሁን፡፡
– ለምንድን ነው የተቃጠላችሁት?
– በቃ ዶላር ሰውን አንበሽብሻችሁት እኛ ጋ እኮ ወደቀ፡፡
– ያጋጥማል እንግዲህ፡፡
– ክቡር ሚኒስትር ክፉኛ እኮ ነው የከሰርኩት፡፡
– ስንት ከሰርክ?
– ኧረ አልጠራው ቁጥሩን፡፡
– ለምን?
– ስጠራው ያመኛል፡፡
– አስፕሪን መዋጥ ነዋ፡፡
– አስፕሪን የሚያሽለው ቁጥር አይደለም፡፡
– ለማንኛውም በአስቸኳይ ፈልግልኝ፡፡
– ምን ያህል?
– የቻልከውን ያህል፡፡
– መቼም እኔ ለእርስዎ የማልሆነው ነገር የለም?
– እኔስ ለአንተ የማልሆነው ምን አለ?
– ድር ቢያብር …
– ዶላር ያስር!
[ክቡር ሚኒስትሩ ለምሳ ቤት ሲሄዱ ሚስታቸውን አገኟቸው]
– እኔ የምልሽ?
– ምንድን ነው?
– የአንቺ ቢዝነሶች መቼ ነው የሚያተርፉት?
– ምን ለማለት ፈልገህ ነው?
– ባለፈው ማተሚያ ቤት ክፈትልኝ አልሽ ከፈትኩልሽ፡፡
– እናሳ?
– ከዛም በኋላ ሞባይል ቤት አልሽ እሱም ተከፈተ፡፡
– ልክ ነው፡፡
– ትርፍ ግን ሲያመጡ አላይም፡፡
– እንዴት ማለት?
– ቢያተርፉ ኖሮማ እስኪብርቶ እንኳን ትገዥልኝ ነበር፡፡
– እኔ እኮ ከእስኪብርቶ ፋብሪካው ይሻላል ብዬ ነው፡፡
– የምን ፋብሪካ?
– የእስኪብርቶ ፋብሪካ ነዋ፡፡
– ትቀልጃለሽ?
– የምን ቀልድ ነው፤ መንግሥት ራሱ ወደ ኢንዱስትሪ ግቡ እያለ አይደል?
– እሺ የእኛ የኢኮኖሚ ተንታኝ፡፡
– ተሳሳትኩ እንዴ?
– ስሚ መቼም በከፈትኩልሽ ቢዝነሶች ከብዙ ሰዎች ጋር ትገናኛለሽ ብዬ አስባለሁ?
– አዎን ምነው?
– እስኪ አፈላልጊልኝ፡፡
– ምንድን ነው የማፈላልግልህ?
– ዶላር ነዋ፡፡
– ምን ያህል?
– ቁጥሩን ቴክስት አደርግልሻለሁ፡፡
– ዶላር ስትል እኔንም አስታወስከኝ፡፡
– ምንድን ነው ያስታወስኩሽ?
– እኔም እፈልጋለሁ፡፡
– ምን?
– ዶላር ነዋ፡፡
– ለምን?
– አሜሪካ ያለችው ልጃችን ምርቃት እኮ ደርሷል፡፡
– ወይ ጣጣ፡፡
– ሲሆን አንተም መምጣት አለብህ፡፡
– አገሪቷን ለማን ትቼ?
– ስለዚህ እኔ ከእህቴ ጋር እሄዳለሁ፡፡
– ስለዚህ?
– ያው ለሁለታችንም የሚበቃ ዶላር ፈልግልና፡፡
– ወይ ጣጣ፡፡
– ከዛም ልጅህን ትንሽ ማዝናናት አለብኝ፡፡
– ምን ዓይነት ነገር ነው?
– እንድታስብበት ብዬ ነው፡፡
– ምኑን?
– ዶላሩን!
[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ዳያስፖራ ደወለላቸው]
– ሄሎ!
– ምነው ክቡር ሚኒስትር?
– ምነው?
– የተበሳጩ ይመስላሉ፡፡
– ምን ባክህ አስቸጋሪ ሆነ እኮ?
– ምኑ?
– ዶላር ማግኘት፡፡
– ይኸው ሰሞኑን እንዳንበሻበሻችሁት ሰምቼ አይደል እንዴ!
– እኛ አልተንበሻበሽንማ፡፡
– ለራስዎት ነው እንዴ የፈለጉት?
– አዎን፡፡
– ለምን አልክልዎትም እኔ ታዲያ?
