የባቡሩ ጦስ!! – ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ሴትና የሰው ጉልበት እርካሽ ነው፡፡›› – በዘሪሁን ገሠሠ
የባቡሩ ጦስ!!
በዘሪሁን ገሠሠ
‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ሴትና የሰው ጉልበት እርካሽ ነው፡፡››
ውድ አንባቢያን በዚህ ፅሁፌ የአዋሽ ኮምቦልቻ ወልድያ /ሀራ/ የባቡር መስመር ግንባታን ተከትሎ ግንባታውን ለመስራት አሸናፊ ሆኖ በቀረበው ያፒ መርከዚ የተሰኘ የቱርክ ኩባንያ ወደሀገራችን በገቡ ቱርካውያን ሰራተኞች እየተፈፀመ ስላለው ባህልና ወግ የማጥፋትና በኢትዮጵያውያን ሴቶች ላይ ስለሚፈፀመው ወሲባዊ ጥቃትና ልቅ የሆነ የወሲብ ንግድ ዘመቻ በቦታው ተገኝቼ የታዘብኩትን ትዝብት እንዲሁም የችግሩ አስከፊነት ከልማቱ የገዘፈ በመሆኑ ለሚመለከታቸው አካላት ማሳሰቢያዬን አቀርባለሁ፡፡
~~~ ~~~ ~~~
እንደአለመታደል ሆኖ በሀገራችን ‹‹ልማት ልማት›› እየተባለ ብዙ ፕሮፓጋንዳ የሚናፈስለትና መንግስት እንደመንግስት ሊሰራቸው የሚገቡ የግንባታ ተግባራት ተመርቀው ለህዝቡ ከሚሰጡት ፋይዳ ይልቅ ግንባታቸውን ተከትሎ ከሀገር ውጭ በሚመጡ ዜጎች እየተፈፀሙ ያሉ ጥፋቶች እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እየደረሱና ባህላዊ፤ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እሴቶቻችንን እየሸረሸሩና እያጠፉ ለቀጣይ ትውልድ ሳይቀር የሚተላለፍ አስከፊ ጠባሳና ነቀርሳ እያስቀመጡልን ብሎም ወደከፋ ቀውስ እያሸጋገሩን ይገኛሉ፡፡ ምናልባት ይህን ለማረጋገጥ በውጭ ዜጎች ሰፋፊ ግንባታ እየተሰራባቸው በሚገኙ የሀገራችን አካባቢዎች ዝለቁና የማህበረሰቡን የልብ ትርታ በማዳመጥ በነዚህ ዜጎች እየተፈፀመ ያለውን ተጨባጭ ለመገምገም ሞክሩ፡፡ እኔም ወደዋናው ርእሴ ልውሰዳችሁ፡፡
~~~ ~~~ ~~~
የኮምቦልቻ ወልዲያ ሀራ የባቡር መስመር በርካታ ሺህ ቱርካውያን ሰራተኞችን ይዞ በገባው ያፒ መርከዚ የተሰኘ ግዙፍ ኩባንያ እየተከወነ ይገኛል፡፡ ኮምቦልቻ ከተማ ደግሞ አንዱ የተቋራጩ ካምፕ የሚገኝባትና በመናገሻነት የተመረጠጭ ከተማ ሆና ከነዋሪው ባልተናነሰ በርካታ የቱርክ ተወላጆች ይርመሰመሱባት ከጀመሩ ዋል አደር ብለዋል፡፡ እነዚህ የቱርክ ሰራተኞች ከመጡለት አላማ በይበልጥ የኮምቦልቻና አጎራባች ከተማዎቿን ሴቶች በማደንና ከባህል ያፈነገጠና ልቅ የሆነ ወሲባዊ ጥቃት ላይ ተጠምደው ይገኛሉ፡፡ የሀይስኩልና የኢለመንታሪ ተማሪዎች፤ ባለትዳር የቤት ወይዛዝርቶች፤ የወሎ ዩኒቨርስቲ ሴት ተማሪዎች፤ ሴተኛ አዳሪዎች፤ …….. የዚህ አሳሳቢ ወሲባዊ ጥቃትና ተያይዘው የሚመጡ የጤናና የስነ ልቦና ችግሮች ሰለባ ሲሆኑ መስተዋል ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል፡፡ ቱርካውያኑ ይህን ድርጊት የሚፈፅሙት በኢትዮጵያውያን አገናኝ ደላሎች መሆኑ ደግሞ ድርቱን አሳዛኝ ያደርገዋል፡፡ ከፍተኛ ገንዘብ በሚከፈላቸው ደላሎች በመታገዝ፤ ገንዘብን በመደለያነት በመጠቀም ያሻቸውን ሴት በማግባባት የቡድን ወሲብን ያካተተ፤ በድብቅ ካሜራዎች ቪዲዎችን በመቅረፅ፤ እጅግ አስነዋሪ የወሲብ ድርጊት ይፈፅማሉ፡፡ የዩኒቨርስቲ ሴት ተማሪዎች እጅግ አሳፋሪ በሆነ ሁኔታ በቱርካውያኑና ደላሎቻቸው ወጥመድ በቀላሉ በመጠመድ ለጊዜያዊ ጥቅም ለዘላቂ ችግርና ቀውስ እየተጋለጡ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ የወሲብ ልማተኞች በሚርም ሁኔታ በኮንዶም መጠቀምን የሚፀየፉና ያለኮንዶም ወሲብ ለመፈፀም ለምትስማማ እንስት ተጨማሪና ከፍ ያለ ክፍያ እንደሚከፍሉ ያነጋገርኳት ከቫይረሱ ጋር የምትኖር ሴተኛ አዳሪ ገልፃልኛለች፡፡ እንደዚች ሴተኛ አዳሪ ገለፃ ቱርካውያኑ ኮንዶምን የማይጠቀሙት ኤች አይቪም ሆነ ሌሎች የአባላዘር በሽታዎችን የሚከላከል ክትባት ስለተከተቡ ነው የሚል አስተያየት እንዳለ ስትገልፅ እስካሁን ከደርዘን ከሚበልጡ ቱርካውያን ጋር ቫይረሱ እያለባት ልቅ የሆነ ወሲብ እንደፈፀመች አልሸሸገችም፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ሴትና የሰው ጉልበት እርካሽ ነው›› ሲል የሰማሁት ሙሀመት የተሰኘ ቱርካዊ ንግግር ቅስሜን የሰበረና ወዴት እያመራን ነው? ለዚህ ብሄራዊ ውርደት የዳረገንስ ምንድን ነው? የሚሉ ሰፊ ጥያቄዎችን ያጫረብኝ ነበር፡፡ በአሁኑ ሰአት ሁኔታው ይፋ ባይወጣም በአካባቢው የቫይረሱ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ እንደጨመረ በመነገር ላይ ይገኛል፡፡ ታዳጊ ህፃናትና ወጣቶች ለከፍተኛ የፌስቱላና፤ የአባላዘር በሽታዎች ብሎም ለአስከፊ ውርጃ እየተዳረጉ መሆኑን ከማህበረሰቡ ውስጥ ዘልቆ በመግባት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ይህ ሁኔታም በዚህ ከቀጠለ የከፋ የባህላዊና ማህበራዊ እንዲሁም ስነልቦናዊ ቀውሱን በማስፋፋት ሀገራዊ ችግር ማስከተሉ ሳይታለም የተፈታ ነውና የሚመለከታችሁ የመንግስት አካላት፤ የአካባቢው ነዋሪዎች፤ የትምህርት ተቋማት ባለድርሻ አካላትና ኢትዮጵያዊ ወገኖች ሁሉ ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ፤ ለዚህ ድርጊት ተባባሪ በመሆን ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ደላሎችንና የድርጊቱ ዋና ተዋንያን የሆኑትን ቱርካውያን የጥፋት ሰራዊቶችን ተገቢውን እርምጃ በመውሰድ ልናስቆማቸው ብሎም በኢኮኖሚ ጥገኝነት ለዚህ ፀያፍ ድርጊት ተገዢ ሆነው በመቸብቸብ ላይ ያሉ እህቶቻችንን ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ምክርና ተግሳፅ ልንለግሳቸው ይገባልና ይህን ሀጋራዊ ጥፋት በእንጭጩ እንቀጨው ዘንድ ወቅቱ አሁን ነው፡፡ የበኩላችንን እንወጣ!!!
————————————————አበቃሁ!!!—–