– አንተ ብትልክልኝም እዚህ የሚደርሰኝ በብር ነው፡፡
– እሱስ ልክ ነው፡፡
– ሲቀጥል የምፈልገው መጠን ደግሞ አንተ የምትችለው አይደለም፡፡
– ይኼን ያህል?
– አገሪቷ እኮ አድጋለች፡፡
– እርስዎም አድገዋል እንጂ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ አማካሪያቸውን አስጠሩት]
– መቼም የግል ሚዲያ ትከታተላለህ?
– አዎን ክቡር ሚኒስትር፣ እርስዎም ቢከታተሉ ጥሩ ነው፡፡
– አንተን የቀጠርኩህ ተከታትለህ ሪፖርት እንድታደርግ መስሎኝ?
– አይ እንዲሁ ነገሩን ነው፡፡
– ለመሆኑ ሰው ዶላር ከየት ነው የሚያገኘው?
– ያው ከባንክ ነዋ፡፡
– ከዚያ ሌላ?
– ከብላክ ማርኬት ነዋ፡፡
– ከእሱ ሌላ?
– ከሰሞኑ ስብሰባ ነዋ፡፡
– ቀልዱን ተው እስቲ፡፡
– ማለቴ ለአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ከሚመጡት ተሰብሳቢዎች ማለቴ ነው፡፡
– እንዴት ማለት?
– ያው ተሳታፊዎቹ ዶላር ይዘው ስለሚመጡ ከእነሱ ሊገኝ ይችላል፡፡
– የት ነው የሚገኙት እነሱ?
– ሆቴላቸው ነዋ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ ባለሆቴል ወዳጃቸው ጋ ደወሉ]
– ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
– እንዴት ነህ ባክህ?
– ዛሬ ከየት ተገኙ?
– ሁሌም እኔ ነኝ እንጂ አንተ መቼ ትፈልገኛለህ?
– አይ ክቡር ሚኒስትር እርስዎም ጉዳይ ሲኖርዎት ነው የሚፈልጉኝ፡፡
– እ…
– ምን ልታዘዝ ታዲያ?
– ሥራ እንዴት ነው?
– ያው ከእጅ ወደ አፍ ነው፡፡
– የሆቴል ሥራውን ማለቴ ነው፡፡
– ምንም አይል፡፡
– ሰሞኑን እንግዶቹ እየመጡ ነው?
– አዎ ሰሞኑን እንኳን ቢዚ ሆነናል፡፡
– አንድ ነገር ላስቸግርህ ነበር፡፡
– ምን ክቡር ሚኒስትር?
– ለአክስቴ ልጅ እናንተ ሪሰፕሽን ጋ ትንሽ ሱቅ ፈልጌ ነበር፡፡
– የምን ሱቅ?
– የዶላር መመንዘሪያ፡፡
– እሱ ሥራ እኮ የመንግሥት ፈቃድ ያለው ባንክ ብቻ ነው የሚሠራው፡፡
– ስለእሱ አታስብ፡፡
– እንዴት አላስብ ክቡር ሚኒስትር፡፡
– እኔ ሁሉን ነገር እጨርሰዋለሁ፡፡
– ይጠንቀቁ ግን፡፡
– ምኑን?
– እጨርሳለሁ ብለው እንዳይጨረሱ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ቤት ሲገቡ ሚስታቸውን አገኟቸው]
– እኔ የምልህ?
– ምንድን ነው?
– ዶላሩን የምትፈልገው ለምንድን ነው?
– ለጨረታ፡፡
– የምን ጨረታ?
– ከአንድ የውጭ ኩባንያ ጋር ልሠራው ያሰብኩት ሥራ አለ፡፡
– ሥራ ቀየርክ እንዴ?
– የምን ሥራ?
– ሚኒስትርነትህን፡፡
– ወደ ምንድን ነው የምቀይረው?
– ወደ ኢንቨስተርነት፡፡
– ምን?
– ጡረታዬ እየደረሰ እንደሆነ አትርሺ፡፡
– ለመሆኑ ተሳካልህ?
– ምኑ?
– የዶላሩ ፍለጋ፡፡
– ኧረ ተይኝ እስቲ፡፡
– ምነው?
– ምንም የሚያበረታታ ነገር አይደለም፡፡
– ለመሆኑ የት ነው የፈለግከው?
– ያልፈለግኩበትን ጠይቂኝ፡፡
– እኮ የት የት ፈልገሃል?
– ከአባ ኮራን ሰፈር …
– እ…
– እስከ አባ ኮራፕት ሰፈር! === http://www.ethiopianreporter.com/